
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጥያቄዎቿን እንዲቀበላት ጠየቀች
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እንደሚነገረው “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይሆኑ፣ የተሳሳቱ ርዕዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረና በተደራጀ ሥልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የማፅዳት እንቅስቃሴዎች መሆናቸውን ቤተ ክህነት ገለጸች።
የኦሮምኛ ቋንቋ ድምፃዊው ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ምክንያት በማድረግ በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች በስድስት ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ 25 ወረዳዎች በሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የገለጸችው ቤተ ክህነት፣ በጥቅምት ወርና በጥር ወር ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሃጫሉ ሞት ምክንያት በአቢያተ ክርስቲያናትና ምዕመናን ላይ የተፈጸመው ድርጊት ግልጽ እየሆነ መምጣቱንና በአጭር ጊዜ ሳይፈታ ቀርቶ በዚሁ ከቀጠለ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል አሳውቃለች።
በተለይ ከሰኔ 23 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያናትና ምዕመናኑ ላይ የደረሰው አሰቃቂና ግፍ የተሞላበት ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ንብረት ማውደም፣ ዝርፊያና ማፈናቀል እንደ ሌላው ጊዜ በቀላሉ ሊታለፍ እንደማይችል ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውይይት በማድረግ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በአካል ተገኝቶ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ዓብይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም መደረጉን ቤተ ክህነት በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች።
በርካታ አካላት ጉዳቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች ተጉዘው እንዳስተዋሉት ከሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ቀናት በተፈጸመ ጥቃት፤
- 67 ምዕመናን በግፍ ሲገደሉ፣
- በ38 ምዕመናን ላይ ከባድ
- በ29 ምዕመናን ላይ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል
- ከ7,000 (ሰባት ሺሕ) በላይ ምዕመናን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል
- እጅግ በርካቶች ለተለያዩ ሥነ ልቦናዊና ሥነ አዕምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል
- ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸው በዘረፋና በእሳት መውደሙንም ጠቁማለች።
በኦሮሚያና በሌሎችም ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች በቤተ እምነቶችና በምዕመናኑ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ የሚገኙ ሥልታዊ የሆኑ ግልጽ ተፅዕኖዎች በዓይነትና በመጠን እየጨመሩ መምጣታቸውን ቤተ ክህነት ጠቁማለች። አብዛኛዎቹ የክልሉ አመራሮች ለመወያየት ባሳዩት በጎ ፈቃድ ጥቃቱንና ተፅዕኖውን በተወሰነ ደረጃ ለመግታት ቢቻልም፣ በሰኔ ወር በተለይ በኦሮሚያ ላይ የተፈጸመው ከባድና አሳዛኝ መሆኑን ኮሚቴው ገልጿል።
ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ለክልሉ መንግሥት የመፍትሔ ጥያቄዎችን ቤተ ክርስቲያን ብታቀርብም፣ ጥያቄዋ ችላ መባሉንና ክልሉ አለመቀበሉ እንዳሳዘናት ቤተ ክህነት ገልጻለች። በክልሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያገደው ሕገወጥ ቡድን ለቤተ ክርስቲያን በሕግ የተሰጧትን መብቶች ከመጋፋት ጀምሮ የአስተዳደር መዋቅሯን እስከ ማፍረስ ድረስ የተዳፈረው፣ የክልሉ መንግሥት ለጥያቄዎቿ አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ መሆኑንም ቤተ ክህነት አስታውቃለች። የትናንቱን ችግር ለማከምና ነገ በከፋ መልኩ ሊመጣ የሚችለውን ለማስቀረት እንዲቻልና በጋራ ከመሥራት ውጪ መፍትሔ እንደሌለም በመጠቆም፣ የክልሉ መንግሥት ጥያቄዎቿን ተቀብሎ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንዲሆን ጠይቃለች።
የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና የሐሰት ትርክቶች በመንዛት ሆን ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሳቀቅና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስና በማቋቋም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ቤተ ክህነት ጠይቃለች።
መንግሥት “አጥፊዎችን አንታገስም፤ ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፤ የተጎዱትን እንክሳለን” ማለቱን ያስታወሰችው ቤተ ክህነት፣ መንግሥት የገባውን ቃል ይፈጽማል በማለት በትዕግሥት ብትጠብቅም በወቅቱና በብቃት ሲወጣ አለማየቷንም ጠቁማለች። በመሆኑም ከላይ የተገለጸውን ኮሚቴ በማቋቋም ጥቃቱ በደረሰባቸው አካባቢዎች በመላክ ምዕመናን የደረሰባቸውን ሁሉ መመልከት መቻሏንና ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማትም አስታውቃለች። አጥፊዎችን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋልና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ የፍትሕ ርትዕ እስከ መጨረሻው እንዲሰፍን የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ ያንን ተግብሮ ለማየት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም ተናግራለች። አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የግፉዓን ሰማዕታቱን መጠቃት አላግባብ ለቡድናዊና ፖለቲካ ትርፍ በመጠቀም ሐዘኗን መሳለቂያ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስባ፣ መንግሥት ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲያስታግስላትም አሳስባለች። (ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply