የተፈራው የጦርነቱ የዜና መረጃዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ሆድ አስፍቶ፣ ጥርስን ነክሶ ሃቁን መቀበል ግድ ነው። ከልብ ሰባሪ የጦርነት ውጤት እውነተኛ ዜና ጦርነትን ለትርፍ ስትገለገሉበት የነበራችሁ ቢያንስ ዛሬ ላይ ተማሩ። ልጆቻችሁን በሙቅ ዕቅፋችሁ ይዛችሁ ደሃን ስታስጨርሱ የነበራችሁ ይብቃችሁ። “በዩትዩብ ስለፈልፍ ልጆቼ ተሳቀቁብኝ፤ ቤት መከራየት አለብኝ” ብለህ ዲሲ ምድር ቤት የተከራየኸውም ባክህን ይብቃህ። ምን ፈልገህና በየትኛው ብቃትህ አገር ለመምራት እንደምትቋምጥ የተረዳህ ሰው አይደለህምና ይብቃህ አቁም። ይህን ሁሉ እያየህ ዛሬም ታጋድላለህ። ዛሬም በየቀኑ መርዝህን ትረጫለህ። ከፍጹም ጥሪ ተማር።
“በለው፣ ስበረው፣ ጀግና፣ ጥይት የማይነካህ … እያሉ ምክንያቱና ውጤቱ በውል በማይታወቅ ጉዳይ ወጣቱን ሲማግዱ የነበሩ ምን ይሉ ይሆን?” በሚል ከሰላም አማራጭ ስምምነቱ በኋላ በርካቶች የካድሬን ባህሪ ባለመረዳት በጉጉት ይጠብቁ ነበር። አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየት ሰጪ “አትጓጉ ተቃቅፈው ሌላ ትርክት ያሰማሉ። ካድሬ ጸጸት ብሎ ነገር አያውቅም” ሲሉ በድፍረት ጽፈዋል።
ካድሬ ካድሬ ነው። ካድሬ ይሉኝታ የለውም። አሜሪካ ቁጭ ብለው የሚሰብኩትን የሚተነትኑት ትናንት የትህነግ ባሪያ የነበሩ ካድሬዎች ናቸው። ትናንት ሲሉት የነበረው በፊልም ማስረጃ ፊታቸው እየታየ አይፍሩም። ትናንት ከትህነግ በላይ ትህነግ ሆነው ሕዝብ ላይ ሲተፉ የነበሩ ዛሬ ተቃዋሚ መስለው ጦርነትን በየገጹ ይሰብካሉ። አንዱ ሲበላሽባቸው ሌላ እየፈበረኩ ሊያጋድሉ እንደ ጅብ ሌሊት ሌሊት ይጮሃሉ። ከሁሉም በላይ እነዚህን እየሰማ የሚነጉደውና ለእነርሱ ከርስ መሙያ መሃረቡን የሚፈታው ደነቋቁርት ነው።
ትናንት ልጆቹ በአደባባይ ግምባራቸው እየተለየ በአልሞ ተኳሽ እንዲፈርስ ተደርጎ ሲጨፍጨፉ፣ አንተ አስከሬን ታቅፈህ፣ እናት ጎዳና አስከሬን ላይ ተኝታ፣ “ሌቦች ናቸው” ሲል በልጆቻችን አስከሬን የፖለቲካ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ሲተፋ ለነበረ ካድሬ ማታ ማታ ግብር ማስገባት እጅግ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ወራዳነትም ነው። ከዛም በላይ በግፍ በተደፉት ልጆቻችን ደም ላይ የመደነስና የመማማል ያህል ነው። ለኢህአዴግ እያለቀሰ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ሲመለምል የነበረ ካድሬ ዓይኑን በበረኪና አጥቦ ሲያጭበረብርህ መረዳት የማትችል አንተ “ምንድን ነህ? እናንተ ምንድ ናችሁ? ምን እንዲሆን ነው የምትፈልጉትና ኪሳችሁን የምታራግፉት? ስለምን ነው የትናቱን የማታስቡት?” ከጦርነቱ በኋላ የሚሰሙትን ዘግናኝና ልብ ሰባሪ ዜናዎች ስትሰሙ እጃችሁ እንዳለበት አስቡ። ነገሩ ትግራይ ላይ ብቻ አያበቃም። አያያዙና ፍላጎቱ ሌላ ነው።
የጦርነት አታሞ ሲመቱ የነበሩ፣ ጦርነቱን እንደ አክሽን ፊልም ሲተርኩና ነዳጅ ሲጨምሩ የነበሩ፣ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ኪሳቸውን እያሳበጡ የነበሩ፣ በፍጹም እብደት ሲከንፉ የነበሩ፣ እብደታቸውን ዕውን ለማድረግ የጥላቻና የማጋደያ መርዝ ሲረጩና ሲያከፋፍሉ የነበሩ፣ በየቀኑ፣ በየሰዓቱ እብሪት ሲረጩና በደመነፍስ በተከታዮቻቸው አበባ ሲረጭላቸው የነበሩ፣ አዲስ አበባ ለመግባት መንገድ ሲያማርጡ የነበሩ፣ በምንም ምክንያት እርቅ የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል ታብየው ሲያናፉ የነበሩ … አለቆች፣ ጀሌዎች፣ አድማቂዎች፣ ተቀጣሪና ተላላኪዎች፣ ተከፋዮችና አጎብዳጆች… ሁሉም ከዚህም ከዚያም ውጤቱን በድሃ እልቂት ደመደሙት። ደሃን አካለ ጎዶሎ አድርገው ለሌላ የሥልጣን ዘመናቸው መማማል ጀመሩ።
“በአጭር ጊዜ ጠቅ ጠቅ አድርገን እንጨርሰዋለን፤ ጊዜ እንዲወስድ አንፈልግም” እያለ የቅዠት ትንተና ሲሰጥ የነበረው የዳንኤል ብርሃኔ ወንድም ፍጹም ብርሃኔ አሳዛኝ ጥሪ ማስተላለፉ ከላይ የተባለውን የሚያጸና ነው። የጦርነቱ ውጤት ሲሰላ ከንቱ ሞትና አካለ ጎዶሎ መሆን ሆነ።
“ከውጪ አገር ወደ አገር ቤት የምትመጡ ተጋሩዎች ከቻላችሁ አንድ ዊልቼር ይዛችሁ እንድትመጡ እማፀናችኋለሁ፤ የበርካታ ወጣቶችን ተስፋ ታለመልማላችሁ” ሲል ነው በትግርኛ ጥሪውን ያቀረበው። የፍጹም ብርሃኔ ጥሪ አግባብነት ያለውና ወደ ቀልቡ መመለሱን የሚያመላክትና ሌሎች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ የሚገፋ መልዕክት ሆኖ ተገኝቷል። ፍጹም የቀድሞ ቀረርቶውን አስቦ ከራሱ ጋር እልህ ሳይጋባ፣ ወቅታዊ እውነታውን ተረድቶ ይህን ማለቱ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግር እያለ እዛ ላይ ማተኮር ትተው “አካኪ ዘራፍ” እያሉ የጦርነት እስክስታ ለሚመቱ ትምህርት የሚሰጥም ይሆናል።
አንዳንዶች ትግራይ ምድር ላይ ምን እንደሆነ አሁንም ያልገባቸው “ከብልጽግና ጋር ሆነን ሻዕቢያን እንውጋ፣ እሱ አይሆንም ከሻዕቢያ ጋር ሆነን ኢትዮጵያን እንውጋ” እያሉ የሚደናቆሩትን ዕልቂት ጠማቂዎች ወግዱ በማለት ፍጹም ላቀረበው ጥያቄ ኢትዮጵያዊያን ምላሽ ሊሰጡ ግድ ነው። መሬት ላይ እየተንደባለላችሁ ፊልም ስትሠሩ የነበራችሁ፣ በአንድ ሌሊት በሚሊዮን ስታዋጡ የከረማችሁ አሁን ዊልቸር ለማስገባት ተሟሟቱ። ይህ የወቅቱ ጥያቄ ነው።
“እናቴን አላገኘኋትም!”
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዩጂን – ኦሬገን ላይ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና በሴቶች አሥር ሺህ ሜትር የተሰለፈችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ከሁለት ዓመት መለያየት በኋላ ዛሬ ከቤተሰቦቹ ጋራ መተያየቱን እና እናቱን ግን እንዳላገኛቸው ገልጿል።
“ሰላም ያመጡ ሰዎችን አመሰግናቸዋለሁ። ወደ ሀገሬ በመምጣቴም ደግሞ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ሆኖም እናትና ሀገር አንድ ናቸው። ባጋጠመው ሊሆን በማይገባው ሁኔታ በመድኃኒት እጦት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ነግረውኛል” ሲል እያነባ ስሜቱን ለቢቢሲ ነበር የገለጸው።
ቢቢሲ ለተቀጠረበት ዓላማ ጦርነቱን ሲያነድና ሲቆሰቁስ የነበረ፣ የትግራይ ወጣቶች እንዲነሱ ወስዋሽ መረጃ ከሙያው አፈልግጦ ሲበትን እንዳልነበር፣ ዛሬ ለቅሶና ሲቆሰቁሰው የነበረው ጦርነት ያስከተለውን ማኅበራዊ ወለምታ ማስተጋባት ጀምሯል።
ደብረፅዮን ስለ ደራርቱ ቱሉ ምን አለ?
በመቀሌ በተካሄደው የአትሌቶች ውይይት ላይ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሆነው ደብረጽዮን “ከሁሉም በፊት በራሴና በትግራይ ሕዝብ ስም ደራርቱን ላመሠግን እወዳለሁ፤ ከዚህ ቀደም ወደ ጦርነት እንዳንገባ ወደ’ኔ እየደወለች ነገሩ የከፋ ደረጃ እንዳይደርስ እባካችሁ ለሕዝባችሁ ስትሉ ሁለታችሁም ተሸነፉ ስትል ስለ ሰላም ያላትን ፅኑ አቋም ስታንፀባርቅ ነበር” ሲል ተናግሯል።
ደብረፅዮን ልቡ በእብሪት በተሞላበት ወቅት “ውጊያው አልቋል፣ እጃችሁን ስጡ” ሲልና “እኛ ትግራይ ሰላም ነን፤ ከኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ያለበት ብቸኛ ቦታ ትግራይ ነው፤ ሰላም የሌለባቸው ቦታ ሂዱ…” በሚል ዕርቅ የገፋው ሰውዬ “ደብረጽዮን ይህን አሉ” እያሉ እንደ ትልቅ መሪና አሳበ ያለው ሰው ሚዲያ ነን ባዮቹ ሲቀባበሉት ማየት አሳፋሪ ነው።
“ተሸንፈናል፤ ሽንፈታችንን ግን አሳምሩልን” ብሎ በጌቶቻቸው አማካይነት ከሞት የተረፈው የትህነግ መሪ “ደራርቱ በችግራችን ወቅት ከጎናችን የነበረች የሰላም ሰው በመሆኗ ደግሜ ደጋግሜ አመሰግናታለሁ፤ ከትግራይ አትሌቶች ጎን እንደ እናት በመሆን ብርታት የሆነቻቸው ደራርቱ የትግራይ አትሌቶች በችግር ውስጥም ሁነው በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማድረግ በመቻላቸው ክብር ይገባቸዋል፤ የፅናትም ተምሳሌቶች ናቸው” ሲል ያለ አንዳች ሐፍረት መናገሩ ለወደፊት ካድሬን የምርጫ ዋዜማ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም አግባብ ማመን እንደማይቻል ማረጋገጫ የሰጠ ንግግር ከመሆን የዘለለ አይሆንም።
ዛሬ ላይ በመናበብ የሚሰሩ የአማራና የኦሮሞ ጽንፈኞችን የሚደግፉ በተመሳሳይ ዊልቼር ከመለመን ወደሁኋላ እንደማይሉ መታመን አለበት። ምክንያቱም እነዚህ ጽነፈኞች ከትህነግ በላይ መሳሪያ፣ ጦር፣ የፖለቲካ ኃይል፣ አደረጃጀት፣ ሃብት፣ … የላቸውም። የኢትዮጵያ መከላከያዋ ባዶ ቤት ሆኖ፣ የስለላ ተቋሟ ፈርሶ፣ ፖሊስ አልባ ሆና ትህነግን ከትክታዋለች። ትዕቢቱን አስተንፍሳ ለማኝ አድርገዋለች። እናንተ ከትህነግ አንጻር ኢምንት ናችሁና ነገ በተመሳሳይ ዊልቼር ከመለመን፣ ወጣቱን ከማስጨረስ ተቆጠቡ። አቁሙ። ትግላችሁን የሰለጠነና የሃሳብ ብቻ አድርጉ። (Ethio12)
Tesfa says
ለገባው የሃበሻ ፓለቲካ ሸፋፋ ነው። በወረፋ ከመገዳደል ያለፈ ምንም ለህዝባችን የፈየደው ነገር የለም። በብሄር ነጻነት ስም ጠበንጃ አንስተው በረሃ በመግባት የተፋለሙና የነበረውን መንግስት ስልጣን በሃይል ቀምተው በስልጣን ላይ የወጡ ሃይሎች ሁሉ ከበፊቱ ቢከፉ እንጂ የተሻለ ነገር ለህዝባችን አላደረጉም። ያው በህዝብ ስም መነገዳቸው ግን የታየና የተሰላ ሂሳብ በመሆኑ አይንና ጀሮ ያለው ይረዳዋል። 17 ዓመት ወያኔና ደርግ ሲፋለሙ የደረሰው ግፍ አልበቃ ብሎ ከ 27 ዓመት የአስረሽ ምቺው አገዛዝ በህዋላ ወያኔ ከስልጣን በሾኬ ጠለፋ ሲገፈተር መቀሌ ላይ መሽጎ የትግራይን ህዝብ ለድጋሚ ስቃይ መዳረጉ የስልጣን ጥማቱ ከ 27 ዓመት በህዋላ እንኳን አለመርካቱን ይነግረናል።
አንድ ዲስኩረኛ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ መብረቃዊ ጥቃት በማድረግ የሰሜን ጦርን ተቆጣጥረናል ብሎን ሲያልፍ ሌላው ቋሚ የወያኔ የጦር መሪ ደግሞ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ጦርነቱ እኮ አልቋል እንዳላሉን ሁሉ አሁን ጅራታቸውን እግሮቻቸው መሃል ሸጉጠው ለትግራይ ህዝብ ስንል የሰላም ውል ገብተናል ማለት ከእብደትም እብደት ነው። ጦርነቱ ግን የቆመው ስለተሸነፉ ነው። ይህ የሰላም ውልም አይጸናም! ወያኔ በባህሬው ሰላምን አያውቃትምና! ለጊዜው ግን ሁለቱንም ጎራ አሸሸ ገዳሜ ያሰኛል። የቀድሞው የናይጀሪያ መሪና የአሁኑ የእርቅ አጋፋሪ ወደ 600 ሺህ ሰው አልቋል ይለናል ቆሞ እንደቆጠረ። አንድ የሳተላይትና የዓይን ምስክርን መረጃ ተመርኩዞ ያወጣው አሃዝ ደግሞ ታጣቂና ሰላማዊ ህዝብን ጨምሮ 1.5 ሚሊዪን ህዝብ አልቋል ይላል። ትክክለኛ ቁጥሩን ሟች የወደቀበት መሬትና የተቀራመቱት የሰማይ አሞሮችና የድር አራዊቶች ያውቃሉ። ሌላው ሁሉ የነሲብ ስሌት ነው። ግን ለጥቁር ህዝብ ማን ገዶት። ወያኔን ከሰማይና ከምድር አይዞህ አለን ይሉት የነበሩት አሜሪካኖች ያላቸውን ካርድ ሁሉ ተጫውተው ጦርነቱ በእነርሱ ስሌት ባለመሄድ የብልጽግናው (የድህነቱ) መንግስት ላይ ጫና በማድረግ ዛሬ ላለንበት በቅተናል። ጥያቄው ሰላሙ ይዘልቃል ወይ? ባይገባን ነው እንጂ የሚያስታርቁን ናቸው እሳት የሚጭሩት።
ትላንት በምዕራባዊያን ከተሞች ተመሽገው በለው ሲሉ የነበሩ አፍቃሪ ወያኔዎች ዛሬ ያ ሁሉ ጭኸታቸው ውሃ ገብቶ ሲሰጥም ምን ይሰማቸው ይሆን? እውነት እነዚህ ዘር አዝማዳቸውን በስደት ከሃገር አስወጥተው ሌላውን በለውና በሉት ይሉ የነበሩ የሃበሻ አረመኔዎች ህሊናቸው ጤነኛ ነው? ፍትህ ቢኖር የወያኔ መሪዎችና ያን ሁሉ ውድመት በሰውና በንብረት ላይ ያደረሱት ሁሉ ፍርድ በተሰጣቸው ነበር። ግን ጠበንጃ አንጋች እንደ አሸን በፈላበት ምድር እንደ እንቁራሪት ከባለቀን ጋር አብሮ መንጋጋት እንጂ ጥሬ ቆርጥሞ በሰላም ለመኖር ለሚሻው ህዝባችን የሚያስብ የለም። ዛሬ በየዜና ማሰራጫውና በሶሻል ሚዲያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ በረረ ገለ መሌ መባሉ ሃብት ያለውን ለማጓጓዝ እንጂ 99% የትግራይ ህዝብ 8ሺህ ብር ከፍሎ ለመብረር አይችልም። ለሰፊው ህዝብ ቆመናል የሚሉት ወያኔና የድህነቱ መንግስት በጋራ ያፈረሱትን ድልድዪችና መንገዶች በመጠገንና ተሽከርካሪ በማቅረብ ህዝብ በነጻነት ወጥቶ የሚገባበትና ወደ ፈለገው ደርሶ የሚመለሰበት ብልሃት እስካልተፈጠረ ድረስ ትንሽ ከወያኔ ጋር አብረው የዘረፉና የወያኔ ደጋፊዎች መቀሌ አየር ማረፊያ ደርሰው እልል መባሉ ፋይዳ ቢስ ነው።
ባጭሩ የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ኮኸን በቅርቡ እንዳሉት ” የወያኔ ከትግራይ ህዝብ ጀርባ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማውረድ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላ ሃገራችን አዲስ ምዕራፍ ከፋች ይሆናል” ያለበለዚያ ያው መልካቸውን እየለዋወጡና ሌላ የሞት ነጋሪት እየመቱ ዳግም ለመፋጀት እንደማይተኙ ሳይታለም የተፈታ ነው። መገዳደል በቃ። በዘር መሰለፍ ይቁም፡ ሃገሪቱ ለትግራዩም ለአማራውም ለኦሮሞውም የጋራ እንጂ በክልል እየከፈሉ አጥር ማበጀት ይቁም። ወንዝ የማያሻገርን ቋንቋ እያመለኩና የሌለ ታሪክ እየፈጠሩ ከመፋተግ አይንና ጆሮአችን ከፍተን አንድ አርጎ ልዪነታችን በአንድነታችን የሚጎላበት መንገድ መፈለግ አማራጭ የማይገኝለት ነው። ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ ኑራ አታውቅም። ይህ የ 21ኛ ዘመን እብደት ተምረናል በሚሉ ድውያን የመነጨ የመከራ ዝናብ ነው። የትግራይ ህዝብ ጠላቱ በፊትም፤ ዛሬም ወደፊትም ወያኔ ነው። ማንም የውጭ ሃይል ትግራይን በሃይል ወሮ ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የራሳችሁ ጉዳይ ነው ያለበት የታሪክ ጊዜ አልነበረውም ወደፊትም አይኖርም። ኤርትራም አማራም የትግራይ ህዝብ ጠላቶች አልነበሩም አሁንም አይደሉም።
በመዝጊያው የትግራይ ህዝብ አሁን ነው እርዳታና ድጋፍ የሚሻው። ያኔ ጦርነቱ እንዲፋፋም ሲገፋፉ የነበሩ ሁሉ ዛሬ ነው ይህን ህዝብ ከገባበት መጠራቅቅ ለማውጣት በተግባር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ ያለባቸው። የሃበሻዋ ምድር ገመናና ችግር እልፍ ቢሆንም በዚህ ጦርነት አካለ ጎደሎ ለሆኑ ሁሉ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ግን ዛሬም በጦርነቱ ለተሰው የትግራይ ልጆች አታልቅሱ የሚሉ የወያኔ ድርቡሾችንም በሃሳብ መፋለም ተገቢ ይሆናል። እንደ ፍጽም በርሄ ያሉት የትግራይ ልጆች ያለፈውን የጦርነት ቁስቆሳ በመተው ለትግራይ ህዝብ ተጨባጭ ነገር ለማድረግ መጣራቸው ጎሽ በርቱ ያሰኛል። መገዳደላችን ይብቃ። የኢትዮጵያ የፓለቲካ እውነት በቴሌቪዝን የምናየው አይደለም። የማይታየው እንጂ! ስለሆነም የትግራይ መንገዶች ይከፈቱ፤ ሰዎች በፈለጋቸው ጊዜ ወደ ፈለጉበት የመዘዋወር መብታቸው ይከበር። የወያኔ መሪዎችና በሴራው ተባባሪዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ያ ካልሆነ ነገሩ እንደገና አገርሽቶ ዳግም መፋለምንና መከራን ሊያመጣ ይችላል። በቃኝ!