ጀግኖቹ በስሌት እና በቀመር የሚተኩሱት ተተኳሽ ዶግ አመድ የሚያደርገው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ክምር መረማመጃ ያሳጣል፡፡ በተረበሸው የጠላት ምሽግ ዙሪያ እንደ ዘንዶ የተጠመጠሙት የእናት ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ድልን ለማጣጣም መጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል፡፡ ሴት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትም ከወንድሞቻቸው ጋር ጠላት የገባበት ጉድጓድ ገብተው ወደ ቋመጠው ሞት በመሸኘት ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ እንደምትኖር እያሳዩት ነው፡፡
ፈርጣማ ወታደራዊ ተክለ ቁመና እና የገዘፈ ኢትዮጵያዊ ልብ የታደሉት እነዚህ እንስቶች የሚሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ይፈጽማሉ፤ ቆፍጣና አዋጊዎችም ናቸው፡፡ አልመው አይስቱም፤ ሽብርተኛው ትህነግ የትኛውንም ያህል ብዛት እና ብቃት አለው ብሎ የሚያሰማራውን ወራሪ ቡድን በኮንክሪት ጭምር ተጨንቆ የገነባው ምሽግ ድረስ ዘለው ገብተው ዶግ አመድ ማድረግን ተክነውበታል፡፡ ያኔ ገና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ሲቀላቀሉ ከሠንደቅ ዓላማው ጋር የተረከቡትን የሀገር ሕልውናን የማስከበር ኀላፊነት እንስቶቹ የጦር ሜዳ ፈርጦች በጀብድ እየተወጡት ነው፡፡
ከሰሞኑ በነበሩ አውደ ውጊያዎች ላይ አስደናቂ ጀብዱ ከፈፀሙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል አራት እንስት አናብስቶችን ለአብነት በግንባር ተገኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡
፲ አለቃ ደርቤ አበራ ትባላለች፤ ወታደርነትን እንደነፍሷ የምትወደው ሙያ እንደሆነ ነው የነገረችን፡፡
ኢትዮጵያን ከድቶ፣ አዋርዶ እና “እበታትናታለሁ” ብሎ በአደባባይ አውጆ ጦር ሰብቆ የተነሳውን የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ትእቢት ለማስተንፈስ እና ለመቅበር ምንግዜም ዝግጁ የሆኑት ፲ አለቃ ደርቤ እና ጓዶቿ የጠላትን ምሽግ እንዲሰብሩ ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡
ቡድኑን የመምራት ኀላፊነቱን የተቀበለችው ፲ አለቃ ደርቤ ጓደኞቿ ትክክለኛ ቦታቸውን መያዛቸውን አረጋገጠች፡፡ ከዛም ወደ ሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ምሽግ ዱብዳ ሆነው የደረሱት እነ ፲ አለቃ ደርቤ ለወራት የገነባውን እና ሲመካበት የነበረውን ምሽግ በደቂቃዎች እንዳልነበር አደረጉት፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በቆፈረው ምሽግ ላይ እስከ ወዲያኛው ተሸኘ፡፡ ሽብርተኛው ትህነግ እንደሚነዛው የሐሰት ወሬ በጦር ሜዳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ፊት መቆም ቀላል አልሆነለትም፡፡ ፲ አለቃ ደርቤ እና ጓዶቿም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እና ጀግንነት ፈጸሙ፡፡ ይህ የአናብስቶቹ የዕለት ተዕለት የጀብድ ውሎ ነው፡፡ ፲ አለቃ ደርቤ ዛሬ ጓዶቿ የሚኮሩባት የጦር መሪ ናት፡፡ ነገ ደግሞ ዛሬ አርአያ እንደምታደርጋቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ደርሳ የማየት ሕልም አላት፡፡
ወታደራዊ የደንብ ልብሷ ከሰውነቷ ጋር ተዋህዷል፤ ተክለ ሰውነቷ ኢትዮጵያዊ ወታደርነቷን ይናገራል፤ ገራገር ደግሞ ጀግና ነች፤ መሰረታዊ ወታደር ሀዋ ሙሃመድ፡፡ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ ጥቁር ቀን የሚባለው እና ሽብርተኛው ትህነግ ክህደት የፈጸመበት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፊት መስከረም 5/2013 ዓ.ም ውትድርና ሙያን እንደተቀላቀለች ተናገራለች፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያሳለፈችውን ለአንድ ዓመት የዘለቀ የውትድርና ሕይወት ስትገልጸው “እንጀራ በመሶብ ቀርቦ የበላንበት ጊዜ የለም” ብላለች፡፡
መሰረታዊ ወታደር ሀዋ ሙሃመድ ከተመረቀች በኋላ የመጀመሪያ ግዳጇ የሆነው በሀገር ክህደት ፈጽሞ ሀገር ካልበተንኩ ብሎ የተነሳውን ሽብርተኛው ትህነግ እኩይ ዓላማውን መፈጸም እንደማይችል ለማሳየት በታወጀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ነበር፡፡ በትግራይ ክልል መሽጎ ሲያቅራራ የነበረውን ሽብርተኛው ትህነግ የሚደመሰሰውን በመደምሰስ፣ የሚማረከውን በመማረክ እና የሚበተነውን በመበተን ከስምንት ወራት በላይ ቆይታለች፡፡
መሰረታዊ ወታደር ሀዋ “ሙሉ ትጥቅ ታጥቆ፣ ስንቅ አንጠልጥሎ ዓመት ሙሉ ማሳለፍ ቢከብድም እኛ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘቦች ነንና በየቀኑ ይህንን እናደርገዋልን” ነው ያለችው፡፡ ዳግም ወረራ ፈጽሞ ሕዝብን እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ እየዘረፈ እና እያሰቃየ ያለውን የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ከጓዶቿ ጋር የገባበት ገብተው ወደ ሚፈልገው ሞት እየሸኙት ነው፡፡
“የጠላትን አስከሬን ተረማምዶ ማለፍ እና በጠላት ምሽግ ውስጥ ቦንብ ወርውሮ ማጋየት ደስታው ወደር የለውም” የምትለው መሰረታዊ ወታደር ሃዋ ይህንን ጀብዱ ፈጽማ እና የጠላትን ምሽግ አመድ አድርጋ ደስታውን አጣጥማዋለች፡፡
በተሰጣቸው ወታደራዊ ግዳጅ ጋንታዋ ምሽግ ሰባሪ ናት፤ ሃዋ ደግሞ የዚህ ግዳጅ አብሪ ኮኮብ ነበረች፡፡ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ፍጹም ጥንቃቄን እና የላቀ ጀግንነትን ትጠይቃለች፡፡
ትዕዛዝ ስትጠባበቅ የነበረችው ሃዋ ትዕዛዙ እንደደረሳት ጊዜ ሳትወስድ አከታትላ ቦንብ በሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ጭንቅላት ላይ አወረደችባቸው፡፡ በወረደበት የቦንብ ናዳ የሚገባበት የጠፋው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አየር ሳያገኝ ምሽጋቸው ድረስ ዘላ ገብታ የጥይት እሩምታ አርከፈከፈችባቸው፡፡ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን አሳንሶ ከማይችለው ኀይል ጋር የገጠመው የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላቱ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይቀሩ እስከ ወዲያኛው በነሃዋና ጓደኞቿ ተሸኙ፡፡
እነሃዋ የተሰጣቸውን ወታደራዊ ግዳጅ በላቀ ጀግንነት ፈጽመው ከያዙት አባል ሳያጎሉ የፈለጉትን ድል ተጎናጸፉ፡፡
ሌላኛዋ አሚኮ ያነጋገራት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል መሰረታዊ ወታደር ዓለሜ አሥራት ትባላለች፤ ከሌሎች ጓዶቿ ጋር በመሆን የተሳካ ግዳጅ በላቀ ውጤት እያስመዘገቡ ነው፡፡ ወታደርነት ከባድ ኀላፊነት እንደሆነ ገልጻ “የሕዝቡ ደጀንነት ከዚህ በላይ ኀላፊነት እንድትሸከም ያስገድዳል” ብላለች፤ መሰረታዊ ወታደር ዓለሜ፡፡ ነገም ለሌላ ግዳጅ እና ድል ዝግጁ መሆኗን ስትናገር በልበ ሙሉነት ነው፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን እነ መሰረታዊ ወታደር ዓለሜ ፊት የመቆም የሞራልም የአካልም ብቃት የለውም፡፡
የወታደር ልጅ ነች፤ አባቷ ለ16 ዓመታት ሀገራቸውን በውትድርና ሙያ አገልግለዋል፤ ዛሬም በአንድ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ውስጥ አሰልጣኝ ናቸው፤ ውትድርናን የምታውቀው ከልጅነቷ ጀምሮ በመሆኑ 11ኛ ክፍል ስትደርስ ለአባቷ ወታደር መሆን እንደምትፈልግ ገልጻ ይሁንታቸውን ስታገኝ ወደ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተላከች፤ መሰረታዊ ወታደር ሐቢባ አባ ፊያ አባ ፊጣ፡፡
የውትድርና ሙያን በቅርቡ የተቀላቀለችው መሰረታዊ ወታደር ሐቢባ በትምህርት የምታውቀውን የውጊያ ስልት ሽብርተኛውን የትህነግ ወራሪ ቡድን በመደምሰስ በተግባር ድል እየተጎናጸፈች ነው፡፡ በዚህ የህልውና ዘመቻ “የእናቴን ጠላቶች ደምስሻለሁ” የምትለው ወታደር ሐቢባ በአንድ ግዳጅ ብቻ ሽብርተኛውን የትህነግ ወራሪ ቡድን የገባበት ገብታ በመደምሰስ ስምንት ትጥቅ ማርካ፣ ክላሽ እና ጥይት ተረክባ፣ ስናይፐራቸውን ቀምታ እና እስከ ወዲያኛው ሸኝታ ምርኮ አስረክባለች፡፡
“እያሳደድን ጥለን ትጥቃቸውን ገና ሕይዎታቸው ሳያልፍ ከወገባቸው ፈትቸዋለሁ” የምትለው መሰረታዊ ወታደር ሐቢባ “በእንደዚህ አይነት ድል መካከል ብሰዋ እንኳን ለሀገሬ ነውና በደስታ እቀበለዋለሁ” ነው ያለችው፡፡
አራቱ እንስት አናብስት ከወንድ ጓዶቻቸው ጋር ሁሉንም ግዳጆች በብቃት የመወጣት አቅም እንዳላቸው በመግለጽ ሴት እህቶቻቸው የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ በተለይም የአማራ ሕዝብ በየቦታው እና በየግምባሩ ለወታደሩ ያሳየው ፍቅር ሙያቸውን እንዲወዱ እና በሙያቸው እንዲኮሩ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት እነዚህ ሴት ወታደሮች፡፡ የሕልውና ዘመቻውን በስኬት አጠናቀው ሕዝባቸውን እንደሚያስደስቱ ያላቸው እምነት ከፍ ያለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ (አሚኮ)
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
እንዲህ ነው ወገኔ። የሃገራችን ፍዳ ማባሪያ የለውም። አፍራሽን አፍራሽ እየተካው ከአለፈው አዲሱ ይሻላል ስንል የጨነቀው እርጉዝ ያገባል አይነት እየሆነብን ነው። አሁን ጭንቅላት ያለው ሰው ወገን ወገኑን ይገድላል? ግን ወያኔና ግብረ አበሮቹ ከባሩድ ሽታ ሌላ የሚያውቁት ነገር የለም። ይህም ጀግና ነኝ ይላል ሌላውም አላስደፍርም ይላል ተያይዞ ማለቅ ነው። በዘር፤ በጎሳ፤ በክልልና በቋንቋ የተሰመረው የሃበሻ ምድር አፓርታይድ አይነት አሰራር እንደሆነ ግልጽ ነው። ግን ወያኔ የሰጣቸውን የክልል ባንዲራ ይዘው በቋንቋቸው ዙሪያ የሰከሩ እብድ ፓለቲከኞች በሚራወጡባት ሃገር አህጉራዊና አለም አቀፋዊ እይታን ለማራመድ አይቻልም። ወያኔዎች ከፍጡር ውጭ የሆኑ አራዊቶች ናቸው። ይህ ምንም የሂሳብ ስሌት አያስፈልገውም። ያለፈና የአሁን ተግባራቸው ይመሰክራል። የትግራይን ወጣት በውሽት እያሰለፉ የሚያስጨርሱት በለመድት የሸፍጥ ፓለቲካ ነው። ውጊያ ከእኛ በላይ ላሳር እያሉ። ግን ውጊያ የኋላ ቀሮች አስተሳሰብ የሚያመነጨው ለማንም ለምንም የማይጠቅም የአውሬዎች የፓለቲካ ገጸ ባህሪ ነው። አዝማሪው እንዳለው ነው።
ጠባብ ነው እያሉ ሲንቁ፤ ሲንቁ
ነፍጠኛ ነው ብለው ሲንቁ ሲንቁ
ወንድ ነን ባዪቹ በወንዶች አለቁ።
ሌላው ዘፋኝ ደግሞ እንዲህ ይለናል ስለ ወሎ ሲያጫውተን። አቤት ደስ ሲል ያ ጊዜ
የታሪክ ሃገር ናት የፍቅር ከተማ
ወሎ አይወለድም ፈሪና ገገማ
እኮ በለ ወያኔ አሁን በወሎ ወጣቶች፤ በአማራ ልዪ ሃይል፤ በጀግኖቹ የአማራ ፋኖዎች ድኩማን ሲሆኑ ምን ሊባል ነው። አማራ ሰነፍ ነው አይዋጋም ገለ መሌ ሲሉን የነበሩት የወያኔ ጥሩንባ ነፊዎች አሁን ምን ይሉ ይሆን? የተገፋ ህዝብ የራሱን መብትና ነጻነት ለማስከበር ሲነሳ የወያኔ ጉዞ ከአፈርኩ አይመልሰኝ ሆኖበታል። አሁን በልዪ ልዪ መንገድ ድጋፋቸውን ለወያኔ የሚሰጡት የውጭና የውስጥ ሃይሎች ወያኔ ሲሸነፍ አሰላለፋቸውን ይቀይራሉ። በሳተላይት ሳይቀር ድጋፍ የሚደረግላቸው ወያኔዎች የሚያልቅባቸውን የሰው ሃይል ለዘለቄታ እየተኩ መዋጋት አይችሉም። ሂሳብ አወራርዳለሁ ሲሉ ሂሳብ እየተሰራባቸው ነው። በሃበሻው ፓለቲካ የማይረዳኝ ነገር እልፍ ቢሆንም አንድ ነገር ግን ጭራሽ ጨለማ ሆኖብኛል። እንዴት ነው የአማራና የአፋር ህዝብን በእሳት እያጋዪና እየዘረፉ ” የአላማ ጽናት” የሚባለው? እየሞቱና እያቃጠሉ ምን አይነት የአላማ ጽናት ነው የሚገኘው? የወያኔ ደጋፊዎች በዘራቸው የሰከሩ እውነትን ለማየት የዘገዪ ሙታኖች ናቸው። አሁን ማን ይሙት የትግራይ ህዝብ ይህን ጦርነት ይፈልጋል? ጭራሽ? አማራውና አፋሩ ከትግራይ ወገኖቹ ጋር መላተም ይሻል። አይታሰብም። ይህን ሁሉ ያመጣው የወያኔ የስልጣን ጥም ብቻ ነው። ይህ የማይገባው የትግራይ ተወላጅ ከእውነት ተስፈንጣሪና በቁም የሞተ ነው። በቅርቡ በትግል ላይ ለወደቁ ሰዎች የህሊና ጸሎት ወያኔዎች ሲያደርጉ የተነሳ እውነተኛ ፎቶ ሰው ላከልኝና እንዲህ አልኩት። እንዴት ባለ ስሌት ነው ህሊና የሌለው ሰው የህሊና ጸሎት የሚያደርገው ብዬ ለጻፍኩለት ሲመልስ። ስህተቱ የእኔ ነው እንዲህ እንደምትል አውቅ ነበር በማለት ፎቶውን ዴሊት አደረኩት። ይህ ጦርነት ባጭር ካልተቋጨ የሚያመጣው መዘዝና ሰቆቃ አሁን ከምናየውና ከምንሰማው የከፋ ይሆናል። በቃኝ!