“ወይኔ ልጄ፣ እጅ እግሬ ልጄ፣ ወይኔ ልጄ፣ ወዴት ነህ ልጄ፣ የት ላግኝህ ልጄ? እምኑ ጋር ነህ? ልጄ … ልጄ … ልጄ … ልጄ …” ጥቁር ቦርሳቸውን በወገባቸው ተሸክመው፣ ቂሊንጦ እስር ቤት ደጅ የሚያነቡ እናት ለቅሶ!! ሁሉም ያነባሉ። ሁሉም ያለቀሳሉ፣ የሚሰማ ግን የለም። እንደውም “ዘወር በሉ” እየተባሉ ይደገንባቸዋል። “ሊታረሙ በህግ ከለላ ስር ሆነዋል” የተባሉ ወገኖች “ተረሽነዋል” የሚለው አስተሳሰብ እየጠነከረ መጥቷል። ለቤተሰቦቻቸው እንደምን ተቆጥረው ይሁን? ይህ ሁሉ የጭካኔ ግፍ ወዴት ይመራን ይሆን? የብዙዎች ጥያቄና ስጋት ነው። በየሰዓቱ የሚወጡት መረጃዎች ደግሞ ስጋቱን የሚያግሉና ቁጣን የሚቀሰቅሱ ሆነዋል። የህወሃት ሹሞችም “የሆነው ነገር ሁሉ የተከሰተው በዕቅድ አይደለም” ይላሉ፡፡
በአልሞት ባይ ተጋዳነት የሚውተረተረው ህወሃት አሁንም አለሁ ቢልም የቂሊንጦ ጉዳይ ማቆሚያ ላጣው ፈተናው ተጨማሪ ነዳጅ ሆኗል፡፡ ይህ አገራዊ ሃዘን ምናልባትም ህወሃት የራሱን ማክተሚያ እያጣደፈ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የታሳሪ ቤተሰቦች “እስከ አርብ ጠብቁ” ተብለዋል – ከአርብ በፊትስ ምን ታስቧል?
“ህወሃት አብቅቶለታል” በማለት እየተናገሩ ያሉት ምዕራባውያን በተለይም አሜሪካ በህወሃት ላይ ያላትን አቋም ጠበቅ እያደረገች መጥታለች፡፡ ፊት እየዞረባቸው እንደሆነ የተገነዘቡት እነ አባይ ጸሃዬ ጌቶቻቸው ዘንድ ቀርበው በሚችሉት ቋንቋ ኦሮሞና አማራ ተባብረውብናል፤ ሰግተናል በማለት ለሦስት ሳምንት ያህል እየተመላለሱ ቢለምኑም እንደ ቀድሞው የጌቶቻቸውን ይሁንታ ሊያገኙ አልቻሉም። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት ህወሃት የሚመዘው የማደናገሪያ ካርታ ስላለቀበት ትዕዛዝ እንዲቀበል እየተገደደ ነው።
ከእውነታው በተገላቢጦሽ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) አገር እየገዛ እንደሆነ ለማሳመን ቢጥርም አልተሳካለትም። የአገሪቱ በርካታው አካባቢዎች ከቁጥጥሩ ውጪ ሆኗል፡፡ በከመረው እርምና ባፈሰሰው የንጹሃን ደም ህዝብ ፊት ነስቶታል። ሁኔታውን በውል የተረዱት ጌቶቹም እንደቀድሞው ሊጠጋገኑት ከመሞከር ይልቅ ፊታቸውን አዙረውበታል፤ ባደባባይ ሊለዩት ጫፍ ላይ ናቸው። በዚሁ መነሻ እንደ ዱሮው ስብሰባ አይጠራም፤ አይጋበዝም፤ አይፈለግም፡፡ በጎረቤት አገራት በሚካሄዱ ስብሰባዎች እንኳን “አትፈለግም” ተብሏል፡፡ ዥጉርጉር ሚዲያዎች “መንግሥት” እያሉ የሌለውን ወግና ማዕረግ የሰጡት ህወሃት ከትክክለኛ ማንነቱ ጋር የሚመጣጠን ተግባር ላይ የተጠመደውም ለዚሁ እንደሆነ ብዙዎች እየመሰከሩ ነው።
የሌለውን ስብዕና ተጎናጽፎ እመራዋለሁ የሚለው ህዝብ ላይ ጦርነት የሚያውጅ የወንበዴ ቡድን፣ እየዋለ ሲያድር ማንነቱና ለመንግስትነት ወግ ሊበቃ የማይገባው እንደነበር ያረጋገጠው የመለስ ህወሃት፣ የህዝብ ተቃውሞን በጸጋ ተቀበሎ ከማስተናገድ ይልቅ የመረጠው መንገድ እርቃኑን ያወጣው ሲሆን፣ ሰሞኑንን የረሸናቸው ወገኖች ጉዳይ ይህንኑ አውሬነቱን ያመላከተ እንደሆን በውጪም ሆነ ባገር ውስጥ ስምምነት አለ።
ባለፈው ቅዳሜ የበርካታ ወገኖችን ህይወት የቀጠፈው የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ፣ በውስጡ ሌላ እሣት ፈጥሮበታል፡፡ “አንድ ሰው ሞተ” ሲል ጀምሮ 23 የደረሰው የሟቾች ቁጥር እጅግ በርካታዎች እንደሞቱ በውል የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ በራሱ በህወሃት/ኢህአዴግ ሁለት ዜጎች በጥይት ተመትተው መሞታቸው መናገሩ ምን ያህሉ በጥይት ተመትተው ይሆን የሚል ጥያቄ ፈጥሯል፡፡ በ1998 ዓም ላይ “የኦነግ አባላት ናችሁ” በሚል ታስረው የነበሩና “ከቃሊቲ ሊያመልጡ ሲሉ ሰባት ታራሚዎች ተገደሉ” ያለው ህወሃት በኋላ ግን ከ160 የሚበልጡ ታራሚዎች በተተኮሰባቸው ጥይት በግፍ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ቢታሰሩም ድምጻቸው ያልታሰረውና የህወሃትን የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ የጣሉት እነ በቀለ ገርባ የታሰሩበት ቂሊንጦስ? እንዴት ሆኖ ይሆን? አንድ እናት እዚያው ቂሊንጦ ደጅ “ወይኔ ልጄ፣ እጅ እግሬ ልጄ፣ ወይኔ ልጄ፣ ወዴት ነህ ልጄ፣ የት ላግኝህ ልጄ? እምኑ ጋር ነህ? ልጄ … ልጄ … ልጄ … ልጄ …” እያሉ ያነቡ ነበር። የእናት አንጀት!!
ከእሣቱ በፊት 45 ደቂቃ የወሰደ የቀለጠ የተኩስ ድምጽ መሰማቱ፣ እሣት አደጋ መከላከያ እሣቱን ለማጥፋት በቦታው የተገኘበት ሰዓት፣ እሳቱ የተነሳበት ቦታ የት እንደሆነ በውል አለመነገሩና በህወሃት/ኢህአዴግ ሹሞችና አፍቃሪዎች የሚነገረው የተምታታ መሆኑ፣ እሣቱን ያስነሳው ምን እንደሆነና ያስነሳው ማን እንደሆነ ከህወሃት በኩል የሚጣረስ መረጃ መሰጠቱ፣ ሐኪሞች የሟቾች ቁጥር 60 እንደሆነ መናገራቸውና የግለሰቦቹን ማንነታቸውን እንዳይለዩ በአስከሬን ላይ ቁጥር እንዲጠቀሙ መታዘዛቸው … ከዚህ አልፎ ደግሞ ከአገዛዙ የሚሰጠው መረጃ እርስበርሱ የሚጋጭ መሆኑ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ከፍተኛ አመራር “ይህ ሁኔታ በራሱ የሟቾቹን ማንነት ለመደበቅ ሆን ተብሎ እየተቀናበረ ያለ ሤራ እንዳለ አመላካች ነው” ብለዋል፡፡ ቪኦኤ ያነጋገራቸው ቤተሰቦች “እስከ አርብ ጠብቁ” መባላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከአርብ በፊትስ የታሰበው ነገር ምን ይሆን?
በቂሊንጦ የተሰዉትን ስም ህወሃት ይፋ እንዲያደርግ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና እና ሚዲያው አስጨንቀው መያዛቸው ጎልጉል ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ አንጻር በተደጋጋሚ የእስረኞቹ ማንነት እንዲናገሩ ጥያቄው ከቀረበባቸው ከፍተኛ የህወሃት ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የማውቀው ነገር የለኝም፤ ሆኖም ግን የተከሰተው ነገር ሁሉ በዕቅድ የተደረገ አይደለም፤ ሆን ተብሎ የተከናወነ ድርጊት አይደለም በማለት ማስተባቤ መስጠታቸው የሟቾቹን ማንነት ከፍተኛ ጥርጣሬ ላይ የጣለ አድርጎታል፡፡
የተከሰተው ቃጠሎ ነው፤ የፈረሰና የተቆለለ ክምር የለም፤ ከፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን የማውጣት ሥራ አይደረግ፤ … የሞቱት ሰዎች ማንነት በቃጠሎው አልጠፋ፤ ታዲያ ለምን ይሆን ቤተሰብ እንዲህ የሚንገላታው? “እናቶች ልጆቻቸውን ፍለጋ ወገባቸውን በመቀነት አስረው በጉልበታቸው እየሄዱ” እንደሆነ ትላንት የተሰራጨው የቪኦኤ ዘገባ ላይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የወጣቶች ክፍል ኃላፊ አቶ ጉርሜሳ አያና ባለቤት ወ/ሮ ዐይናለም ደበላ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸውም እንደሌሎቹ የባለቤታቸውን መኖር በተመለከተ እስከ አርብ ጠብቁ ተብለው ጭንቅ ውስጥ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ወገኖች ሌላ ህወሃት በግፍ በሚገዛት ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ ዜጎች በየቀኑ እየተገደሉ፣ እየተሰወሩ፣ እየተሰቃዩ፣ … ይገኛሉ፡፡ መኖራቸው የማይታወቅ፣ የሚጮህላቸው ወገን የሌላቸው፣ የሚዲያ ሽፋን የማያገኙ፣ … የእነዚህስ ቤተሰቦችና ወገኖች እስከመቼ ይሆን የሚጠብቁት?
“ልጅን ያህል ነገር ያለበትን ሳላውቅ እንዴት ዝም ልበል?” ያሉትን የዮናታን ተስፋዬን እናት ወ/ሮ ሙጪት ተካን ጨምሮ የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወ/ሮ ሃና እና ልጃቸው ወ/ት ቦንቱ በቀለ፣ የአቶ ደጀኔ ጣፋ ባለቤት ወ/ሮ አሰለፈች ሙላትና የመኢአድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ አሰጋ አሰፋ ልጅ ወ/ት ህይወት አሰፋ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አለማወቃቸው ጭንቀት ውስጥ እንደከተታቸው ለአሜሪካ ድምፅ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በግፍ መታሰራቸው፣ በየቀኑ ግፍ መቀበላቸው፣ መንገላታቸው ሳያንስ አሁን ደግሞ “ንገሩን” እያሉ የሲቃ ድምጽ እያሰሙ ነው፡፡ ቀን አልፎ ቀን እየተተካ መሄዱ በራሱ የግፉዓኑን በሕይወት መኖር ጥርጣሬ ላይ እየጣለው መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቃጠሎው የዓለምአቀፉን ሚዲያ ትኩረት መሳቡ በህወሃት ላይ ከፍተኛ ጫና እያመጣ ነው፡፡ “አብቅቶልሃል” ባሉት አንጋሾቹ ዘንድ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ብዙም የሚወደድ ባለመሆኑ ህወሃትን ውጥረት ውስጥ ከቶታል። ዜጎችን በግፍ እየጨፈጨፈ ያለው ህወሃት ከአንጋሾቹ ጋር ፍጥጫ ውስጥ በመግባቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ነገር “ስሉሱ” የዞረ መሆኑን የሚያመካልት ሆንዋል።
እየተገደሉ ያሉትን ዜጎች በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ቡድን ህወሃት/ኢህአዴግ በሩን መክፈት እንዳለበት አክርረው የተናገሩት ሳማንታ ፓወር ህወሃት ዜጎችን እየፈጀ መሆኑን ሲናገሩ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የጸጥታ ኃይላት “ከልክ ያለፈ ኃይል” መጠቀማቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ የሁልጊዜ የፖለቲካ ወዳጅ ከሌላት አሜሪካ እንዲህ ያለ የከረረ ነገር መስማት የማይወደው ህወሃት በቂሊንጦ ጉዳይ ውሳኔውን ይፋ ለማድረግ መስማማት አቅቶታል፡፡ ይህም ከአንጋሾቹና ከዓለምአቀፍ ሚዲያ ከሚመጣው ተጽዕኖ ጋር ተዳምሮ ኅልውናውን የሚፈትንበት ሰዓት ላይ አድርሶታል፡፡ “እስከ አርብ ጠብቁ” ብሏል!
ሰሞኑን የቀድሞው የበረሃ ጓድ እና የድል ተካፋይ ታምራት ላይኔ ከኤስቢኤስ ሬዲዮ ጋር በሁለት ክፍል ባደረጉት ቃለምልልስ የቀድሞ ጓዶቻቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው በርካታ ምክር ሰጥተዋል፡፡ የወቅቱን የሕዝቡ ጥያቄ “በምን ዓይነት መልኩ እንፍታው በሚለው ጥያቄ ላይ የኢህአዴግ መሪ አካላት (ህወሃትን ማለታቸው ነው) ወታደራዊውና ሲቪል መሪዎች በጉዳዩ ላይ አንድ ቁመና ይዘው የማይገኙበት ሁኔታ ይፈጥራል፤ … ቅራኔው ስለተባባሰ በዚህ እንሂድ ወይስ በዚያ እንሂድ በሚለው ጉዳይ ላይ” የማይቀር ክፍፍል እንደሚከሰት ተናግረው ነበር፡፡ የቂሊንጦ ሟቾችን በተመለከተስ? የሟቾችን ማንነት ይፋ ከማድረግ ጋር የተፈጠረ ነገር ይኖር ይሆን? ስምምነት ወይስ መለያየት? ከአርብ በፊት የታሰበውስ ምንድነው? አንዳንድ “ታማኝ ጋዜጠኞች” በፌስቡክ ገጻቸው “የሟቾች ስም ዝርዝር ሃሙስ ይለጠፋል” እያሉ ነው። የሰው ልጅ ሞት እንደ ኮንዶሚኒየም ወይም እንደ ትምህርት ፈተና ውጤት ወይም “ስማቸው ይለጠፋል” ማለት ሰብዕና የሌለው ህወሃት ራሱ የሚመልሰው እንኳን አይደለም፡፡ ውዶቻቸው የሞቱባቸውና ያልሞቱባቸው እንደ ሎተሪ ዕጣ ነገ ስማቸው ሲለጠፍ ያያሉ፤ ለመሆኑ የህወሃት ግፍና የጭከና መጠን የሚለካበት ገደብ ይኖር ይሆን? ጉዳዩ የታዋቂ ፖለቲከኞች ጉዳይ ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ የማንም ህይወትስ ቢሆን እንዴት “የስም ዝርዝር ይለጠፋል” ይባላል?
በተመሳሳይ የቂሊንጦ እስር ቤት የተፈጸመውን አሳዛኝ ትራጀዲ አዲስ ስታንዳርድ (addis standard) ሲዘግብ “እስረኞች ሲረሸኑ አየሁ” ያለ እማኝ ጠቅሶ ጽፏል። ቃጠሎው ሲደርስ በቂሊንጦ እስር ቤት ጥበቃ ላይ የነበረ የዓይን እማኝ ጠቅሶ የሚሰቀጥጥ መረጃ ያስነበበው አዲስ ስታንዳርድ እስረኞች ላይ ጥይት መርከፈከፉን አርጋግጧል። እንደ ዘገባው ከሆነ የጥበቃ ሰራተኛው ማንነቱ እንዳይጠቀስ ጠይቆ፣ ቂሊንጦ እስር ቤት ሰራተኛ መሆኑንን የሚያረጋግጥ የስራ መታወቂያውን አያይዞ ነው እልቂቱን በኢሜይል ያጋለጠው።
የዓይን ምስክሩ እንዳለው እሳቱ እንደተነሳ 5 እስረኞች ከሁለት ማማ ላይ በተቀመጡ ጠባቂዎች ተገድለዋል። እሳቱን ለማጥፋት ሲረባረቡ የነበሩ እስረኞች ላይ የጥይት እሩምታ ሲወርድባቸውም ተመልክቷል። የ18 እስረኞች አስከሬን ከእስር ቤቱ ሲወጣ ማየቱን የተናገረው የዓይን እማኝ፣ ሁሉም በጥይት መገደላቸውንና እሳት የሚባል ነገር እንዳልነካቸው ያየውን መስክሯል። የእማኙ ገለጻ በቂሊንጦ እስር ቤት ታሳሪዎች “በጅምላ ተጨፍጭፈዋል” የሚለውን ዜና ያጠናክረዋል።
በፋሽስት የሚመሰለው ህወሃት “ለማምለጥ የሞከሩ” ሲል የጠራቸው ሁለት እስረኞች በጥይት መገደላቸውን፣ 21 ደግሞ እሳትና ጭስ ተባብረው እንደገደሏቸው የፋሽስት ልሳን የሆነው ራዲዮ ፋና መዘገቡ አይዘነጋም። “የእርም ሽንት፣ የባንዳ ዘር ፍሬ” የሚባለው ፋና የፊታችን ዓርብ ውይም ሐሙስ ደግሞ ምን እንደሚል ይጠበቃል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply