
የአሜሪካንን ዜግነት ለመውሰድ ቀኝ እጅን ወደ ላይ ቀስሮ መማል ግድ ነው። እከሌ ከገሌ ሳይባል “ቀደም ሲል የነበረኝን ዜግነት እክዳለሁ” በማለት የሚከናወነው ምህላ “እግዚአብሔር ይርዳኝ” በሚል ማሳረጊያ ይቋጫል።
“ቀደም ሲል የነበረኝን ዜግነቴን፣ የማንኛውንም የልዑል፣ የግዛት፣ የአገር፣ ወይም የሉዓላዊ መንግሥት ተገዢነቴን በሙሉና በፍጹም መካዴን በምሕላ አውጃለሁ” በሚል የሚከናወነው የመሐላ አሰጣጥ፣ ምሕላውን በፍጹምና ያለምንም ማወላዳት መቅበልን የሚጠይቅ ሲሆን ይህንንም ቀኝ እጅ በማውጣት የሚከናወን ሥርዓት ነው።
Oath
“I hereby declare, on oath, that I absolutely and entirely renounce and abjure all allegiance and fidelity to any foreign prince, potentate, state, or sovereignty, of whom or which I have heretofore been a subject or citizen; that I will support and defend the Constitution and laws of the United States of America against all enemies, foreign and domestic; that I will bear true faith and allegiance to the same; that I will bear arms on behalf of the United States when required by the law; that I will perform noncombatant service in the Armed Forces of the United States when required by the law; that I will perform work of national importance under civilian direction when required by the law; and that I take this obligation freely, without any mental reservation or purpose of evasion; so help me God.”
የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት፣ ሕጎችና ሠንደቅ ዓላማ ከውጪም ሆነ ከአገር ውስጥ ካሉ ጠላቶች ሁሉ መከላከል፤ ከልብ በእውነትና በእምነት ታማኝነት መሆን፣ ሕጉ በሚጠይቀው መሠረትና አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስን ወክዬ መሣሪያ ማንገት፤ በሕግ በተፈለገ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች ውስጥ ከውጊያ ውጭ የሆነ አገልግሎት ማከናወን፣ በሚፍለግ ጊዜ በሲቪል መመሪያ መሠረት አገራዊ ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት፣ እንዲሁም ሕጉ የሚለውን ሁሉ ያለ አንዳች ማመንታት በሙሉ ፈቃደኛነት፣ ያለሽሽት ለማከናወን ቃለ መሃላው ይከናወናል። ይህን ቃለ መሐላ ሲጠናቀቅ መሐላውን የሚፈጽመው ግለሰብ መሐላውን ተግባራዊ ለማድረግ “እግዚአብሔር እርዳኝ” ይላል።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደ እርሳቸው አባባል ከሆነ ይህን የመሐላ ሂደት አልፈው ፈጽመዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑም አቡነ ማቲያስም ምለው ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው አሜሪካዊነትና ለሠንደቅ ዓላማው ቃል ገብተው ተቀብለዋል።
ከአራተኛው ክፍለዘመን (ከአብርሃ ወአጽብሐ ዘመን) አንስቶ ከ1,400 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ፓትሪያርክ ይላክ የነበረው ከግብጽ ነበር። ይህ አሠራር እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ድረስ ቀጥሎ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ ሆነው የተሾሙት አቡነ ባስልዮስ እንደነበሩ ይታወቃል።
ለበርካታ ዓመታት ከግብጽ ፓትርያርክ ሲሾምላት የነበረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አሁን ደግሞ በቃለ መሐላ ዜግነታቸውንና ሠንደቅ ዓላማቸውን በቀየሩ “አባቶች” መመራቷ ሥጋት እንደሆነባቸው የሚገልጹ ወገኖች “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ባላት ክብር ለሌሎች ሁሉ አርዓያ፣ ለታሪክም ማጣቀሻ ሆና ሳለ ሠንደቅ ዓላማዋንና አገራቸውን በምህላ ‘እግዚአብሔር ይርዳኝ’ ብለው በተው፣ በካዱ፣ ባወረዱ መመራቷ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም” ሲሉ በተለያዩ ወቅቶች መናገራቸው ይታወሳል። ይህን በማለታቸው መከራም የተቀበሉ ጥቂቶች አይደሉም።
ዛሬ (ማክሰኞ) “በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ተሰማ” በሚል በርካቶች እየተቀባበሉት ያለው ዜና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ተከልክለው ወደ አሜሪካ ለመመለስ የመገደዳቸው ጉዳይ ነው።
አቡነ ጴጥሮስ የተናገሩበትን መገናኛ ከጠቀሱት መካከል ቲክቫህ “ብፁዕነታቸው ከደቂቃዎች በፊት ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል አሁን አሳፍረውኝ ተመለስኩ፤ ወደ አሜሪካ ወደ መጣሁበት መለሱኝ ፤ ወደ ሥራዬ እንዳልመለስ ከለከሉኝ ” ማለታቸውን አስነብቧል።
አውሮፕላኑ ሊነሳ ስለነበር በችኮላ አስተያየት መስጠታቸው ተጠቁሞ በተሰራጨው ዜና ወደ አሜሪካ እንዲመለሱ የተደረገበትን ምክንያት ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ዘገባው ምክንያቱን ከማተም ውጭ ላቀረቡት ምክንያት የማንጠሪያ ጥያቄ አንስቶ ዜናውን አላፍታታም።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ “በቃ ግሪን ካርዱን ብቻ ነው የምንፈልገው፤ እኛ ያንተን ፓስፖርት አንፈልግም፤ ግሪን ካርድ ብቻ ነው የምንፈልገው፤ ብለው ወሰዱ በሩን ዘጉ!” ሲሉ ለተጠየቁት ምላሽ መስጠታቸውን ተመልክቷል። “ይህን ያደረጉት የደህንነት ሰዎች ናቸው” ማለታቸውም በዜናው ተመክልቷል። አቡነ ጴጥሮስ ግሪን ካርድ ሲሉ የጠቀሱት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ቢጫ ካርድም ሊሆን ይችላል። ይህ ግን በየትኛውም አካል አልተስተባበለም።
ብፁዕነታቸው ወደ አውሮፕላን እንዲገቡ ከመደረጋቸው በፊት ውጭ ላይ ሲጉላሉ እንደነበር ተናግረው አንድ የኢሚግሬሽን ሰው “የማውቀው ነገር የለም ግሪንካርዱ ትክክል አይደለም” እንዳላቸውና እርሳቸውም ግሪንካርዱ ገና 3 ዓመት እንደሚቀረው እንደነገሩት አስረድተዋል።
ይህን ሲያስረዱ ከግለሰቡ መልስ እንዳልተሰጣቸውና “ሌሎች ሰዎችንም ዲፖርት እያደረግን ነው” በማለት እንደነገራቸው ገልጸዋል።
አቡነ ጴጥሮስ የአሜሪካ ፓስፖርት እንዳላቸው ገልጸው ፤ “እሱን ምንም ለማድረግ ስላልቻሉ ግሪንካርድ እንወስዳለን በማለት ወስደዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከሳምንታት በፊት ለአገልግሎት ከሀገር ሲወጡ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ ሌሎችም “ሊያስቀሩህ ይችላሉ” የሚል ነገር ሰምተው እንደነገሯቸው ነገር ግን በአሜሪካ የያዙትን አገልግሎት መተው ስላልፈለጉ ወደ አሜሪካ መሄዳቸውን እንደገለጹ ቲክቫህ ጽፏል።
ዜናውን የሰሙና ለአሠራሩ ቅርበት ያላቸው እንዳሉት ከሆነ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ “እንዴት የአሜሪካ ፓስፖርትና ግሪን ካርድ በአንድነት እጃቸው ላይ ተገኘ” በሚል ጠይቀዋል።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ከላይ የተገለጸው የቀድሞ ማንነትን የ”መካድ ምህላ” ከተከናወነ በኋላ የአሜሪካ ዜግነት ሲወሰድና ፓስፖርት ሲሰጥ የቀድሞውን ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ወይም በተለምዶ ግሪን ካርድ የሚባለውን መመለስ ግድ ነው። ይህም በአሜሪካ የዜግነትና የኢሚግሬሽን አገልግሎቶች ድረገጽ በግልጽ የተቀመጠ ነው። ስለዚህ በሌላ አነጋገር እንደ ፓትሪያርኩ አቡነ ማቲያስ አቡነ ጴጥሮም አሜሪካዊ ዜጎች ናቸው ሊባል ይችላል።
አሠራሩ ይህ ከሆነ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፓስፖርትና ግሪን ካርዳቸውን ሁለቱንም አጣምረው በጃቸው እንዴት ሊይዙ ቻሉ? ለምንስ ያዙ? ማን ነው ይህንን የጠቆመባቸው? ለምንስ ቦሌ ላይ ተጠየቁ? ለሚሉ ጥያቂዎች ምላሽ ሊቀርበብት እንደሚገባ እነዚሁ ወገኖች ይጠይቃሉ። ወይስ እርሳቸው ግሪን ካርድ ሲሉ የጠቀሱት ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ቢጫ ካርድ ነው? ይህንንም ቢሆን በራሳቸው አንደበት ማስተካከል አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ እና እርሳቸውም በቃላቸው በተናገሩት መሠረት የአሜሪካ ፓስፖርት ባይኖራቸው ኖሮ ግሪን ካርዳቸውን ተነጥቀው በኢትዮጵያ ፓስፖርት አሜሪካ መግባት አይችሉም።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የነፍጥ ትግል እያራመዱ ያሉትን “እንመራለን፣ የትጥቅ ትግሉን ሃይማኖታዊ እናደርጋለን” ከሚሉ ክፍሎች ጋር ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በአሜሪካ በቆዩበት ጊዜ እንደታዩ የመረጃው ባለቤቶች ለጎልጉል ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት እነዚሁ ክፍሎች የሚመሯቸው ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ትሥሥሮች ላይ ጉዳዩን ከፖለቲካ በማያያዝ “ኮበለሉ” የሚሉ መረጃዎች አሰራጭተው ነበር። ይህ ከተሰራጨ በኋላ ቤተክርስቲያኗ መግለጫ አውጥታ እንደነበር የሚታወስ ነው። በመግለጫቸው በሕጋዊ መንገድ በቤተክርስቲያን ዕውቅና ከሀገር እንደወጡና ሀገር ሊክዱ የሚችልበት ምክንያት እንደሌለ ተመልክቶ ነበር።
አቡነ ጴጥሮስ የዜግነት አገራቸው አሜሪካ ከደረሱ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደሚመለሱ የታወቀ ነገር ባይኖርም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለመኖር በቅድሚያ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠውን ቢጫ ካርድ ማግኘት አለባቸው። ካርዱን ከመቀበላቸው በፊት በአሜሪካ ፓስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከፈለጉ ለአንድ ወር የሚቆይ የቱሪስት ቪዛ አስመትተው ወደ አገር ከገቡ በኋላ ከሒልተን ጀርባ ካዛንቺስ መስመር ላይ ከሚገኘው የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት በየአምስት ዓመት የሚታደስ ቢጫ ካርድ ማውጣት አለባቸው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ምድሩ ሁሉ ወስላታ የሆነበት እንደ ሃበሻ መሬት የለም። ሲጀመር የአሜሪካ ዜጋ ሲኮን በእጅ ያለ የግሪን ካርድ መታወቂያ መመለስ ነበረበት። በሁለት ቢለዋ መብላት ማለት ይህ ነው። ዜግነት መቀየሩ እንዳይታወቅ ጊዜው ያላለፈበት የአሜሪካ
የግሪን ካርድ መታወቂያ ማቅረብና ህጋዊ የሆነውን ፓስፓርት መደበቅ ምን የሚሉት ማጭበርበር ነው? ለነገሩ የሃበሻው የኢሚግሬሽን አገልግሎትና ደህንነት ክፋትን አያውቁም ማለትም አይቻልም። በዘሩ ተንፍሶ በቋንቋው አውርቶ፤ ነገርን አጣመው የሚያዪ የአንድ ዘር ጥርቅሞች በመሆናቸው። ግራም ነፈሰ ቀኝ ይህም ያም የሰውየውን መመለስ እንደ ፓለቲካ ማጣጫ ዜናቸው መጠቀማቸው ሆን ተብሎ የተሰላ ነገር ነው። የሚያስገርመው ነገር ግን አንድ ታላቅ ሰው የሆነ ከውጭ ለሥራ ተግባር ወደ ተወለደበት ምድር ሲገባ እንዴት ነው ገብተው ይህን ያን ያደርጋሉ አለመባሉ? በዚህ ቀን እዚህ ቦታ በዚህ ሰአት እንዲህ አይነት ምክክር ስብሰባ ይኖራል ተብሎ አለመነገሩ? የመግባታቸው ምክንያት አጀንዳ የት አለ? ግን ሚስጢሩ ጠሊቅ ነው እንዲገቡ የገፋፋቸው የራሳቸው ሰዎች እንዳይገቡ መንገድን ከዘጉባቸው መካከል ናቸው። ለዚህ ነው ሃበሻው አብሮ መከሮ ዞሮ ጠላት ካምፕ በመግባት ተዋጊና አዋጊ ሆኖ ሃገር የሚያፈርሰው።
የዓለማችን ወሬ ሁሉ ሾካካና እውነት ላይ ያልተመሰረተ፤ የተቀነሰለት፤ ካልሆነ ተጋኖ የሚወራለት ጀግና ያልሆነውን ጀግና፤ በደል ያልፈጸመውን በደለኛ በማለት ” በሰበር ዜና ” አለምን ያማታሉ። እኔን የናፈቀኝ የተሰበረ ዜና ሳይሆን ቆሞ የሚሄድ ዜና ነው። ሲፈለግ የሚገኝ። ሊዳሰስ ሊጨበጥ የሚችል ዜና። ያ ግን የለም። ሁሉም ቱልቱላ ነው። ይነፋል ያናፋል። ሶሻል ሚዲያው ለራሱ ገንዘብ ሲል ወሬው እንዲራባና እንዲሰራጭ መንገድ ያመቻቻል። ሌላው ሽራፊ ሳንቲሞችን ለመለቃቀም ወሬ ሲያገላብጥ ይውላል። የሞተ ጊዜ ላይ ቆመው የሞቱ ብዙዎች ናቸው። የቲክ ቶኳ ንግስት፤ የዪቱብ ንጉስ፤ ኸረ ስንቱ ብቻ አበው ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንዲሉ ሞኞች ሜዳ ተገኘ ብለው ይጋልባሉ። ወደ ገደል እየተጓዙ እንደሆነ ግን አልታያቸውም። ለዚህም ነው የሃገሪቱ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ፤ የሰው የተንኮልና የጭካኔ በትር እያየለ፤ በእኔ ላይ ካልደረሰ እኔ ምን አገባኝ በማለት እንደ ሜዳ ከብቶች ዝም ብለን ያለንን እየጋጥን ሌላው ሲራብና ሲሞት ጸጥ የምንለው። መደንዘዝ ማለት ይህ ነው።
ለምሳሌ የጠ/ሚሩ የትላንት የፓርላማ ውሎ ላዳመጠ ምን ያህል ጠ/ሚሩ በአፉና በተግባሩ ሰውን እንደሚገድል ያሳያል። ስለ ረሃብ ሲጠየቅ በየአስር አመቱ ረሃብ ያጠቃናል ይላል። ስለ ሰላም ሲጠየቅ የሰላም ውሉ ያተረፈልን ምንድነው ብሎ የሚጠይቅ የለም ይላል። ረጋ ብሎ የሰውየውን ቃሎችና የሚያሳየውን የሰውነት እንቅስቃሴ ለተመለከተ ጭንቅ ውስጥ ያለች ነፍስ ለመሆኗ አመላካች ነገሮች አሉ። አይ ሃገር። አይ ምድር። መቼ ይሆን ከእውነት ጋር ተገናኝተን ሰው መሆናችን በተግባር የምናሳየው? በእውነት የጳጳሱ ጉዞ ሰላም አደፍራሽ ነውን? በጭራሽ። ግን እሳቸውም የአሜሪካ ዜጋ ከሆኑ የዜግነት ፓስፓርት ማቅረብ እንጂ ሌላ ነገር ማሳየቱ ልክ አይመስለኝም ባይ ነኝ። ያም ቢሆን ተፈቅዶላቸው ቢገቡ ችግር አልነበረውም። ግን ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል ይሉ የለ። የጌዜው አለቆቻችንም ስልጣናቸውን ማሳየታቸው ነው። ግን መሆን የነበረበት ይኸው የአሜሪካ ፓስፓርቴና ልግባ ነበር ….ግን ያ አልሆነም በዚህም በዚያም ስንሸራደድ እድሜአችን ያልቃል። ውስልትና ይቅር። ዘረኝነት ይጥፋ!