ፖሊስ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ባደረገው ክትትል ግምቱ 150 ሺህ ብር የሚያወጣን ሞባይል ስልክን ከሌባ ላይ የገዛችን ግለሰብን በቁጥጥር ስር አውሎ ንብረቱን ማስመለሱን አስታወቀ፡፡ ግለሰቧ ከወንጀለኞች በተለያየ ጊዜ የገዛቻቸው ልዩ ልዩ ሞባይል ስልኮችን፣ ላፕቶፖችንና ታብሌት ይዞ ምርመራው መቀጠሉን አዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው አለምነሽ ፕላዛ አካባቢ አንድ ግለሰብ ግምቱ 150 ሺህ ብር የሚያወጣ አይነቱ አይፎን ፕሮ ማክስ ሞባይል ስልክ መቀማታቸውን በቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለአደይ አበባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያመለክታሉ።
የግለሰቡን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ፖሊስ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቴክኖሎጂ በመደገፍ ባደረገው ክትትል የተሰረቀው ስልክ አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ የሞባይል መሸጫ ሱቅ መኖሩ ይረጋገጣል፡፡
ፖሊስ የህግ አግባብን በመከተል ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትእዛዝ በማውጣት ባደረገው ብርበራ ከግለሰቡ ላይ የተቀማውን ስልክ ጨምሮ በልዩ ልዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች የተሰረቁ 85 ስማርት ሞባይል ስልኮችን፣ 4 ለፕቶፖችን፣ 1 ታብሌትና የላፕቶፕ ቦርሳዎችን በኤግዚቢትነት መያዙን የአደይ አበባ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡ የቅሚያ ወንጀል የፈፀመውን ተጠርጣሪ ለመያዝ ክትትሉ መቀጠሉን ከፖሊስ ጣቢያው ከተገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል፡፡
ህጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ የተሰረቁ እቃዎችን የሚገዙ ህገወጦችን በህግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ የህብረተሰቡ መረጃና ጥቆማ ሰጪነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ እና አከራዮችም የሚያከራዩትን ግለሰብ ማንነትና ምን ስራ እንደሚሰራ በማረጋገጥ ራሳቸውን ከወንጀል ተጠያቂነት ሊከላከሉ እንደሚገባ አዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
የሞባይል ስልክ እና ላፕቶፕ ጠፍቶብኛል የሚል ማንኛውም ግለሰብ አደይ አበባ ስቴዲዮም አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል በመቅረብ ሞባይል ስልኩን በመለየትና ትክክለኛ ማስረጃ በማቅረብ ንብረቱን መረከብ እንደሚችል አዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
Misrak Tatek says
አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠዋል ወደ ለብ ቤት ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ቀን ተዘጋጁ አንድ