የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያልተገባ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለተኛዋን የተመድ የኢትዮጵያ ኃላፊን ጠርቷል።
ተመድ የጠራቸው የድርጅቱ ሥነ ሕዝብ ጽ/ቤት (ዩኤንኤፍፒኤ) የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል መሆናቸውን ኤኤፍፒን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
ቀደም ሲል የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን አቻንግ “የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ” አስተያየት በመስጠታቸው ምክንያት አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን ተቋሙ ገልጾ ነበር።
መንግሥታቱ ድርጅት የሥነ ሕዝብ እና የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊዎች ለትግራይ ኃይሎች ርኅራኄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገናል ማለታቸው ተዘግቧል።
ሁለቱ በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ ኃላፊዎች የፌዴራሉ መንግሥት በትግራይ ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ በተመለከተ በርካታ መጣጥፎችን ለሚፅፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።
በቃለ መጠይቁ ላይ እንደሚሰማው የአይኦኤም ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ብለዋል።
ህወሓትንም “ቆሻሻ” እና “ጨካኝ” በማለትም ሲናገሩም ይሰማል።
በአንድ ወቅትም ህወሓት ከሳዑዲ ዓረቢያ የተባረሩ የትግራይ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ እንዲላኩ አሲረዋል በማለትም ሲከሱ ይሰማል።
የሥነ ሕዝብ ጽ/ቤት ኃላፊዋ ጌይል ደግሞ ኢትዮጵያ የገቡ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች አዲስ አበባ የሚገኙ ከፍተኛ የተመድ ኃላፊዎችን በማለፍ በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ ይላሉ።
ይህም የሚያመለክተው “በተመድ ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ” ስለመኖሩ ሲሉ ጌይል ይሰማሉ።
በኢትዮጵያ የድርጅቱ የሥነ ሕዝብ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል እና የስደተኖች ጉዳይ ድርጅት ኃላፊዋ ወደ ኒው ዮርክ መጠራታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚደረገውን ሥራ የበለጠ እንደሚያውከው ተጠቅሷል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Miherete Tibebe says
አመሰራቱ ለአለም ሰላምና እድገት የሆነው ተመድ አሁን ወዙ ተቀይሮበት አወዛጋቢ ችግሮች ውስጥ መግባቱ ይሆን! በተለይ ገና በዳዴ ባሉ ሀገራት ላይ አይኑ የሚቀላው ለምንድን ነው! ምናልባት ከጀርባው ተቀምጠው እጁን የሚጠመዝዙት ሳይበዛ ዘአልቀርም ማለት ይቻላል! ለዚህ ነው ጥቁር፣ ጉበዝና እውነተኛ አመራሮቹን ማዋከብ የገባው!