
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከደቡብ ሱዳን አቻው ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ ጋር በጋራ ለመስራት በደረሰው ስምምነት መሰረት ለሀገሪቱ የደኅንነት ተቋም አመራሮች በከፍተኛ የመረጃና ደህንነት አመራር ኪነሙያ ስልጠና በመስጠት አስመርቋል፡፡
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስልጠና የወሰዱት የደቡብ ሱዳን የደኅንነት ተቋም አባላት የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የተገኙት የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ የሁለቱ ሀገራት የደህንነት ተቋማት በመረጃ ልውውጥ፤ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመቆጣጠር እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመከላከል ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የጋራ የደኅንነት ስጋቶችን ለማስወገድ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከቀጣናዊ፤ ከአህጉራዊና አለማቀፋዊ አቻ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ የደቡብ ሱዳን ናሽናል ሴኩሪቲ ሰርቪስ አመራሮች በከፍተኛ የመረጃና ደህንነት አመራር ኪነ ሙያ ስኬታማ በሆነ መንገድ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ለምረቃ መብቃታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠንካራ ትብብር እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
ተመራቂዎቹም በቆይታቸው በመረጃ እና በአመራር ኪነ ሙያ ያገኙትን እውቀትም ወደ ተግባር በመቀየር ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡ (EBC)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply