ምዕራባውያንና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በእነርሱ ይሁንታና ቁጥጥር ስር ማዋል ባለመቻላቸው፣ ኢትዮጵያንም ሆነ ቀጠናውን ማተራመስን መምረጣቸውን የአፍሪካ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ሎረንስ ፍሪማን ተናገሩ።
አሜሪካ ዜጎችን ውጡ እያለች በምትወተውትበት ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሎረንስ ፍሪማን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት የአሜሪካና የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ላይ በውሸት ላይ የተመሰረተ የስነ-ልቦና ጦርነት ከፍተዋል፡፡
ይህንን የሚያደርጉት በሚስ-ኢንፎርሜሽን ሳይሆን ሆን ብለው፣ አቅደው ተከታዮቻቸውን ዲስ-ኢንፎርም ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡
ምዕራባውያንና አሜሪካ የሐሰት መረጃ የሚያሰራጩት ኢትዮጵያውያን በመሪያቸው አማካይነት የተደፈረውን ሉዓላዊነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ እየሰሩት ያለውን ስራ የፖለቲካ ጦርነት በማካሄድ ለማዳከም ነው ብለዋል።
በባይደን አስተዳደር ውስጥ ለረጅም ግዜ ከህወሓት ጋር ግንኙነት የነበራቸውና አገሪቱን በእነሱ ቁጥጥር ስር አድርገው የነበሩ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት ፍሪማን በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱትም ይህን የበላይነታቸውን ስላጡና ወደነበረበት ለመመለስ ስለሚፈልጉ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መንግስትም፣ ኮንግረሱም፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱም በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ማመን አይፈልጉም፣ ዕውነታውን መጋፈጥም አይፈልግም ነው ያሉት፡፡ (ኢዜአ)
ምሁሩ በትዊተር ገጻቸው ደግሞ ይህንን ብለዋል፤
ከ30 ዓመታት በላይ የአፍሪካን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በመተንተን የማታወቁት አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖሊሲ ተመራማሪ ሎውረንስ ፍሪማን አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሎውረንስ ፍሪማን አዲስ አበባ መግባታቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ ስላለው ሁኔታ በትዊተር ገፃቸው ባሰራጩት መልዕክት፥ “መዋሸታችሁን አቁሙ፤ እዚህ ሁሉም ነገር ሰላም ነው፤ አፍጋኒስታን እዚህ የለችም” ብለዋል።
የኢኮኖሚ ተንታኝ እና ተመራማሪው የአሜሪካ መንግስት እና ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ከከፈቱት የስነልቦና ጦርነት በቀር ሁሉም ነገር አዲስ አበባ ውስጥ የተረጋጋ ነው ብለዋል።
“ባርና ሬስቶራንቶች በምሽትም ጭምር ክፍት ናቸው፤ ሆቴሎችም ስራ ላይ ናቸው” ያሉት ፍሪማን “ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁበት አውሮፕላን መቀመጫዎች በመንገደኞች ለመሙላት የተቃረቡ እንደሆነ ታዝቢያለሁ” ሲሉ ፅፈዋል።
ፍሪማን ቦሌ ኤርፖርት ሲደርሱ ሁሉም ነገር እንደሁል ጊዜው ሰላማዊ እና የተረጋጋ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን “መዋሸታችሁን አቁሙ በተሳሳተ መረጃ ማደናገራችሁን አቁሙ፤ የስርዓተ መንግስት ለውጥም እዚህ አያስፈልግም ” ብለዋል። (ሸገር ኤፍ ኤም 102.1)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply