የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በሀገሪቱ ወታደራዊ አመራር የቁም እስረኛ እንዲሆኑ መደረጋቸውን መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
አል ሃዲት ቲቪ እንደዘገበው ከሃምዶክ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ኢብራሒም ለ-ሼክ፣ የመረጃ ሚኒስትሩ ሃምዛ ባሉል፣ በሚዲያ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ፋይሳል ሞሐመድ ሳሌህ በተጨማሪ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብሏል።
ከእነዚህ በተጨማሪ የገዢው ምክርቤት አፈቀላጤ ሞሐመድ አል-ፊኪ ሱሊይማን እና የዋና ከተማዋ ካርቱም ገዢ አይማን ኻሊድም መያዛቸው ተዘግቧል።
ባለፈው ወር በሱዳን የመፈንቅለ መንግሥት ከተሞከረ በኋላ አገሪቱ በተቃውሞ ሰልፍና ከሚሊታሪው ጋር ሲጋጩ በነበሩ የሲቪል ማኅበረሰቦች ስትናጥ ከርማለች።
እንደ አልጃዚራ ዘገባ የመገናኛ መሥመሩ በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቋል ከሰዎች ጋርም ግንኙነት ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ወታደራዊ አመራሩ ወደ ካርቱም የሚወስዱትን መንገዶች በሙሉ ዘጋግቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ የሽግግር መንግሥቱ በተከፋፈለበት ወቅት “(ይህ ክፍፍል) ሽግግሩን የገጠመው “በጣም አስከፊውና አደገኛው ቀውስ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ዓለማችን ልትወጣበት ወደማትችልበት ሽክርክሪት ገብታለች። የሱዳኑ ቀውስ የታለመና የታቀደ በመሆኑ ለግብጽና ለሌሎች ጽንፈኛ መለዪ ለባሾች የወረፋ የስልጣን መውጫ መሰላል ነው። ሱዳን ልክ እንደ ግብጽ ሁሌም ጠበንጃ አንጋች የሚፍገመግማት ሃገር ናት። ግን የሱዳን ደም አፍሳሽ ወታደሮች ያልገባቸው ጊዜው መቀየሩን ነው። የወታደራዊ መንግሥት ዛሬ ለአለንበት ዓለም አይመጥንም። ወደፊትም ተቀባይነት አይኖረውም። ለፈስፋሳው አብደላ ሃምዶክ የራሱን ቤት ከማስተካከል ይልቅ በድንበር ይገባኛልና በወያኔ ድጋፍ ሰጭነት ጊዜውን በማባከኑ ይኸው ዛሬ ላለበት ውርደት ደርሷል። ራሱ የሱዳን ወታደራዊ ሃይሎች ነበሩ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ያደረጉበት። ሲጀመር አሜሪካን መጠለያ ያደረገ ውጤቱ ፍሬ ፈርስኪ ነው። ሆን ተብሎ ሰው በአደባባይ በመውጣቱ ወታደሩ ስልጣን እንዲወስድ ያስጠየቁት፤ መገቢ መንገዶች እንዲዘጉና ምግብና ሌላም ነገር ለከተማዋ እንዳይደረስ የተደረገው ልክ እንደ ግብጽ መሬ ሌላ መለዪ ለባሽ በሱዳን ለማስቀመጥ እንዲረዳ ነው።
ሱዳን በባህረ ሰላጤው ሃብታም ሃገሮች እንካችሁ የምትኖር፤ ብዙም ምርት የሌላት፤ አልፎ አልፎ ከነዳጅ በሚገኝ ሃብት እዚህም እዚያም ለህዝብ ጣል የሚደረግባት ሃገር ናት። ይመስለኛል ሻቢያ ይህ ሁሉ እንደሚመጣ ቀድሞ ስለተረዳ ጦሩን በተጠንቀቅ ካቆመ ሰንብቷል። የወያኔ ፍራቻ እንዳልሆነ አውቃለሁ። እንግዲህ በዚህ የአፈሙዝ ስልጣን ንጥቂያ ሰበብ የሚመጣውን ለመተንበይ ቢያዳግትም የቀድሞው ወታደራዊ መሪ አመራሮች ሁሉ ከእስር የሚፈቱና መልሰው ኮፍያ ለባሾች እንደሚሆኑ ይገመታል። በዳርፉር፤ በኢትዮጵያ ድንበርና በደቡብ ሱዳን በኩል ያሉት ፍትጊያዎችም ከአሁኑ በባሰ ሁኔታ መልሰው ሊቀጣጠሉ ይችላሉ። ሱዳን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከግብጽ ጋር ሳይቀር ነው ያላት። አልሲሲ በካይሮ አሁን ደስተኛ ነው። ሲመክር፤ ሲዘክር የቆየበት መልሶ በሱዳን እሱን መሰል ወታደራዊ መኮንኖች በአፈሙዝ ስልጣን ላይ መውጣታቸው አስፈንድቆታል። የሱዳን ህዝብ ግን ልክ እንደ ሌላው የአፍሪቃ ህዝብ ከመከራ ወደ መከራ ይሸጋገራል። ለውጥ የምንለው ይህን ነው። እንሰንብት ብዙ እናያለን ገና። በቃኝ!