
በሰላም ንግግሩ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ተዓማኒ የሆነና ግልጽነት ያለው የሽግግር ፍትሕ የሚፈፀም መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።
በሰላም ስምምነቱ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ተዓማኒ የሆነና ግልጽነት ያለው የሽግግር ፍትሕ ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚፈፀም መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶክተር) ገልፀዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሠረት ግልፅ እና ተዓማኒ የሆነ የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን እንደሚሠራ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ከያዝነው ወር ጀምሮ ሰፊ የሆኑ ሥራዎች ሁሉንም አካላት ባሳተፈ መልኩ እንደሚሠራ ነው የገለጹት።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃሳባቸው በሚሰማበት እና ወደ ሽግግር ፍትሕ ለሚደረገው ሂደት የበኩላቸውን ተሳትፎ በሚያደርጉበት ሁኔታ በሚያረጋግጥ መልኩ ተዓማኒነት ያለውና ሁሉን አቀፍ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ይሠራል ብለዋል።
በአጠቃላይ በደህንነት ዙሪያ የተካሄዱ ስብሰባዎችን በማጠናከር ማጠናቀቅ እንደተቻለ በማንሳትም፤ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያሉትን አከራካሪ ነገሮች በስምምነቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ግልፅ በሆነ መንገድ አጥብቀው እንደሚያትቱት በኢፌዴሪ ሕግ መንግሥት በሚያዘው መልኩ የሚፈፀም መሆኑን ጠቁመዋል።
የፕሪቶሪያውም ሆነ የናይሮቢው ስምምነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ጌዲዮን፤ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮች እና ወታደራዊ አዛዦች በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ላይ ያተኮሩ ስብሰባዎች አካሂደው በስኬት መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል በምትገኘው የሽሬ ከተማ በሁለቱም ወገን ባሉ ወታደራዊና የደህንነት አመራሮች መካከል ቀጥሎ የተካሄደው የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ላይ ያተኮረ ስብሰባ በስኬት መጠናቀቁን በማስረዳት፤ በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተደረጉት ስምምነቶች በቅርቡም በሽሬ የተካሄዱ ውይይቶች በስኬት በመጠናቀቃቸው ለተጨማሪ ሥራ የሚያነሳሱና ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ወዳጆችና አጋር ሀገራት የሰላም ስምምነቱን በመደገፍ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያስታወሱት የፍትሕ ሚኒስትሩ፤ በውይይቱ ሁለቱም ወገኖች እንዲገፉና ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጉዳዩን ከእልባት ላይ ለማድረስ እንዲሁም እርቅ እና መረጋጋት እንዲመጣ የሀገራት ሚና አስተዋፅዖ እንደነበረው አንስተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ በሰላም ስምምነቱ ላይ ያለው ቁርጠኝነት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳትም በፓርቲው ይህን መሰል ቁርጠኝነት እና ግንዛቤ እስካለ ድረስ ምንም እንኳን እንቅፋቶች እና ተግዳሮቶች ሊኖሩ ቢችሉም በስኬት ማጠናቀቅ እንችላለን ሲሉ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የፖለቲካ ችግሮች ላይ እልባት ለመስጠት ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ጌዲዮን፣ በአካታች ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ምክክር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ አስፈላጊ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። (አዲስ ዘመን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply