
[ጁን 8፤ 2010] ዋኤል ጎኒም (ዕድሜ 28) እንደወትሮው ዜናዎችን ለመቃረም፣ ከዘመድና ወዳጅ ጋር ለመወያየት ዱባይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተቀምጦ በፌስቡክ መስኮት ወደ ትውልድ ሀገሩ ግብጽ ዘለቀ፤ በዚያን ዕለት ያነበበው ዜና እና የተመለከተው ፎቶ ስሜቱን አወከው፣ እረፍት ነሳው፣ ዜናው አሌክሳንድሪያ ውስጥ በሙባረክ የጸጥታ ሀይሎች በግፍ ስለተገደለው ካሊድ ሰይድ (ዕድሜ 28) ነበር፡፡ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የነበረው የካሊድ አስከሬን በዐይን ለማየት ይከብዳል፡፡
“በዛ አሰቃቂ የካሊድ ፎቶ ውስጥ ራሴን አየሁት፣ በካሊድ ቦታ እኔም ልሆን እችል ነበር ብዬ አሰብኩ” ይላል ዋኤል በዚያች ቅጽፈት የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ፣ ከቁጭትና ንዴት ባለፈ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት አሰበ፤ ጊዜ ሳያጠፋ ማንነቱን ደብቆ “We are all Khaled Said/ሁላችንም ካሊድ ሰይድ ነን” የሚል የፌስቡክ ገጽ ከፈተ፡፡
ገጹ በተከፈተ ሁለት ሰዓት ውስጥ 300 ሰዎች ተቀላቀሉት፣ ከሁለት ወር በኋላ የአባላቱ ብዛት ወደ 250,000 ሲያድግ አብዮቱ ዋዜማ ላይ የአባላቱ ብዛት 3 ሚሊየን ደርሶ ነበር፡፡ ገጹ ከአረቡ አለም ብዙ ተከታይ ያለው ገጽ ሆኖ ተመዘገበ፤ የአባላቱ ቁጥር ከፍ እያለ ሲመጣ ዋኤል ሙሉ ሰዓቱን ሰጥቶ አብዮቱን በከፍተኛ ኃላፊነት ይከካውና ያቦካው ገባ፣ ሀሳብ ያለው ይሳተፋል፣ ቀሪው አስተያየት ይሰጣል፣ የሰማው ላልሰማው ያጋራል፣ “ፌስቡክ ላይ ለሆነው ሁሉ ስሙን ጠርተን ጀግና ነህ የምንለው ሰው የለንም፣ ሁሉም ጀግና ነውና” ይላል ዋኤል፡፡ የሁሉንም አስተዋጽዖ ዋጋ እንደነበረው ሲገልጽ፣ “የግብጽ አብዮት የተጻፈው ልክ እንደ ዊኪፒዲያ ነው፣ ሁሉም አዋጥቷል፣ ያዋጣው ሰው ስም ግን አይታወቅም፣ አይጠቀስም” ነው የሚለው፡፡
የግብጽ አብዮት ፌስቡክ ላይ እየጋመ ባለበት ወቅት ቱኒዚያ የተነሳው ህዝባዊ ማዕበል በ28 ቀን ውስጥ የቤን አሊን መንግስት ጠራርጎ ወሰደው፡፡ ከተፎው ዋኤል “ቱኒዚያ ውስጥ የሆነው ግብጽ ውስጥ የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?” የሚል ወሳኝ ጥያቄ ይዞ ብቅ አለ፡፡ የህዝቡ ምላሽ አዎንታዊ ሆነ፣ “እናድርገው! የፈራ ይመለስ!” ባይ ሆነ፡፡ ዋኤል ጊዜ ሳያጠፍ የሰልፍ አስተባባሪዎችን በሚስጥር እየተገናኘና ሰልፍ የሚከናወንበትን መንገድ ይገልጽ ገባ፤ ጃንዋሪ 25፣ 2011 የጣሂር አደባባይ በወጣቶች ተጥለቀለቀ፣ የሙባረክ ምጥ “ሀ” ብሎ ጀመረ፡፡
ፌስቡክ ላይ የተጸነሰው አብዮት ሽሉ እየገፋ ሲመጣ ለግል ጉዳይ ወደ ሀገሩ መመለስ እንዳለበት አለቆቹን አሳምኖ አብዮቱን ሊያዋልድ ዋኤል ካይሮ ገባ፡፡
ጃንዋሪ 27 ዋኤል የተሳተፈበት ሀገር አቀፍ ሰልፍ ተደረገ፤ ውጥረት የበዛበት የሙባረክ መንግሥት አራት የሚሆኑ የኢንተርኔት ማስተላለፉያ መስመሮችን ዘጋ፤ በዚያኑ ቀን የጸጥታ ኃይሎች ዋኤልን አፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ ወሰዱት፤ የልጁ መታፈን ወጣቶቹን አስቆጣ፤ መሰወሩን የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተቀባበሉት፣ ጉግል መግለጫ አወጣ፤ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተንጫጩ፣ አላየሁም ዐይኔን ግንባር ያድርገው ሲል የነበረው የሙባረክ መንግሥት ጫና ሲበዛበት (ከ11 ቀን በኋላ) ይኸውላችሁ ብሎ ለቤተሰቡ አስረከበው፡፡
የዋኤል ከእስር የወጣው ሃሞቱን እምርሮ ነበር፡፡ ከእስር በወጣበት ቀን Dream TV ጋር ባደረገው ቆይታ የሙባረክን መንግስት “ቆሻሻ ነው፣ ቆሻሻ ደግሞ ተጠርጎ መጣል አለበት” ሲል ቆምጨጭ ያለ አስተያቱን ሰጠ፡፡ አስከትሎም በዚህ ትግል ውስጥ መሞት ለሱ ክብር እንደሆነ በመግለጽ ከትግሉ ወደ ኋላ እንደማይል አስረግጦ ተናገረ፡፡
የሙባረክ መንግሥት ስንብት እርግጥ እየሆነ ሲመጣ (ፌብሩዋሪ 9) እስከ ዛሬ የምትጠቀስለት አንድ ወሳኝ መልዕክት ጣሂር አደባባይ ለተሰበሰቡት አብዮተኞች አስተላለፈ፤
“This is not the time for individuals, or parties, or movements. It’s a time for all of us to say just one thing: Egypt above all”
“ይህ የግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም የንቅናቄዎች ጊዜ አይደለም፣ ይህ ሁላችንም በአንድ ልብ “ግብፅ ትቅደም” የምንልበት ወቅት ነው”፡፡
ይህን ንግግር ባደረገ ሁለተኛው ቀን የሙባረክ መንግሥት ሥልጣን ለቅቆ ወታደራዊው ምክር ቤት ሀገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ፡፡ አንድ ላይ የሚያጨበጭበው፣ በአንድ ላይ የሚጮህው፣ አምባገነኑን ስርዓት ያራደው ማኅበራዊው ሚዲያ በለውጡ ማግስት መሰንጠቅ ጀመረ፣ ቆየት ብሎ ተተረተረ፡፡
ይህ ዋኤል የጠበቀውና የተዘጋጀበት ጉዳይ አልነበረም፣ “ህዝብን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ የሚያስፈልግህ ኢንተርኔት ነው የምል ሰው ነበርኩ፣ ተሳስቼ ነበር / I once said If you want to liberate a society all you need is the internet, I was wrong” ይላል ወቅቱን ሲያስታውስ፡፡
ከሙባረክ ፈርጣማ ክንድ ያላቀቃት ማኅበራዊ ሚዲያ ግብጽን ሊያጠፋት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ስድስት ነገሮች ናቸው የሆኑት ይላል የአብዮቱ ወላጅ አባት ዋኤል ጎኒም፣
[1] በወታደራዊው ኃይል ደጋፊዎችና ኢስላሚስት መካከል ዋልታ ረገጥነት (ጽንፈኝነት) (polarization) ሥር ሰደደ
[2] ሀሜትና የውሸት/የተሳሳተ መረጃ (rumours and misinformation) ነገሰ
[3] ፌስቡከኛው የራሱን ድምጽ የሚያስተጋባለት ጎጆ (echo chamber) ፈጠረ፣ የተለየ ሀሳብ ያለው ሰው በብሎክ ያሰናብተው፣ ባለመከተል (unfollow) ይርቀው ጀመር
[4] ውይይትና ክርክር ወደ ስድብና ዘለፋ ተለወጡ
[5] አዲስ ማስረጃ በቀረበለት ጉዳይ ላይ ጭምር ሀሳብ መቀየር፣ አቋምን መከለስ ከባድ ሆነ፣ ግትርነት ጌጥ ሆነ
[6] ሁሉም ተንታኝ፣ ሁሉም ጸሐፊ፣ ሁሉም ተናጋሪ ሆነ፣ የሚሰማና የሚያነብ ጠፋ፡፡
ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ስርዐት አልበኛ የሆነው ማኅበራዊ ሚዲያ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የተረከበውን መሐመድ ሙርሲን ጁላይ 3፣ 2013 ከወንበሩ ከነበለው፣ “የዚያን ዕለት ተስፋ ቆርጬ ከማኅበራዊ ሚዲያው ራሴን አገለልኩ” ይላል ዋኤል፣ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትቶ፣ ጨርቁን ከጣለው ማኅበራዊ ሚዲያ ራሱን አግልሎ ከሥር የምገልጻቸውን ከወነ፤
[የግብጽ ማህበራዊ ሚዲያ አደብ እንዲገዛ የሆነበትን ሂደት ወደ ፊት አቀርበዋለሁ]
ነገረ ዋኤል
ዋኤል ከዕድሜው በላይ ያነበበ፣ ከሁለት ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች ሁለት ዲግሪዎች በከፍተኛ ማዕረግ የወሰደ ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣት ነው፡፡ የመጀመሪያው ዲግሪ በኮምፒውተር ሳይንስ መሆኑና ጉግል ውስጥ መሥራቱ ማኅበራዊ ሚዲያውን በስፋትና በተገቢው መንገድ እንዲጠቀምበት ሳይረዳው አልቀረም፡፡
ዋኤል በግብጽ አብዮት ከነበረው ተጽዕኖ አንጻር የፕሬዚዳንትነት ወንበር ቢያጣ ጠቅላይነቱን የሚከለክለው አልነበረም፡፡ ልጁ ቀልቡን የገዛ፣ በጭብጨባ ያልሰከረ፣ ሰክኖ የተወለደ ሆኖ ኑሮ ይህን ጥያቄ ሲቀርብለት እኔ ለፖለቲካ አልተፈጠርኩም፣ ሥልጣንም አልፈልግም፤ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ሳላደርግ ሀገሬን በምችለው ሁሉ እረዳለው እያለ መልስ ይሰጥ ነበር፡፡ አብዮቱን በከፍተኛ ኃላፊነት ከመምራቱ በበለጠ ከአብዮቱ በኋላ ባሳየው ስክነትና አርቆ አሳቢነት ዓለም አደነቀው፡፡
በ2011 ለሰላም ኖቤል ሽልማት እጩ ሁኖ ቀረበ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ የዓለማችን 100 ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎች መዝገብ ላይ ስሙን ከተበለት፣ “Arabian Business” የሚሰኝ ደረጃ አውጪ “የ2013 ተጽኖ ፈጣሪ አረብ” ብዬ ሰይሜሀለው ብሎታል፣ የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም የ2012 “Young Global leader” አለው፣ በጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ የሚሰጠው “Profile in Courage Award” ይገባሀል ተባለ (ሽልማቱን የወሰደው የJFK ሴት ልጅ እጅ ነው)፣ ሀርቫርድ ዮኒቨርስቲ ደረቱን በሜዳሊያ ካሸበረቀለት በኋላ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ (senior fellow) አድርጌ ሹሜሀለው አለው፣ TEDTalks ተናጋሪ ነው፣ በትልልቅ ዩኒቨርስቲዋች እየተጋበዘ “ቃል አውጣ” የሚባል ሰው ሆነ፡፡

ዋኤል በበኩሉ “Revolution 2.0: The power of people is greater than the people in power ” በሚል ርዕስ አብዮቱን የሚያትት መጽሐፍ አሳተመ፣ ከመጽሐፍ ሽያጭ የተገኘውን 2.5 ሚሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጎት ድርጅት ለገሰ፣ “Tahrir Academy” የሚሰኝ ማሰልጠኛ ከፍቶ ጥልቅ አሳቢዎችን የወደፊት መሪዎችን እያሰለጠነ ነው፡፡
ነገረ ጃዋር
ጃዋር መሐመድ የዋኤልን መንገድ ይከተል እንደነበር ብዙ ማሳያዎች አሉ፣ ህልሙና ግቡ ዋኤልን መሆን ነበር፡፡
በእርግጥ የጸረ ወያኔ ትግል በተፈለገው መንገድ ቢጻፍ ጃዋር መሐመድን ሳይጠቅስ አያልፍም፣ የልጁን አስተዋጽዖ ማኮስመን ትዝብት ላይ ይጥላል እንጂ ሀቁን አይቀይረውም፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ግንድ ነው ብዬ ስለማስብ ጃዋር ለኢትዮጵያ አልታገለም ለማለት እቸገራለሁ፡፡

ጃዋር የገዛ ራሱን ቁርጭምጭሚት በጥይት የነደለው ከድህረ ወያኔ በኋላ ነው፡፡ ራሱን መግዛት አቃተው፣ ጭብጨባ አሰከረው፣ በዋኤል ልሳን “ፖለቲካ የኔ አይደለም፣ ሀገሪቷ እንድትረጋጋ የበኩሌን ካበረከትኩ በኋላ ማስተማር ነው የምፈልገው፣ የኔ ስራ የወደፊት መሪዎችን ማብቃት ነው” ሲል ቆየ፡፡ ብዙም ሳይቆይ “ኦፌኮ” ነኝ ብሎ መጣ፤ የዚያን ቀን ጃዋር መሐመድ የግብጹን ዋኤል ጎኒምን እንደማይሆን ተረጋገጠ፡፡
ጃዋር መሐመድ የዋኤልን መንገድ ተከትሎ ቢሆን ኑሮ ዛሬ ሀውልት አፍርሱ የሚለው ጃዋር ጎንደር ውስጥ ሀውልት በተጠረበለት ነበር፤ ከዋኤል ያላነሰ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና አያጣም ነበር፣ ነበር ባይሰበር፡፡
መውጫ
ጃዋር መሐመድ የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆኑ ትልቅ ስህተት እንደሆነ የገባው ይመስለኛል፡፡ እንደ እግር እሳት እንደሚያቃጥለው አልጠራጠርም፡፡ የድርጅት አባል መሆኑ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ተጽኖ ቀነሰበት እንጂ አልጨመረለትም፡፡ አንድ የኦፌኮ አባል የኦነግ ወይም የብልጽግና (ኦሮሞ ክንፍ) ደጋፊና አባል ላይ በቀላሉ ተጽዕኖ መፍጠር ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ፖለቲካውም የተሳካለት አይመስልም፤ ጃዋር ከሁለት ያጣ ቁማርተኛ ነው፤ የቆሰለ አውሬ ነው፣ ተስፋ የቆረጠ ፍጡር ነው፡፡ የቆሰለ አውሬ፣ ተስፋ የቆረጠ ፍጡር ደግሞ ሰማይ ቢከነበል፣ ምድር ብትጠቀለል ደንታው አይደለም፣ እንጠንቀቀው!
[ካሳ አንበሳው] ጸሃፊው የሰጡት ርዕስ ጃዋርና ዋኤል የሚል ነው
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply