በአሜሪካ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር መገናኘታቸውን ማምሻው ላይ የኋይት ሃውስ ጽህፈት ቤታቸው ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቋል። በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን የተሃድሶ ጥረት እንደሚያደንቁ ሚስተር ፔንስ ተናግረዋል።
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ በትላንትናው ዕትም ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ ጋር እንደሚገናኙ በዘገበ ወቅት ግንኙነቱ ወሳኝና ጠቃሚ እንደሆነ መጥቀሱ ይታወሳል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ዐቢይ “ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር፣ የንግዱን ማኅበረሰብ ሁኔታ በማሻሻል እና ከኤርትራ ጋር ሰላም በመፍጠር ረገድ” እያካሄዱ ያሉትን ለውጥ በማድነቅ አገራቸው የተሃድሶ ለውጡን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።
ከዚህ ሌላ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ ጋር ተገናኝተዋል። ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ አይ ኤም ኤፍ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከኤርትራ ጋር የደረሱት ስምምነት ለቀጣናው መረጋጋት በማምጣት አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ያለውን ዕምነት ገልጾዋል።
አይ ኤም ኤፍ በነጻ “የሚሰጠው ምሳ” እንደሌለ የሚታወቅ ሲሆን የምዕራባውያን ድርጅቶች አገልጋይ ሎሌ የነበረው ሟቹ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን በነጻ ለዕርድ እንዳቀረበ ይታወሳል። በአስተሳሰብ፣ በዕውቀት፣ በጥበብ፣ በራዕይ፣ በአመለካከት፣ በባህርይና በኢትዮጵያዊነት ፍጹም ልዩ የሆኑትና ለውድድር በማይቀርብበት መልኩ እጅግ የላቁት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ከሚከተሉት አገራዊ መርህ አኳያ ተመሳሳይ ተግባር እንደማይፈጽሙ ይታመናሉ። (ፎቶዎቹ የተወሰዱት ከዕልፍኝ አስከልካዩ አቶ ፍጹም አረጋ የትዊተር ገጽ ነው)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Lusif says
One of my friend who had been angry, upset and frustrated for several years about Ethiopian politics after looking to the pictures above said: he completely is seeing a transformed ( of the previous officials ) human face. Dr. Abiy and his team of change must be miraculous plastic surgeons. This much people are exited. Really funny.
Tesfa says
አማርኛ ቋንቋ ማለፊያ ቋንቋ ነው። እንዳበጁት ይበጃልና። በቅኔም/በግጥም/በወርቅና ሰም/በተረትና ምሳሌ እንዲሁም በሌሎቹ የንግግርና የጽሁፍ ዘይቤዎች ልብን ለማስተንፈስ ይመቻል። ትዝ ከሚለኝ አንድ ልጥቀስ።
ቋት ላይሞላ ነገር ከላይ ታች ይሮጣል
የአንዳንድ ሰው ቆዳ እየለፋ ያልፋል።
(ከፈቃድ ተ/ማሪያም ስራዎች የተወሰደ)
በኑሮ መባከንን በምዕራቡ ዓለም ለምትኖሩ አልነግራችሁም። ያው በሽታ ወደ ሃገር ቤት መጋባቱ ግን ያሳስባል። ጠ/ሚ አብይና አብረዋቸው ወደ አሜሪካ ያቀኑት ልኡካን በሰላም ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው እፎይታ ነው። ይሁን እንጂ በዲሲ/በሎስ አንጀለስ ያዩትን ሚኒሶታ ከገጠማቸው የጠባብ ብሄተኞች የስብስብ ፓለቲካን ሲመለከቱ አብይም ሆነ ለማ ልባቸው ሳይዝን አይቀርም። በመሰረቱ ለአንዲት ሃገር የቆመ ህዝብ ለመሪው የሚያደርገው አቀባበል ሳይሆን “የኦሮሞ ፊስቲቫል” ነበር የሚመስለው። ተልካሾች ዛሬም የሚያስቡት በዚያው በቋንቋቸውና በዘራቸው ዙሪያ ብቻ ነው። እንደመር ያሉ ተገፍተው የኢትዮጵያ ባንዲራ ወደ ዳር ተጥሎ እኛን ብቻ ስሙ የተባለበት መድረክ ነበር። እኔ ይህን ትኢይንት በቴሌቪዝን እየተከታተልኩ አቶ ለማ በአማርኛ ሲናገር በኦሮምኛ እንዲሆን ሲጮሁ መስማት የመደመር ሃሳብ እንደሌላቸው ያመላክታል። በመሰረቱ ዶ/ር አቢይና ለማ ኦሮሞዎች ባይሆኑ ኑሮ ማለትም የሃገሪቱ መሪ ከትግራይ/ከአማራ ክልል/ከአፋር/ከሱማሌ ቢሆን ምን ያደርጉ ነበር ብሎ ማሰብንም ከግምት ማስገባት መልካም ነው። ገና ይቀረናል!
ጠ/ሚ አብይ ሰውን ሁሉ ሃገር ግቡ ማለታቸው ማለፊያ ሆኖ እያለ ለእኔ ግን የሚያሳስቡኝ አያሌ ነገሮች አሉ። በቅርቡ የሃገሪቱን አንጡራ ሃብት የሚፈስበት የዓባይ ግድም ሥራ አስፈጻሚ በጠራራ ጸሃይ በሃገሪቱ መዲና ተገለው ሲገኙ ምን ያህል ሃገሪቱ የወሮበሎች እንደሆነች ያሳያል። እንዴት ይህን ያህል ሃላፊነት የተጣለበት ሰው ያለ ጠባቂ ይንቀሳቀሳል? የሃገር ውስጥ ገዳዮች እንኳን ባይሆኑ የውጭ ጠላቶች ፕሮጀክቱን ለማዳከም የሚፈጽሙት ደባ ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰብ ለምን አልተቻለም። በመሰረቱ ግድያው ሃገር በቀል ነው። ከዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኛ ሞት ጋር ተመሳሳይነትም አለው። ከየአቅጣጫው ወደ ሃገሪቱ ጥሪውን ሰምተው የሚገቡ የተቃዋሚም ሆነ የድሮ ባለስልጣኖች የደህንነት ዋስትና ያሰጋኛል። ከዚህም በዘለለ ጠበንጃ አንግተው ወያኔና ሥራውን ሲጋፈጡ የነበሩ የተናጠልም ሆነ የቡድን ሃይሎች ወያኔ ጥቃት እንዳያደርስባቸው ምን ጥንቃቄ ተደርጓል። ዝም ብሎ እንደመር እያሉ ሰውን አሰባስቦ ለሞት መዳረግም ተገቢ አይደለም። ዛሬ አፍቃሪ ወያኔ በሆኑ ድህረ ገጾች የምናነበው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው። መሰረታዊ ጥንቃቄ ካልተደረገ የማይጠፋ እሳት ሊቀሰቅስ የሚችል ችግር ሊፈጠር ይችላል።
ብሩህ በሆነ መልኩ ጠ/ሚ ሃገርና አንድነትን አስቀድመው በሃገርና በውጭ የሚያደርጉትን ጥረት አደንቃለሁ። በሃገሪቱ የረጅም ጊዜ ታሪክ በባህር ማዶ መሪዎቿ የሃገሬን ሰዎች ከእሥር ፍቱ በማለት ጠበቃ የቆምበት ጊዜ አልነበረም። ጠ/ሚ አብይና ለማ በእውን ለኢትዮጵያ አንድነትና ህብረት እንደቆሙ ምስክር አንሻም። ተግባራቸውና ቃላቸው በቂ ነውና! እኔም ከጎልጉል ድህረ ገጽ ተበድሬ ““ታሪካዊውን የተሃድሶ ጥረት” አደንቃለሁ። በየጊዜው የሚገደሉት ወገኖቻችን ደም ለፍትህ ይጮሃል። ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ!