ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተግባራት ገምግሟል፡፡ የዕዙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅድ በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ በደብረ ብርሃን፣ በላሊበላ፣ በጎንደርና በሸዋ ሮቢት አካባቢ የተሰባሰበውን በዘረፋ እና በጥፋት የተሰማራ ቡድን በመምታትና ከተሞቹን ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ነበር። እነዚህ አካባቢዎች የተመረጡት ብዙ ሕዝብ የሚኖርባቸው፣ ከፍተኛ የንግድና የቱሪስት እንቅስቃሴ ያለባቸው፣ የፖለቲካና የኢንዱስትሪ ማዕከላት በመሆናቸው ነው።
በዚህ መሠረት በስድስቱ ከተሞች ዙሪያ የመጣው የጥፋት ቡድን መሣሪያውን እንዲያስረክብና እጁን እንዲሰጥ የተሰጠውን ዕድል ባለመጠቀሙ እርምጃ ተወስዶበታል፣ የሕግ የበላይነትም እንዲከበር ተደርጓል። የክልሉ ሕዝብ በዚህ ዘራፊ ቡድኑ የተማረረ በመሆኑ፣ የህግ አስካባሪ አካላት ተልዕኮዋቸውን በስኬት እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍ አድርጓል። ጠቅላይ መመሪያ እዙም የክልሉ ህዝብ ላደረገለት ትብብር ምስጋናውን ያቀርባል።
በአሁኑ ሰዓት ከተሞቹ ከዘረፊዉ መንጋ ስጋት ነጻ ሆነዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት በየሥርቻው የተራረፈውን ዘራፊ በማጽዳት ላይ ናቸው። ማኅበረሰቡም መረጃ በመስጠት፣ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ ለዚህ ስራ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ሽንፈት የተከናነበው የፅንፈኞች ቡድን በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ቅርስ ቦታዎችና የእምነት ተቋማት በመግባት ለመደበቅ እየሞከረ ነው።
የመከላከያ ሠራዊቱ እና የክልሉ ህግ አስከባሪ አካላት ህግ፣ ሥርዓትና ሞራልን ባከበረ መንገድ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛል። በቀጣይም የመጨረሻውን የማጽዳት እና የመልቀም ተግባር በማከናወን ከተሞቹ በአጭር ጊዜ ወደ ተሟላ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ይደረጋል።
በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የጠቅላይ መምሪያ ዕዙ እስካሁን 14 ተጠርጣሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን ወደፊትም እንደሁኔታው በቁጥጥር ሥር የሚያውላቸውን ግለሰቦች አስመልክቶ አስፈላጊውን መረጃ ለህዝብ ይፋ ያደርጋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ዕቅድ የተያዘው ከተሞቹን ከዘራፊ የጥፋት ቡድን የማጽዳቱ ተግባር እየተጠናቀቀ በመሆኑ፣
1. ከሐሙስ ነሐሴ 4 ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች መደበኛ የአውሮፕላን በረራ ይጀመራል፤
2. ከባጃጅና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም ዓይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ አገልግሎት ይገባሉ፤
3. የመንግሥት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ፣ ወዘተ. ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል።
በዚሁ አጋጣሚ የክልሉ ሕዝብ ራሱን ከዘራፊውና ከጽንፈኛው መንጋ በመነጠልና በመከላከል፣ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሰለፍ ላደረገው ተጋድሎ ዕዙ በድጋሚ ምስጋናውን ያቀርባል።
ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓም
አዲስ አበባ
የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ
Leave a Reply