የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን “በዓሉ በአዲስ አበባ ሶስቱም ቦታ በሰላም ተከብሯል፣ በዓሉን እንዳያከብር የተከለከለ ሰውም የለም” ብሏል
127ኛው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ፣ አድዋ ድልድይ እና መስቀል አደባባይ በተለያዩ ስነስርአቶች ተከብሯል።
የድል በዓሉን በሚኒሊክ አደባባይ ለማክበር የወጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ግን” በዓሉን እንዳናከብር ተከልክለን ነበር፤ አስለቃሽ ጭስም ተተኩሶብናል” ብለዋል ከአል አይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
እታገኘሁ በየዓመቱ የካቲት 23 የአድዋ ድል በዓልን ሚኒሊክ አደባባይና አድዋ ድልድይ ታከብራለች።
ዘንድሮም በዓሉን ሁሌም እንደምታደርገው ጠዋት 3:00 መንገድ አቆራርጣ ሰሜን ሆቴል ከባለቤቷና ልጇ ጋር ደረሰች። ሆኖም ህዝባዊ በዓሉን ማክበር ከጀመረች ወዲህ ያልገጠማት ሁነት እንደተፈጠረ ገልጻለች።
እታገኘሁ የጸጥታ ኃይሎች መንገድ ዘግተው “ማለፍ አትችሉም” በማለት ግርግር መፈጠራቸውን ለአል ዐይን ተናግራለች።
“ከኋላችን አድማ በታኞች (ሄልሜትና መከላከያ የለበሱ) መጥተው አስለቃሽ ጭስ ሲተኩሱ ሁላችንም እግሬ አውጭኝ አልን” የምትለው እታገኘሁ፥ በዚህም ህዝቡ ራሱን ከአደጋ ለመጠበቅ መበተኑን ትገልጻለች።
በዓሉን ለማክበር ወደ ሚኒሊክ አደባባይ እየተጓዙ የነበሩ ሰዎች ማዋከብም እንደደረሰባቸውም ነው የአይን እማኟ የተናገረችው።
ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የመዲናዋ ነዋሪም ከጓደኞቹ ጋር ከፈረንሳይና ስድስት ኪሎ ተሰባስበው ወደ ሚኒሊክ አደባባይ በዓሉን ለማክበር ቢጓዝም “አትገቡም” እንደተባሉ ይናገራል።
“አትገቡም ብለው አስቆሙን፣ ሰው እየበዛ ሲመጣ ግን አስገቡን፤ የጸጥታ ሃይሎች ሃይል ከሰበሰቡ በኋላ ግን አስለቃሽ ጭስ ለቀዉብን፣ ትርምስ ሆነ፣ ህጻናትና ነፍሰጡሮች ጭምር ራሳቸውን ስተውነበር፣ በጭሱ ምክንያት የሚያስመልሳቸውን ሰዎችም አይቻለሁ” ይላል የአይን እማኙ።
በተፈጠረው ግፊያና ትርምስ በርካታ ሰው ተረጋግጦ መጎዳቱንም ነው ለአል አይን የተናገረው።
“ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞን አያውቀም፤ የጸጥታ ሃይሎች ሁለት ሶስት ሆነው የአጼ ሚኒሊክ እና ጣይቱን ቲሸርት እንዲሁም ባንዲራ (አረንጓዴ ቢጫ ቀይ) የበለሱ ሰዎችን እየመረጡ ሲመልሱ ነበር” ሲልም አክሏል።
ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች እና በዓሉን ለማክበር ወደ ጊዮርጊስ ለመምጣት የሞከረች ሌላኛዋ በዓል አክባሪም “ጣልያን ሀገራችንን በቅኝ ግዛት በወረረ ጊዜ እናቶቻችን ከሌሎች ማህበረሰብ ጋር ሆነው የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማሰብ በየዓመቱ በምኒልክ አደባባይ እየተገኘሁ አከብራለሁል፤ ዘንድሮ ግን ወደ ሚኒሊክ ሀውልት እንዳልቀርብ በጸጥታ ሀይል ተከልክያለሁ” ብላለች።
የመንግስት ኮሙንኬሽን ሚንስትር ዴኤታ አቶ አቶ ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው የዘንድሮው 127ኛው የአድዋ ድል በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበሩን ተናግረዋል።
አቶ ከበደ አክለውም በአዲስ አበባም በመስቀል አደባባይ፣ በአድዋ ድልድይ እና በሚኒሊክ አደባባይ በሰላም መከበሩን ጠቅሰዋል።
በምኒልክ አደባባይ በነበረው የበዓሉ አከባበር ወቅት ዜጎች ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ እንዳይገቡ በጸጥታ ሀይሎች መከልከላቸው ተነግሯል፤ ይህ ለምን ሆነ? በሚል ለአቶ ከበደ ላቀረብንላቸው ጥያቄ “በዓሉ በአዲስ አበባ ሶስቱም ቦታ በሰላም ተከብሯል፤ በዓሉን እንዳያከብር የተከለከለ ሰውም የለም” ሲሉ ለአል ዓይን ተናግረዋል።
ወደ ኋላ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ የሚከተለውን ብሏል፤
“127ኛው የአድዋ ድል በዓል ከወትሮው በላቀና ድሉን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት በቂ ዝግጅት አድርገዋል። የጸጥታ ተቋማትም የበዓሉን ድባብ የሚያውክ ነገር እንዳይፈጠር የቅድሚያ መረጃዎችን መሠረት አድርገው በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል።
“በበዓል አዘጋጆችና በጸጥታ አካላት ጥምረት በዓሉ በብሔራዊ ደረጃና በመላ ሀገሪቱ በታቀደለት ልክና ዓላማ ተከብሯል።
“ይሁን እንጂ ይሄንን መሰል ሀገራዊ ክንውኖች እንዳይሳኩ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን የጸጥታ አካላት አስቀድሞ መረጃ ነበራቸው። በመረጃው መሠረትም ተገቢውን ጥንቃቄ እና ጥበቃ አከናውነዋል። በተለይም በምኒልክ አደባባይ የሚደረገውን በዓል ለመረበሽ የፈለጉ አካላት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረው ነበር። እነዚህ አካላት የአደባባዩን በዓል መረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ ሞክረዋል።
“የጸጥታ አካላት ሑከት ፈጣሪዎችን ለማስታገሥ በሚያደርጉት ጥረት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ በዓል ሊስተጓጎልና ለሃይማኖታዊ በዓል የመጡ ምእመናን መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሆኖም የጸጥታ አካላት ባደረጉት ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የተሸረበዉን ሤራ ከሽፏል። መንግሥት ይሄንን መሰል ተግባር መፈጸም እንደሌለበት ያምናል። ሁኔታውንም አጣርቶ በችግር ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ ይወስዳል።
“በአጠቃላይ በዓሉ በታሰበው ደረጃና ልክ እንዲከበር ኃላፊነት ወስደው የሠሩትን ሁሉ መንግሥት ያመሰግናል። ከዘንድሮው አከባበር በተወሰዱ ትምህርቶችም ለወደፊቱ የተሻለ የበዓል አከባበር እንዲኖር መንግሥት ጥረት ያደርጋል።”
በዚህ መልኩ ነጻነት በሚከበርበት ቀን በሕዝብ ላይ የደረሰን እንግልት ምላሽ ሊሰጠውና አጥፊዎችም ተገቢው ቅጣት ሊቀበሉ ይገባል ሲሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
ከዚህ ሌላ በዓሉ በትግራይ ዓድዋ ከተማ ተከብሯል። በዕለቱ በአማርኛ ተጽፈው የታዩት መፈክሮች ት ህነግ በሚገዛት ትግራይ የማይታሰቡ እንደሆኑ የበዓሉን ዝግጅቶች የተከታተሉ ይናገራሉ።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply