አንድ ሀገር በግዛቷ ውስጥ ማን እንደሚገባ፣ እንደሚወጣና እንደሚቆይ የመወሰን መብቷ የተጠበቀ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ ከተልዕኳቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉ የተመድ ሰራተኞችን በተመለከተ ለጸጥታው ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በሰጡት ማብራርያ “የዛሬው ስብሰባ መነሻ ምክንያት የአንድን ሉዓላዊት ሀገር ውሳኔ የሚጋፋ የመወያያ አጀንዳ መፍጠሩ ተገቢ ካለመሆኑ በላይ ራስን በራስ በማስተዳደር በተወሰነ ውሳኔ ላይ እንዲሁም በሉዐላዊት አገር ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው” ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ህጎች መነሻነት ኢትዮጵያ ውሳኔውን መወሰኗንም አስታውቀዋል።
የተለያዩ አገራት በተለያየ ጊዜ የተመድ ሰራተኞችንና ዲፕሎማቶችን ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት ያለ ምንም ማብራርያ ከአገር ማስወጣታቸውን አስታውሰው፤ ተመድ በእነሱ ላይ ጥያቄ አንስቶ ያውቃል ወይ ? ሲሉ ጠይቀዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም” ሲሉ ገልጸዋል።
አንድ ሀገር በግዛቷ ውስጥ ማን እንደሚገባ፣ እንደሚወጣና እንደሚቆይ የመወሰን መብቷ በተፈጥሮም ሆነ በዓለም አቀፍ ህጎች የተጠበቀ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚጠይቀው የስራ ስነ ምግባርና እንቅስቃሴ ውጪ የተሰማሩ የተመድ ሰራተኞች ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው ሲሉ አመልክተዋል። (ኢብኮ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply