የህወሓት ዘመን ማብቂያው አካባቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ከሥልጣኔ ለቅቄአለሁ” ካለ በኋላ ለጠ/ሚ/ር ቦታ በተደረገው ሽኩቻ ዶ/ር ዐቢይ (የለማ ቡድን) አሸንፎ በወጣ ጊዜ የህወሓት ቡድን ወደ መቀሌ ሄዶ ሲመሽግ ስብሃት ነጋ በተፈጠረው ተናድዶ የሚከተለውን መናገሩ ታማጭ የመረጃ ምንጫችን አስታውቆናል። ስብሃት ነጋ በትግሪኛ የተናገረውና በአማርኛ ተተርጎመው የስብሃት ንግግር እንዲህ ይነበባል፤
“(ደመቀ) ለትህነግ ታማኝና ታዛዥ ነበር። ፈፅም! የተባለውን ነገር ለመፈፀም ‘ለምን?’ ብሎ እንኳን አያውቅም። አንድ ቀን ግን የሱዳን ግዛት የሆነውን አዋሳኝ መሬት ለመስጠት ‘ፈርም’ ሲባል ‘አይሆንም አልፈርምም!’ ብሎ አሻፈረኝ ሲል ያኔ ይህ ሰው አንድ ቀን እንደሚሸውደን እርግጠኛ ሁኜ ለጓዶቼ ነግሬያቸው ነበር። ሁሉም የእኔን እይታ ሳያቅማሙ ሲቀበሉኝ ጌታቸው (አሰፋ)ግን ‘አታስብ እሱ መዳፋችን ውስጥ ነው፤ የትም አይደርስም!’ ብሎ በንቀት ሲመልስልኝ ሲሰሙ ሌሎቹ ጓዶች በጌታቸው ላይ ከፍተኛ እምነት ስለነበራቸው እነሱም የኔን ንግግር ወደጎን ተውት።
“እኔ ግን ‘ጀግናን የሚገድለው ተራ ወይም የተናቀ ሰው ነው’ ብየ ጌታቸውን አስጠንቅቄው ነበር። የመጨረሻው የጠ/ሚ/ር የውድድር ዕለት ዋዜማ ማታ ላይ በነበረን ስብሰባም ይህ ሰው አንድ ነገር እንዳያደርግ በሚል ጥሩ ስሜት እንደማይሰማኝ ስናገር በተለይ ጌታቸው አሰፋ፣ ጌታቸው ረዳ እና አቦይ ፀሀየ ‘አትጨነቅ ደመቀ በሚገባ አምኖበታል፤ የተባለውን ባያደርግ የሚደርስበትንም ያውቃል፤ በተጨማሪ ደግሞ ሁሉንም የብአዴን፣ የኦህዴድ እና የደኢህዴን አባላት ቀጣይ የከፍተኛ ሚኒስትርነት ስልጣንና ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው በራሳቸው ሰዎች ስለተነገራቸው በደስታ ተቀብለውታል’ ብለው ሊያሳምኑኝ ሞከሩ። በእርግጥም በተለይ የደኢህዴንና የብአዴን አመራሮች ለሥልጣንና ለጥቅም የማይከፍሉት ዋጋ እንደሌለ በማስረጃ ሲያስቀምጡልኝ ባላምንበትም ይሁን ብየ ተውኩት።
“በትጥቅ ትግል ወቅትም ሆነ በሥልጣን ላይ ከሆንን በኋላ ድርጅቴ ሊደርስበት ከተጋረጠ እስከ መፍረስ የሚያደርስ ከፍተኛ አደጋዎች በአለቀ ሰዓት እንኳን እንደታደግሁ ስለሚያውቁኝ ይቀበሉኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። አሁን ግን ከእኔ ውጪ የእኔን ሀሳብ የሚያስብና የሚደግፈኝ ሰው ሳጣ ዝም ብየ ቁጭ አልኩና የሚሆነውን ለማየት ወሰንኩ። በመጨረሻ ግን ለረጅም አመታት በነበረን የትጥቅ ትግል መሰሪው ጀበሃ (ሻዕቢያ) እንኳን ሸውዶን የማያውቀውን ሽወዳ ደመቀ ሸወደን! አዋረደን! ለዚህ ውድቀታችን ተጠያቂዎች ሁለቱ ጌታቸው የተባሉትና ፀሀየ ናቸው”።
ስብሃት ነጋ እንደ አንጋፋ የህወሓት ኃላፊ ይህንን ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ሳይሰማ በመቅረቱ የለውጡ ባቡር እየተጓዘ ያለበትን ፍጥነት ህወሓቶች ሊደርሱበት የማይችሉ እንዲሆን አድርጎታል። አሁንም በስተመጨረሻው የኢህአዴግ ፓርቲዎች ተሰባስበው (ህወሓትንም ጨምሮ) የወሰኑትን የውህደት ሃሳብ ህወሓቶች ለመቀበል አቅቷቸው እዚህ ግባ የማይባል ምክንያቶች እየደረደሩ ይገኛሉ።
ሦስቱ እህት ፓርቲዎች ከአምስቱ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ኢህአዴግን ወደ መቃብር ልከው በአዲስ ፓርቲና መርሃ ግብር ወደ ምርጫው ይገባሉ። ህወሓት “ኢህአዴግ አይፈርሰም” ብትልም በፖለቲካዊ አካሄድም ሆነ በሕግ ማስቆም ግን በፍጹም የማትችልበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች።
ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት/ትህነግ) በማለት የሚጠራውና እስካሁን በዓለምአቀፍ የአሸባሪዎች የመረጃ ቋት በአሸባሪነት ተመዝግቦ የሚገኘው ትህነግ/ህወሓት በኢትዮጵያ እጅግ አስከፊ የሚባልና ትውልድን ያወደመ ርዕዮት በመከተል አገር ያፈረሰው የተገንጣዮች ጥርቅም እንደሆነ ይታወቃል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው።
Leave a Reply