* በሶስት ወራት ብቻ ከ6,600 በላይ ወጣቶች በህገ-ወጥ መንገድ ተሰድዋል” – የትግራይ የወጣቶች ጉዳይ ቢሮ
በትግራይ ክልል ከተሞች በሚገኙ አውራ መንገዶች “ልጄ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ስደት ሲሄድ በአጋቾች ተይዞ ይህንን ብር ክፈል፣ ካልከፈልክ ትገደላለህ ብለውኛል እርዱኝ” የሚሉ በትልቅ ባነር በተቀመጠ የወጣቶች ፎቶ አስደግፈው እርዳታ የሚለሙኑ ወላጆች ተበራክተዋል።
ከነዚሁ ወላጆች የአክሱም ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ኣስካለ ውብኣንተ አንድዋ ሲሆኑ፤ ይጦረኛል ብለው ኮስኩሰው አስተምረው ያሳደጉት ወንድ ልጃቸው ህገ-ወጥ ስደት የነጠቃቸው እናት ናቸው።
“ልጄ በጦርነቱ ማግስት በአከባቢው የስራ እድል በማጣቱ በህገ-ወጥ መንገድ የተለያዩ ሃገራት ደንበር አቋርጦ ሊብያ ሲደርስ ለሰው ህይወት ቁብ በሌላቸው ሽፍቶ እጅ ወድቆ ቁም ስቅሉን እያሳዩት ነው” ብለዋል።
“አካል ጉዳተኛ ነኝ፤ ልጄ እኔ እናቱን ለመጦር ዳቦ መጋገሪያ ቤት ከፍቶ የነበረ ቢሆንም ንብረቱ መዘረፉ አናድዶት ነው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ስደት የሄደው” ወ/ሲሉ እኚሁ እናት እንባ እተናነቃቸው ተናግረዋል።
“ልጄ በአጋቾች ቁጥጥር ስር ውሎ ጥዋት እና ማታ በሚደርስበት ገርፋት እየተሰቃየ ሲያናገርኝ የምይዘው የምጨብጠው ይጠፋብኛል ፤ ‘የጠየቁኝ ብር ካልተከፈለ ኩላሊቴ ያወጡታል ምን ማድረግ ነው ያለብኝ?’ ካለኝ ቀንና ሰዓት ጀምሮ አእምሮየ ልክ አይደለም” ብለዋል።
“ልጄ በመጀመሪያው አከባቢ በሙሉ ጤንነት እያለ 1.5 ሚሊዮን ብር እንድከፍል ጠየቁኝ ደጋግመው ደብድበው አካል ጉዳተኛ እና በሽተኛ ካደረጉት በኋላ ግን 300 ሺህ ቀንሰው 1.2 ሚሊዮን ብር ጠይቀውኛል። ይህንን ገቢ ካላደረግኩ ድግሞ እንገድለዋለን ብለውኛል እባካችሁ አርዱኝ” ሲሉ ተማፅነዋል።
ወ/ሮ አስካለ ልጆቻቸው የህገ-ወጥ ስደት ገፋት ቀማሽ ሆኖውባቸው ሌት ተቀን ከሚያለቅሱ በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ እናቶች አንድዋ ናቸው።
እሳቸው ለሚድያ ቃላቸው በሰጡባት ቀን ሰዓትና ደቂቃ ሳይቀር በተለያዩ አቅጣጫዎች በርካታ ወጣቶች በአከባቢያቸው ተስፋ ሰጪ ሁኔታ በማጣት እግራቸው ወደ መራቸው ይሰደዳሉ።
የትግራይ የወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ሓይሽ ስባጋድስ፣ የህገ-ወጥ ስደቱ ዋና መነሻ የሰራ እና መልካም አስተዳደር እጦት መሆኑ ገልጸዋል።
ወጣቶች በነዚህና ሌሎች ችግሮች ተማረው አደገኛ የሆነውን ስደት በመምረጥ ለተለያዩ አደገኛ ነገሮች እየተጋለጡ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቢሮቸው የተካሄደው ዳሰሳ እንደሚያመለክተው ከሓምለ 2016 አስከ መስከረም 2017 ዓ.ም ባሉት ሦስት ወራት ብቻ በክልሉ ማእከላዊ ፣ ምስራቅ እና ሰሜናዊ ምዕራብ ከሚገኙ 11 ወረዳዎች ከ6,600 በላይ ወጣቶች በህገ-ወጥ መንገድ ተሰደዋል ሲሉ ገልጸዋል።
“የትግራይ የፓለቲካ አመራሮች ከገቡበት የስልጣን መቆራቆስ በመውጣት በህገ-ወጥ ስደት ለከፍተኛ አደጋ እና እልቀቂት የተጋለጠውን የወጣቱን ክፍል ለመታደግ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው” ብለዋል።
የመረጃው ምንጭ ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ እና ትግራይ ቴሌቪዥን የህዳር 17/2017 ዓ/ም የዜና ዘገባ ናቸው።@tikvahethiopia
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply