በጋምቤላ ከተማ በአሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ተላላኪነት የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦችን ከጦር መሳሪያና ሌሎች ቁሳቀሶች ጋር በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቱት ኮር ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ሁለቱ የቀድሞውን የሀገር መከላከያ የደንብ ልብስና ጫማ እንዲሁም የሕክምናና ሌሎች ቁሳቁስ ይዘው ከጋምቤላ ከተማ ወደ ጫካ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ነው።
ቀሪው ተጠርጣሪ ደግሞ ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ በቤቱ በተደረገ ፍተሻ አንድ ዘመናዊ የጦር ሜዳ መነጽርና አንድ ሽጉጥ ተገኝቶበት እንደሆነ አመልክተዋል።
ተጠርጣሪው ካሁን በፊትም ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳለው ተጠርጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ እየተደረገ ያለው ተጨማሪ ምርመራ ሲጠናቀቅ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት እንደሚላክ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክልሉ ጠረፋማ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የህወሃትና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ተላላኪዎች ሰርገው እንዳይገቡ የክልሉና የፌዴራል የጸጥታ አካላት የቁጥጥር ስራ እያካሄዱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና የአሸባሪ ቡድኖች ተላላኪዎችን አጋልጦ በመስጠት ረገድ የጀመረውን ተሳተፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በክልሉ ከሶስት ቀን በፊት በተደረገው ክትትል የጸጥታ ስጋት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ 93 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በሱዳን በኩል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመግባት በክልሉ ሽብር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ170 በላይ ጸረ ሰላም ኃይሎች ተደመሰሱ።
በሱዳን በኩል ሾልከው ወደ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አልመሃል አካባቢ በመግባት ሽብር ለመፍጠር እና በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረሰ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ ጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ ከ170 በላይ የሚሆኑት መደምሰሳቸውን የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ በሰጡት መግለጫ፣ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በክልሉ እና ከክልሉ ወጪ ከሚንቀሳቀሱ ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመፍጠር ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፣ በእነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ መወሰድ መጀመሩን ተናግረዋል።
በዚህም መከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ አካላት እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙት የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት ጋር በመቀናጀት እስከትናንት በተወሰደው የህግ የማስከበር እርምጃ ከ170 በላይ የሚሆኑ ጸረ ሰላም ኃይሎች ተደምስሰዋል ብለዋል።
የተደመሰሱት ጸረ ሰላም ኃይሎች በሱዳን ድንበር በኩል በመግባት በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው ጉባ ወረዳ አልመሃል ቀበሌን እንደ ማዕከል ተጠቅመው ወደ ግድቡ የሚወስደውን መስመር በመቁረጥና እንቅስቃሴን በማወክ ሥራውን ለማስተጓጎል ዓላማ የነበራቸው መሆኑን አቶ አብዮት ገልጸዋል። (ኢቢሲ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply