“ከ69 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከመመሪያ ውጪ ከኢትዮጵያ ባንክ መባከኑ በሰነድ ተረጋገጠ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቀድሞ ፕሬዝደንት አቶ ባጫ ጊና የተፈረመበትን ሰነድ ዋቢ አድርጎ ባሰናዳው ወሬ በ2010 ከብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውጪ በትንሹ ከ69 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መሰጠቱን ሸገር 102.1 በመጥቀስ ዘግበን ነበር፡፡
በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር መመሪያው የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ ከተፈቀደላቸው የሥራ ዘርፎች ውጪ ላሉ ወይም መመሪያው ለማይመለከታቸው 5 ድርጅቶች በድምሩ 11 ሚሊዮን 841,583 የአሜሪካ ዶላር እንደተሰጠ ከተገኘው ሰነድ በመጥቀስ በዘገባው ተመልክቷል፡፡
በዚሁ ሰነድ ላይ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል 500,000 የአሜሪካ ዶላር እንደተፈቀደለት ተጽፏል፡፡
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ለሸገር በላከው ማስተባበያ የውጭ ምንዛሬው የተሰጠኝ ሕጋዊ ሂደትን ተከትሎ ነው በማለት በዘገባው ላይ ቅሬታውን በጽሑፍ አቅርቧል፡፡
በዚሁ ደብዳቤ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የነበረው ስያሜው ከመጋቢት ወር 2009 ጀምሮ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት አ.ማ. በሚል እንደተለወጠ የጠቀሰው ድርጅቱ በዘገባው ላይ ከባንኩ ተፈቀደለት ተብሎ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ትክክል አለመሆኑንም ጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተፈረመው ሰነድ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል 5መቶ ሺህ ዶላር ተፈቅዶለታል ቢልም፣ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት አ.ማ በወቅቱ የተሰጠኝ የውጭ ምንዛሬ 415 ሺህ 500 ዶላር ብቻ ነው ሲል ለሸገር ነግሯል፡፡
ይህን የውጭ ምንዛሬ ያገኘሁትም በ2010 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ለነበረው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ 190ሺህ ኮፍያ እና 180 ሺህ ባጅ ከነማንጠልጠያው ለማቅረብ ከስታትስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በደረስሁት ስምምነት መሠረት ነው ሲል በደብዳቤው ጠቅሷል፡፡ (@ ተህቦ ንጉሴ፤ ሸገር 102.1)
ዋልታ የሚዲያ ተቋም ከመሆኑ አኳያ ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮፍያ ማሳተሚያ በሚል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ካለባት አገር ግማሽ ሚሊዮን ዶላር መውሰዱ ትልቅ ጥያቄ የሚጭር ነው።
ከዚህ ሌላ በአሁኑ ጊዜ በየክፍለሃገሩ ምርቱን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ የኢንዱስትሪ ፓርት ተከፍቶ ባለበት ሁኔታ ይህንን ያህል የውጭ ምንዛሪ ለኮፍያና ለባጅ ማውጣቱ ዋልታ ከጅምሩ የህወሓት ልሳን የነበረ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply