በተለይ ምዕራብ ወለጋን ምሽጉ አድርጎ ከትህነግ ጋር በመሆን ንጹሐንን እየጨፈጨፈ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክረው ሸኔ ጠንካራ ይዞታዎቹን እያጣ መሆኑ ተነገረ። ሸኔን የማጽዳት ዘመቻው ወደ ፖለቲካውና መንግሥታዊ መዋቅሩም ውስጥ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
ጎልጉል ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ በተጠናከረ ሁኔታ በሸኔ ላይ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ኦነግ ሸኔ ጠንካራ የሚላቸውን ይዞታዎቹን ሳይወድ በግዱ እንዲለቅ እየተደረገ ነው። በተለይ በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ በንጹሐን ወገኖቻችን ላይ አሰቃቂና ለኅሊና የሚሰቀጥጥ ግድያ በፈጸመው ሸኔ ላይ አሁን ዝርዝሩን መናገር የማያስፈልግ ዘመቻ እየተካሄደበት ይገኛል።
በቀጣይ ባሉት ቀናት መንግሥት በይፋ ዝርዝሩን የሚያሳውቅ ቢሆንም ዘመቻው በዋንኛነት ትኩረት ያደረገው የሸኔን ጠንካራ ምሽጎችን መቆጣጠር ሲሆን ሌላው ደግሞ ዋነኛ አመራሮቹን ማስወገድ ነው። ጎልጉል ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ዘመቻው በሁለቱም መስክ ወሳኝ ድሎችን እያስመዘገበ ነው። አሁን መጥቀስ ባያስፈልግም ዘመቻው በከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች እየተመራ መሆኑ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
ይህ በወታደራዊ መስክ እየተገኘ ያለው ድል በወለጋ ብቻ ሳይሆን ለወለጋ ቅርብ በሆኑና በሌሎች ሸኔ ጠንካራ ምሽጎቼ በሚላቸው አካባቢዎች ጭምርም እንደሆነ ታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ ሸኔ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሳይሆን ከትህነግ ጋር ለመሥራት የፈረመ፣ ለዕኩይ ዓላማ የተሰለፈ ጸረ ኦሮሞ መሆኑን ተረድቶ ልጆቹን በማዝመትም ሆነ ሸኔን በመደገፍ እንዳይተባበር በማድረግ ረገድ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ጎልጉል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በሸኔ ላይ የተመዘገበው ድል በወታደራዊ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን ወደ ፖለቲካዊ አመራሩም እንዲዘልቅ የአገር ወዳድ ዜጎች ፍላጎት መሆኑ ታውቋል። ጥያቄያቸው እንዲሰማላቸው የሚፈልጉ ወገኖች እንደሚሉት የሸኔ ስኬት በሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግሥታዊና ክልላዊ መዋቅር ውስጥ ባሉ ከሚያገኘው ድጋፍ መሆኑ ታውቆ ተመሳሳይ የማጽዳት ዘመቻ ከታች እስከላይ እንዲደረግ የዜጎች ጥያቄ መሆኑ ለመረዳት ተችሏል።
በቅርቡ በመንግሥት በኩል ዝርዝሩ የሚገለጽ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
(ፎቶ፤ ለማሳያ የቀረበ)
Leave a Reply