በአዲስ አበባ 1 ሺሕ 338 ሄክታር መሬት አሁንም በወረራ ተይዞ እንደሚገኝ አስተዳደሩ አስታወቀ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በህገወጥ መሬት ወረራ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ወይዘሮ አዳነች በዚህ ጊዜ እንዳሉት በአዲስ አበባ ካሉ 121 ወረዳዎች ውስጥ በ88ቱ የመሬት ወረራ ተፈጽሟል።
በአጠቃላይ በከተማዋ 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት የተወረረ ሲሆን በተደረገው የህንጻ ቆጠራ 322 ህንጻዎች እና ቤቶች ባለቤት አልባ መሆናቸውን ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል። ወይዘሮ አዳነች በዚህ ጊዜ እንዳሉት በአዲስ አበባ በህገወጥ መንገድ 21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ተይዘው መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ቤቶች ውስጥ 15 ሺህ 891 ቤቶች የባለቤትነት መረጃ አልቀረበባቸውም። 850 ቤቶች ደግሞ ዝግ ሆነው ሲገኙ 4 ሺህ 530ዎቹ ደግሞ ባዶ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ዝርዝር ማብራሪያው እንደሚከተለው ነው፦
– በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ 13,389,955 ካሬ ወይም 1,338 ሄክታር መሬት በህገወጦች ተይዟል። በከተማዋ ካሉ 121 ወረዳዎች በ88ቱ ወይም በ73 % በሚሆኑት ላይ ወረራ ተፈፅሟል።
– በአጠቃላይ ባለቤት አልባ በሚል የተለዩ ህንፃዎች በድምሩ 322 ሲሆኑ የቦታ ስፋታቸው 229,556 ካሬ ነው። ከነዚህ ውስጥ ግንባታቸው የተጠናቀቁት 58 ሲሆኑ 125፣ 409 ካሬ ላይ ተገንብተውና ተከራይተው ያሉ ነገር ግን ባለቤት ነኝ የሚል አካል መረጃውን እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ማቅረብ ባለመቻላቸው ባለቤት አልባ ሆነው ተገኝተዋል።
– ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ እንዲሁም ባለቤታቸው ያልታወቁ ህንፃዎች ብዛት በድምሩ 264 ሲሆኑ ስፋታቸው ደግሞ 104,147 ካሬ ላይ ያረፉ ቤቶች እና ህንፃዎች ናቸው። እነዚህ ቤቶች በተለይ በየካና በላፍቶ ክ/ከተሞች ላይ በአንድ አካባቢ መሬት በመውረር ግንባታ የተገነባባቸው ናቸው።
የኮንደሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ፦
– በህገወጥ መንገድ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶች በጠቅላላው 21,695 ሲሆኑ 15, 891 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መረጃ ያልቀረበባቸው ናቸው።
– 4530 ባዶ የሆኑ ፣ 850 ዝግ የሆኑ ፣ እና 424 በህገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው ይገኛሉ።
– በዕጣ ሳይሆን በተለያዪ አግባቦች ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51,064 ቤቶች ተገኝተዋል፡፡
– በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች ስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መሀከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132,678 እንደሆኑና 18,423 ቤቶች ደግሞ የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው ናቸው። በእነዚህ ቤቶች የሚኖሩ ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ በመሆናቸው ቤቶቹ በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸውም ታውቋል።
ያልተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች በተመለከተ፦
28 ብሎክ ማለትም ከ782 እስከ 842 የሚሆኑ ቤቶች እና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች (ኮሚናል ) ደግሞ 83 ሳይገነቡ መቅረታቸውን ተገልጿል።
በፌደራል እና በአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች በተሰራው የኦዲት ውጤት መሰረት በአጠቃላይ ላልተገነቡ ህንፃዎች የቦርድም ሆነ የስራ አመራር የውሳኔ ቃለ ጉባኤ አልተገኘም።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ፥ ምንም እንኳን መረጃ ባይገኝም ለግንባታው ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር በኦዲት ጥናቱ ማመልከቱን ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚተዳደሩ 150 ሺህ 737 የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች አሉ፡፡ ዛሬ ይፋ በሆነው ጥናት ተደራሽ መሆን የተቻለው 138 ሺህ 652 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን እንደሆነ ተገልጿል።
በከተማዋ 10 ሺህ 565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባት ፣ እና በሌሎች ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ እንደተያዙ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ፡-
1ኛ. 7,723 ቤቶች ውል በሌላቸው (ህገወጥ) በሆኑ ሰዎች ተይዘዋል፡፡
2ኛ. 2,207 የቀበሌ ቤቶች ወደግል የዞሩ፣
3ኛ. 265 በሶስተኛ ወገን የተያዙ፣
4ኛ. 164 ኮንደምንየም በደረሳቸው/የራሳቸው ቤት ባለቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ታውቋል።
5ኛ. 137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፤
6ኛ. 1 ሺህ 243 ታሽገው/ተዘግተው የተቀመጡ፣
7ኛ. 5 ሺህ 43 የፈረሱ፤
8ኛ. 180 አድራሻቸው የማይታዎቁ/የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡
የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተ፦
በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25,096 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶች ብዛት 4,076 ናቸው።
1ኛ. 1 ሺህ 70 የንግድ ቤቶች ውል የሌላቸው ነጋዴዎች እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ተለይቷል
2ኛ. 2 ሺህ 451 የቀበሌ የንግድ ቤቶች ከአንድ በላይ የንግድ ቤት በያዙ 1,086 ነጋዴዎች እንደተያዙ ተለይቷል
3ኛ. 376 የቀበሌ ንግድ ቤቶች ደግሞ በተከራይ ተከራይ በሶስተኛ ወገን መያዛቸው ተለይቷል፣
4ኛ. 179 የታሸጉ የንግድ ቤቶች እንዳሉ ተለይቷል፡፡ (መረጃው የተጠናቀረው ከፋና፤ የአዲስ አበባ ፕሬስና ቲክቫህ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Zekarias Minota says
Thank you for disclosing such a vital information to the public at large. The most important measure would be returning the properties to the respective owners. Then the full thanks giving would be delivered to the respective bodies. The government shall stay transparent, responsible and accountable to public scrutiny. Public trust and recognition is power.
Zekarias Minota says
Thank you for disclosing such a vital information to the public at large. The most important measure would be returning the properties to the respective owners. Then full thanks giving would be delivered to the respective bodies. The government shall stay transparent, responsible and accountable to public scrutiny. Public trust and recognition is power.
Tesfa says
እሰይ እንዲህ ነው የሥልጣኔአችን ምልክቱ። የውጭ ጠላት ሳይመጣ ስለ መሬት ወረራ ማውራት። ለነገሩ ተወረናል በሱዳን ጉዳዪ ለየብቻ ሆነ እንጂ! ወቸው ጉድ። አያድርስ ይላሉ አበው። እውቁ ደራሲ ስብሃት ገ/ሄር እንዲህ ብሎ ነበር። ” አለም ራሷ ለጥቁር ህዝብ ሲኦል ናት” ይህን ያለው ዝም ብሎ አልነበረም በአሜሪካ፤ በፈረንሳይ፤ በስዊዝ በሌሎችም ሃገሮች ያየውንና በሃገራችን የሚፈጸመውን በደል ሁሉንም ቀምሮ እንጂ። ታዲያ በደራሲው ዘመን የንጉሱን መንግስት የተጠናወቱ ሰዎች መሬት ላራሹ የሚለውን መፈከር አንግበው ሲፋከሩ እሱም አይቷል። ሌላው እውቅ ደራሲ አቤ ጎበኛ “አልወለድም” በተሰኘውም መጽሃፉ ላይ ይህኑ የመሬት ስሪትና የጭሰኛና ጉልተኛ ስርዓቱን በማጣጣል የመሬት ላራሹን እይታ የበለጠ አስፍቶ ገልጦታል። ብዙዎች መሬት ላራሹ በማለት ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተገድለዋል ተግዘዋል። የአሁኑ የመሬት ጉዳይ ሌላ ነው። የአራሹ ስም የሚነሳው መፈናቀሉ ሲወራ ብቻ ነው። እስቲ እናያለና ፎቅ ዳቦ ሲሆን! ወደ ሃሳቤ ልመለስ፤ ታገሱኝ ቡና ሻሂ እያላችሁ ሃሳቤን እዩት።
የመሬት ወራሪዎቹ እነማን ናቸው ብለን ስንጠይቅ መልሱ በጥቅል የቀንና የማታ የወረፋ አለቆቻችን ብሎ መመለሱ ወያኔንና የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞችን ለእኔ ብቻ እይታ ከችግሩ ማህል ያስገባልናል። ደላላው እንደፈለገ በሚያወላግዳት ሃገር ውስጥ ሰርቆ መኖር ብልሃት ከሆነ ቆይቷል። በዘርና በቋንቋ መጠቃቀም ልስጥህ ስጠኝ ላካፍልህ አካፍለኝ የሚለው ምንም አይነት የሰው ስብዕና የሌለው የቁስ አካል ፍቅር ደዌ ከሆነ በሃገራችን ሰነባበተ፡፡ ሰው የሚታወቀው በሚነዳው መኪና፤ በሚያከራየው ቤት (ልብ በሉ በሚኖርበት ቤት አይደለም)፤ የስርቆት ሽርኮቹን ደግሶ ብሉልኝ ጠጡልኝ በማለቱ ነው። ዛሬ በዓለም ዙሪያ ጫካዎች እየተመነጠሩ፤ ለንግድ የሚሆኑ የእጽዋትና የእህል ዝርያዎች እየተተከኩ፤ በጫካዎቹ ተጠልለው የሚኖሩ አውሬዎች ነፍሴ አውጭኝ በማለት ከሰው ጋር በግድ ያለውድ ጉርብትና የጀመሩበት፤ በዚሁ ሳቢያ ታይተው የማይታወቁ በሽታዎች ብቅ ብቅ ያሉበት፤ ገበሬዎች ማሳቸውን በባለሃብት ተነጥቀው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የተሰሩበት፤ በዚህም መዘዝ የምግብ ዋስትና የጠፋበት፤ የምግብ ዋጋ በመናሩ አይ ፈጣሪ እንድንል ያደረገን የዘመኑ ባለሃብቶች በድሃው ላይ የሚያደርሱት ሰቆቃ እንኳን የሰው ልጆችን የተንጣለለው ሰማይን ያስለቅሳል። ታዲያ አሁን ሰው ሁሉ በአዲስ አበባ የመሬት ዝርፊያ/ቅሚያ ወዘተ ይበል እንጂ ጉዳዪ በሃበሻው ምድር ሁሉ እየተፈጸመ እንደሆነ መረጃ አለ። ያለምንም ጥናት በሽቅድድም ፓለቲካና አሻጥር ተጀምረው ቆመው የቀሩ፤ መሬቱ ብቻ ታጥሮ እሳርና እሾህ ያበቀለ፤ የአካባቢው ሰው ተፈናቅሎ የንግድ ነገሮች የተተከሉበት፤ ለተፈናቀለው ህዝብ ምንም አይነት ፋይዳ የማይሰጡ በዝባዥ ኩባኒያዎች አካባቢውን የበከሉበት ሁኔታ ይስተዋላል። አንድ ነገር ልጥቀስ። በአዲስ አበባ በቀን 100 በላይ ፍየልና በግ የሚያርድ አንድ ምግብ ቤት አለ አለኝ አንድ ውስኪ ጨላጭና የዓለም አጫዋች። እኔም መልሼ ይህን ሁሉ ለሚያቀርቡለት ገበሬዎች የሚያደርገው ድጋፍ ምን አለ አልኩት። አይ እሱ ከደላላ ጋር ነው ግንኙነቱ ከእነርሱ ጋር አይደለም አለኝ። ፍየልና በጎቹ ሲያልቁ ምን ሊያርድ ነው ስለው ጸጥ አለ። የቀን ዝርፊያ ይሉሃል ይህ ነው? ያው እንደ ቻይናዎቹ የአህያና የፈረስ ሥጋ የበግና የፍየል ነው እያለ ፍየልና በጎቹ ሲያልቁ ያቀርብ ይሆናል። ሰው እንደሆነ ሥጋ በመብላት ተለክፏል። እስቲ አስቡት ሥጋን ስጋ ሲበላው! በዚህ አስተራረድ ይህ ምግብ ቤት ፍየልና በግ አልባ መሆኑ አይቀሬ ነው። ግን ማን ይህን ያስባል። ጮቤ መርገጥ ነው። ያዘው ጥለፈው አካኪ ዘራፍ በሚባልበት መሬት ላይ ረጋ ብሎ የዛሬን ከነገ ጋ አማትሮ ማየት የት ተገኝቶ። በህልም ዓለም መኖር! ለዛሬ ኑሮ መሞት!
በእውን መሬት ላራሹ ወይስ መሬት ለባለሃብት ነው ያለንበት ዘመን ዘይቤና ጎዳና? ከሆነስ ማን ያረሰውንና በምን ላይ የተዘራውን በልቶ ነው ባለሃብቱ ሃብታም የሚሆነው? የአለም ህዝብ ቁጥር ሰማይ ጠቀስ በሆነበት በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን የሚታረሱ መሬቶች እየመነመኑ መምጣት አለምን ከመሰረቷ የሚንጣት የረሃብ ውርጅብኝ እንደሚመጣ ከአሁኑ ይታየኛል። ልብ በሉ። አይ እኔ ነብይ አይደለሁም። ነብይ ነን የሚሉትንም አልወድም። ጠንቋይ ይሻለኛል ለምን ብትሉኝ መጋረጃ ጀርባ እንጂ መድረክ ላይ ሆኖ ስለማይተነብኝ። ያላየሁትን ነገር አላምንም በድምጽ ብቻ ሰውን አልከተልም። ማይክሮፎን ይዘው እንዲህ እና እንዲያ የሚሉ ደብተራዎችን/የፈውስ አታላዪች/ስመ ነብያቶችን ሁሉ እኮንናለሁ። ዝም ጭጭ ምጭጭ ቢሉ በወደድኩ ግን እነርሱስ ገቢ አይደል የሚፈልጉት እንዲህ ነው ለሰማይ ማደር ሰው እየዘረፉ ጽድቅ!
የሚቀማው ይቀማል፤ የሚዘረፈው ይዘረፋል፤ የሚፈናቀለው ይፈናቀላል፤ እርድ የሚያቀርበው ከብቶቹ እስኪያልቁ ሰው ሥጋ ይበላል፤ ፎቆም በቆመበት ለቆመለት ይሸለማል፤ አለቆቻችንም በጊዜአቸው እንደ ጧት ጤዛ ይበናሉ፤ ድሃውና የተገፋው ከለቅሶ ወደ ለቅሶ ትውልድን እያሻገረ የገመና ኑሮውን ይገፋል። የቲያትሩ ፍጻሜ አትራፊ አይኖረውም። በታይታኒክ መርከብ ላይ የነበሩት ሁሉ እጣ ፈንታቸው አንድ እንደሆነ ሁሉ የዚህ የመሬት ንጥቂያውና ግንባታውም በጊዜው የሮም አወዳደቅ ወድቆ የድንጋይ ክምር ይሆናል። በግፍ የተገኘ ሃብት የሚበላው ሌላ ነው። ያ ካልሆነ ደግሞ ዶጋ አመድ ነው የሚሆነው? ለመሆኑ ለሰው ልጅ ለመኖር ( 90 ዓመት ይኖራል ብለን ብናሰላው ለነገሩ የእኛው ህይወት የዝንብ ነው የ 24 ሰአት ጊዜ፡ ዛሬ ታይቶ ነገ የለም) ምን ያህል ሃብት ያሻዋል? በእኔ ግምት በጣም ትንሽ። እጅግ ትንሽ። ራሳችን ጥቂቱ ብዙ ነው ብለን እስካላሳመንን ድረስ ያው ስንቀማና ስናስቀማ ኑረን እንሞታለን። በስብሃት ገ/ሄር ቀልድ ልዝጋ። አንድ ጊዜ አንድ ጓደኛው ወይ በጣም ድመት እፈራለሁ ቢለው አይዞህ ነፍሳችን የአይጥ ነፍስ ስለሆነች ነው እንዳለው ትዝ ይለኛል። ቡናና ሻሂው አለቀ? እኔም በቃኝ!