በአዳማ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የሸኔና የህወሃት ተላላኪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ::
ሐሙስ መስከረም 19 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዳማ ከተማ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ 82 የሸኔና አሸባሪው ህወሃት ተላላኪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የከተማዋ ፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
የአዳማ ከተማ ፀጥታና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሀላፊ መኩሪያ ድንቁ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ሸኔና የህወሃት ተላላኪዎች በከተማዋ መስቀልና ኢሬቻን ጨምሮ ህዝባዊ በዓላትን ለማወክ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።
በዚህም 33 የሸኔና አባ ቶርቤ አባላት እንዲሁም 49 የህወሃት ሴሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።
በመጪው ቅዳሜና እሁድ በሆራ ፊንፊኔና ቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ መስተዳደሩ ከምስራቅ ሸዋ ዞንና አጎራባች ከተሞች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የተቀናጀ የፀጥታ አካላት ስምሪት በመስጠት የፀጥታ ሃይላትን በአንድ ላይ በከተማዋ በአራቱም መግቢያና መውጫ ቦታዎች ላይ በቅንጅት የፍተሻ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ የኢሬቻ በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍተሻ ሥራው ሙያዊ እንዲሆን የፌዴራልና የኦሮሚያ ልዩ ሃይልን ጨምሮ መደበኛ ፖሊሶችን በማሰማራት ውጤታማ ሆነናል ብለዋል።
በዚህም 19 ሽጉጦች፣ 6 ክላሽና ከ3ሺህ በላይ የተለያዩ ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን አመልክተዋል።
እንግዶች አዳማ ከተማ አርፈው ወደ አዲስ አበባና ቢሾፍቱ የሚሄዱ በመሆኑ የፀጥታ ስራውን ከምስራቅ ሸዋ ጋር ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሰርጎ ገቦችን የመከታተል እና የፍተሻ ስራዎችን በጋራ በመስራታችን ውጤታማ ሆነናል ብለዋል።
በከተማ ደረጃ ያለውን የፀጥታ ምክር ቤት እስከ ቀበሌ ድረስ በማጠናከር በየሳምንቱም ግምገማ እያከናወኑ መሆኑም ጠቅሰዋል።
አባ ቶርቤ ተብሎ ወደ ከተማዋ የገባውና በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ከኢትዮጵያ ውጭ በአሸባሪው ሸኔ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር የመጣ መሆኑን ሀላፊው ጠቅሰው በአዳማም ሆነ በዙሪያዋ የሰርጎገቦችን እንቅስቃሴ ለማምከን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል። (አዲስ ማለዳ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply