ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተቃጣባትን የህልውና አደጋ ለመመከትና ሀገርን ለማስቀጠል እያንዳንዱ ዜጋ የአርበኝነት ተጋድሎ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለጹ።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተፈጠረ ቡድን በመሆኑ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ ይህንን አሸባሪ ቡድን ግንባር ድረስ ሄዶ ሊፋለመው ይገባል።
አቶ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ከአሸባሪው ሕወሓት ውጪ በዓለም ታሪክ የመራትን ሀገር ለማጥፋት አልሞ የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲ የለም። አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በገሀድ ሀገርን የማፍረስ አላማን አንግቦ ኢትዮጵያን በማፈራረስ ወደ ትናንሽ መንደርነት የመቀየር ፍላጎት አለው።
አቶ ክርስቲያን አሸባሪ ቡድኑ ለህፃናት አረጋውያንና ለደከሙት እንዲሁም ለእንስሳትም ጭምር የማይራራ መሆኑን ገልፀው፤ ቡድኑን ማስወገድ ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል።
አቶ ክርስቲያን ማንኛውም ህብረተሰብ አካባቢውን የመጠበቅ ሞራልያዊ መብት እንዳለው እንደሚያምኑ የጠቆሙ ሲሆን፤ ፓርቲያቸውም በዚህ ሀገርን የማዳን እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ፓርቲያቸው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ለህልውና ዘመቻው መንግሥት ጥሪ ከማቅረቡ በፊት ጀምሮ በራሱ ተነሳሽነት እንደተሳተፈ የጠቆሙት አቶ ክርስቲያን፤ የዞን ከፍተኛ አመራሮቹንም በዘመቻው ከአካል ጉዳት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ከፍለዋል ሲሉ ገልፀዋል።
አቶ ክርስቲያን “ኢትዮጵያ ከትናንት የወሰድናት ብቻ ሳትሆን ለነገው ትውልድ ልንሰጥ በአደራ መልክ የተረከብናት ናትና ትናንት በተረከብንበት መንገድ ሳትጎዳ በተሻለ ቁመና ልናስረክብ ይገባናል፤ ለዚያም አሸባሪውን መዋጋት አለብን” ሲሉም ሀገር የማዳን ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልፀዋል።
አቶ ክርስቲያን መንግሥትን መቃወም ማለት ሀገርን እንዲፈርስ መተው አይደለም ሲሉም መንግሥትን የሚቃወሙና ሕወሓትን ለሚደግፉ ሌሎች አካላት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሀገርን ማዳን ማለትም መንግሥትን መደገፍ ማለት አይደለም፤ መንግሥትን እኛም እንቃወመዋለን፤ ሀገራችንን ግን አናስነካም ሲሉም ገልፀዋል።
አቶ ክርስቲያን መላው ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ የሃይማኖትና የተለያዩ ልዩነቶቻቸውን በመተው ልዩነትን ማስተናገድ የሚቻልባትን ሀገር ለማትረፍ ሁሉም ሀገሩን ለማስቀጠል የአርበኝነት ተጋድሎ ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉም ገልፀዋል። (አዲስ ዘመን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply