
የኢትዮጵያ ህዝብ በጉያው ተሸሽገው የአሸባሪውን ሀገር የማፈረስ ሴራ እያስፈፀሙ ያሉ የወያኔ ተላላኪዎችን መንጥሮ ማውጣት እንደሚገባው የዲሞክራሲ ተሟጋቹ አቶ ነዓምን ዘለቀ አስታወቁ።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት መስራችና የዲሞክራሲ ተመጓቹ አቶ ነዓምን ዘለቀ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን መለዮ አልብሶ ካሰማራቸው አራዊት መንጋዎች በተጨማሪ በህዝቡ ጉያ ተሸሽገው የሽብር ሥራውን የሚያስፈፅሙ ተላላኪዎችን በስፋት በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።በተለይም በከተሞች አካባቢ በህቡዕ ያደራጃቸው እነዚሁ ፀረ ሰላም ኃይሎች የሃሰት ወሬ በማሰራጨት የህዝቡን ስነልቦና የሚሰርቁ አሉባልታዎችን በማራገብ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ህዝቡ የአሸባሪውን ተላላኪዎች እንቅስቃሴ በንቃት መከታተልና መንጥሮ በማውጣት በህግ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል።
እንደአቶ ነዓምን ገለፃ፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ቆርጦ የተነሳው ይህ ወራሪ ኃይል ከ500 ሺ ያላነሱ ፀረ ህዝብ የሆኑ አራዊት መንጋዎችን በጥላቻና በዘረኝነት መርዞ ንፁሃንን እያስጨፈጨፈ ይገኛል። ከዚህም ባለፈ በየክልሉ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ የክልሉ ተወላጆችን በማደራጀት የህዝቡንና የደህንነት አካላትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን የጥፋት አጀንዳ መዘርጋቱን ነው የተናገሩት።
አሸባሪው ቡድን ደሴ፣ ኮምቦልቻና ጎንደር ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅም እንደነበር አስታውሰው በተለይም ከህዝቡ ጋር አብረው የኖሩ ተላላኪዎችን በመጠቀም ቀላል የማይባል ጥፋት ማድረሱን ጠቁመዋል። “በየከተማው ከውስጥ ሆነው መረጃ የሚሰጡ፤ የሚያስተኩሱ፤ ህዝብን የሚያሸብሩ ከዚያም አልፎ ጎረቤታቸው ላይ ሽጉጥ ያወጡ የእነሱ አባሎች አሉ” ያሉት አቶ ነዓምን በተለይም አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ውድመት ለማስከተል አድብተው እየተጠባበቁ ያሉ ተላላኪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
አሸባሪው ቡድን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በባርነት ለመግዛት ሲል ለዓመታት የራሱን ሰዎች ሲያዘጋጅና ሲያደራጅ መቆየቱን አመልክተው “በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ድብቅ ሴራውን ለሚያስፈፅሙለት የክልሉ ተወላጆች 100 ሺ ጠመንጃ እንዳከፋፈለ እናውቃለን” ብለዋል።በተጨማሪም ከመከላከያ የተባረሩ በጀነራል ማዕረግ ያሉ የወያኔ ቅጥረኞች ሰላማዊ መስለው በየእለቱ መረጃ ከማቀበል ጀምሮ ለአውሬው ቡድን ጥርጊያ መንገድን በማበጀት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በተለይም በሰሜን እዝ ላይ ከተደረገው አራዊታዊ ጥቃት ተከትሎ በህቡዕ ያደራጀው የወያኔ ወኪሎች ለሀገር ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመሆናቸው ህዝቡ ያለአንዳች ይሉኝታ መንጥሮ ማውጣት አለበት ብለዋል። “እነሱን በጉያችን አኑረን የደህንነት ስጋት ውስጥ መግባት የለብንም” በማለት ተናግረውም፤ ወያኔ በለስ ቀንቶት ደብረ ብርሃን ከደረሰ አዲስ ከተማ ውስጥ አድብቶ በመጠባበቅ ላይ ያለው ተላላኪ ሀገር የማፍረስ ሴራውን እውን ሊያደርጉት የሚችሉበት እድል እንዳለ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
“ቡድኑ ንፁሃንን ሊያርድ፤ ደካሞችን ሊገድል፤ ሴቶችን ሊደፍር የሚመጣ ሰው መሳይ አራዊት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፤ በመሆኑም ድምፃቸውን አጥፍተው በየቦታው የተሰገሰጉ የእነሱን ደጋፊዎች በንቃት መጠበቅ ይገባል” ብለዋል። በተለይም በየአካባቢው ያለው ኢትዮጵያዊ ወጣት ተደራጅቶ በጥንቃቄ ህዝቡን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
መንግሥትም ህዝቡን በማደራጀትና በማስታጠቅ ራሱንና አገሩን እንዲጠብቅ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አመልክተዋል። “በዚህ መካከል ንፁሃና ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል” ያሉት አቶ ነዓምን “በግልፅ አሁንም ጭምር እነሱን የሚደግፉ፤ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ቡድኑን የሚጠባበቁ ፤ በየቦታው በውስኪ የሚጨፍሩ እንዳሉ ይታወቃሉ። የመመንጠር ሥራችን ከእነሱ ሊጀምር ይገባል” በማለት አስገንዝበዋል። (አዲስ ዘመን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Ethiopia tashenfalch