
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው 98 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ የክልሉ ፖሊስ የተጠናከር የክትትል ስራ ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ወጥቶ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የክልሉን ሠላም ለማስጠበቅ ለፀጥታ አስከባሪ ኃይሉ ተጨማሪ አቅም ሆኖታል።
ግለሰቦቹ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደነበራቸው ፖሊስ በደረሰው መረጃ መሰረት ከጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባደረገው ኦፕሬሽን ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት በሀሰት ወሬ ሀገርን ለማሸበር ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችም አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመውን ጥቃት ለመድገም በድብቅ ሲዘጋጁ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ግለሰቦቹ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ይዘው በነዋሪው ላይ ሽብር ለመንዛት የሚያስችል የፈጠራ ወሬዎችን የያዙ ቪዲዮዎችን ሲያዘጋጁ ተደርሶባቸዋል፡፡
ፖሊስ ይህን ተጨባጭ ማስረጃ መሠረት በማድረግ ግለሰቦቹን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply