በምርጫ 1997 ማግስት የአደባባይ አመፆች ተበራክተው ነበር፡፡ በጥቅምት 24፣ 1998 አዲስ አበባ በሕዝባዊ አመፅ ስትናወጥ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥም ሊሰጠው ይገባው የነበረውን ያክል ትኩረት ሳያገኝ ያለፈ ትራጄዲ ተከስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ እልፍ በኦ.ነ.ግ. ሥም ተወንጅለው የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች የቃሊቲ ግቢ ውስጥ ታጉረው ነበር፡፡ ታዲያ ግቢው ውስጥ በተፈጠረው ግርግር ‹ሊያመልጡ ሞክረዋል› በሚል 163 የሚደርሱ ታራሚዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸውን አጥተው ነበር፤ መንግሥት የሟቾቹ ቁጥር ዐሥር እንኳን እንደሚሞላ አላመነም ነበር፡፡
‹ሻዕቢያ› በቂሊንጦ እና ቃሊቲ ወኅኒ ቤቶች እጅግ ዝነኛ ሥም ነው፡፡ ‹ሻዕቢያ› በሚባል ቅፅል ሥም የሚጠራው የዋርድያዎች ኃላፊ፣ በቂሊንጦ የሚገኙ ተመላላሽ እስረኞች በፍርሐት ይርዱለታል፡፡ ‹ሻዕቢያ› ከ1998ቱ የቃሊቲ እስረኞች እልቂት ጋር ሥሙ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በወቅቱ የተነሳውን ግርግር ተከትሎ አግድም በመተኮስ ለብዙ እስረኞች እልቂት ምክንያት የሆነው ይኸው ‹ሻዕቢያ› የተባለ ግለሰብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ቃሊቲ እስር ላይ የነበሩ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ ሊፈቱ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ሰዎች ሳይቀሩ ክፍላቸው በተቀመጡበት ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አግድም የተተኮሰው ጥይት ክፍላቸው ውስጥ አርፈው የተቀመጡትን እስረኞች የወኅኒውን የቆርቆሮ ግድግዳዎች እየበሳ በተቀመጡበት ጭንቅላታቸውን ስለመታቸው ነው፡፡ (‹ሻዕቢያ› በዚህ ዓመት አጋማሽ በከባድ የውንብድና ወንጀል ተጠርጥሮ ከሥራ ታግዷል)
ይህ በሆነ ማግስት እና በተከታዩ ሳምንት የቤተሰብ መጠየቂያው አጥር የቀብር ቦታ ይመስል እንደነበር በወቅቱ እዚያ የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ እስረኛ ቤተሰብ የነበረው ሰው ሁሉ ይመጣና ‹እከሌን አስጠሩልኝ› ሲል የሞት መርዶ ይመለስለት እና ‹ዋይታ› መጠየቂያውን ቦታ ያጥለቀልቀው እንደነበር በሐዘን ያስታውሳሉ፡፡
‹ዋይታ› ራሱን ደገመ!
ዛሬ (ነሐሴ 29፣ 2008) ቂሊንጦ የታሰሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሊጠይቁ የሔዱ ሰዎች እስረኞቹ ሁሉ የሉም የሚል መልስ እየተሰጣቸው በዋይታ እና ለቅሶ እየታጠቡ ግማሾቹ ተስፋ ባለመቁረጥ እዚያው አካባቢ በፖሊስ እየተዋከቡ ሲቆዩ፣ ቀሪዎቹ መሔጃ በማጣት እና በተስፋ መቁረጥ ወደቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መንስዔ ትላንት በወኅኒው ግቢ የተነሳው ከፍተኛ የእሳት አደጋ ነው፡፡
ቅዳሜ (ነሐሴ 28 ቀን 2008) ጠዋት 2፡30 ጀምሮ እስከ 10፡00 ሰዐት ድረስ ቂሊንጦ የሚገኘው ‹በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የአዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ› በእሳት ተያይዞ ሲነድ እና ከባድ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ውሏል፡፡ በወቅቱ የተነሱ የምስል ማስረጃዎች እደሚያረጋግጡት እና በወቅቱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች እንዳስረዱት እሳቱ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ሲነድ እና ከውስጥ የፍንዳታ ጩኸትም ይሰማ እንደነበር፣ ጭሱ እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀት ላይ ሲታይ እንደነበር ነው፡፡
የአደጋው ሪፖርት
የእሳት አደጋው ሲደርስ በእስረኞች ማቆያ አካባቢው የነበሩ የእስረኛ ቤተሰቦች እና ታዛቢዎች እሳቱ የተነሳው የቤተሰብ መጠየቂያ ሰዐት ከመድረሱ በፊት እንደነበር እና ጭሱ ጎልቶ መታየት ከመጀመሩ በፊት የማረሚያ ፖሊሶች ከቦታው እንዳስለቀቋቸው ይናገራሉ፡፡ ማምሻውን የኦሮሞ መብት ተከራካሪው ጃዋር መሐመድ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ‹22 የታሸጉ አስከሬኖችን ከቂሊንጦ ወኅኒ እንደተረከበ እና አስከሬኖቹ በወታደር እየተጠበቁ እንደሆነ› መረጃ እንደደረሰው ዘግቧል፡፡ ለአደጋው ሽፋን የሰጠው የበይነ-መረቡ ሬድዮ ዋዜማ በበኩሉ አካባቢው ላይ ከነበሩ የዓይን እማኞች አገኘሁ ያለውን መረጃ ጠቅሶ የማረሚያ ፖሊሶች ከመጠበቂያ ማማ ላይ ሆነው ወደ እስረኞች ሲተኩሱ እንደነበር ዘግቧል፡፡
የቂሊንጦ ወኅኒ ቤት ገጽታ
ቂሊንጦ የሚገኘው የአዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በእስር ላይ ሆነው የሚከታተሉ 3,100 በላይ የሚሆኑ ወንድ እስረኞች የሚገኙበት ሲሆን፣ በአራት ዞኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ ከአራቱ ዞኖች መካከል ሦስቱ እያንዳንዳቸው ለእስረኞች የትኩስ መጠጥ አገልግሎት የሚሰጡበት አነስተኛ ካፌ ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህ ካፌዎች ለማብሰል (ለማፍላት) የሚጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ዞን 4 በቅጣት ምክንያት ከሌሎች እስረኞች እዲገለሉ የተወሰነባቸው እስረኞችን ማቆያ ነው፡፡ በዚህ ዞን ውስጥ ካፌ የለም፡፡ ዞን 1፣ 2 እና 3 እያንዳንዳቸው 130 የሚጠጉ እስረኞችን የሚያሳድሩ ስምንት-ስምንት ክፍሎች ሲኖሯቸው፣ ዞን 4 ውስጥ ሁለት የእስረኛ ማቆያ ቤቶች ይገኛሉ፡፡
እስር ቤቱ በቀን ሦስት ግዜ ለእስረኞች ምግብ ያቀርባል፡፡ ይህ ምግብ የሚበስለው በተለምዶ እስረኞች ሜንሲ ቤት ብለው የሚጠሩት ከዞኖቹ ተገልሎ ካለ ቦታ ሲሆን ምግብ የሚታደልበት ሰዓት ሲደርስ ከየቤቶቹ ውስጥ በወር አነስተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው በተለምዶ ሰፌድ እና ጎላ ሠራተኞች ተብለው የሚጠሩ እስረኞች ሜንሲ ቤት ድረስ በመሔድ ምግቡን እስረኞች ክፍል ድረስ ተሸክመው ያመጣሉ፡፡
እስር ቤቱ ውስጥ ሲጋራን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ሆኖም ሱስ ያለባቸው እስረኞች በዋነኝነት ከማረሚያ ፖሊሶች ጋር በመመሳጠር ሲጋራና አጤፋሪስን የመሳሰሉ አደንዛዥ ዕፆች አስገብተው ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህን ዕፆችን በእስር ቤቱ ውስጥ ለማስገባት እና ለማከፋፈል በአንዳንድ እስረኞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የቡድን ፀብ የሚያስነሳ ፉክክር የሚካሔድ ሲሆን ከኮንትሮባንድ ንግዱም የሚገኘው ገቢ እጅግ ከፍተኛ ነው (የአንድ ኒያላ ሲጋራ ዋጋ ቢያንስ 20 ብር ነው)፡፡
ዕፅ ለማጨስ መለኮሻ የሚሆን እሳት ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ስላለ፣ የተለያዩ አልባሳትን ቀዶ በመግመድ ወይንም ለመተኛ ከሚገለገሉበት ፍራሽ ስፖንጅ በመቅደድ እና በማያያዝ አንዴ የተገኘውን እሳት ለቀናት ሳይጠፋ ያቆዩታል፡፡
በአሁኑ ወቅት እስር ቤቱ ውስጥ በመላው ኦሮሚያ እየተካሔደ ካለው የፀረ-አምባገነን ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታስረው የሽብር ክስ የተመሠረተባቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ እና የመብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ፣ የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ሽፈራው እና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የነበሩ ሌሎች ወጣቶች፣ በሚያዝያ 2006 የታሰሩት ኦሮሞ ተማሪዎች እና ወደኤርትራ ሊኮበልሉ ሲሉ ተያዙ የተባሉት የአየር ኃይል ጓዶች (በእነመቶ አለቃ ማስረሻ መዝገብ) እንዲሁም ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ፡፡
በቃጠሎውና በተኩሱ ምክንያት የተጎዱ እስረኞች ቁጥር ስንት እንደሆነና ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች ማንነት ባለመገለጹ ምክንያት፣ እንዲሁም እስረኞቹ ወደሌላ ወኅኒ ቤት ተዛውረዋል በሚል ቤተሰቦች የዘመዶቻቸውን ደኅንነት ባለማረጋገጣቸው በእስር ቤቱ ውስጥ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል፡፡ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የደረሰ ጉዳት ካለ ወይንም ስለ ደኅንነታቸው ማረጋገጫ መንግሥት የማይሰጥ ከሆነ ከፍተኛ አፀፋዊ የሕዝባዊ የአመፅ እርምጃ እንደሚወስዱ የኦሮሞ መብት አራማጆች ትላንት ማምሻውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
እያገባደድን ባለው ዓመት ሕዳር 21 ቀን በጎንደር በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ እሳት17 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
(አርታኢ፤ በፍቃዱ ኃይሉ)
Leave a Reply