ከዝግጅት ክፍሉ:- “አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር ተሳነን?“ በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል፤ ሙሉው ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህኛው ክፍል ሁለት ዕትም እርግማን ሁለት “ሚኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ” የሚለው ርዕስ ዳሰናል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃሪሪ ትርጓሜና የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ምስረታ ሂደት የተመዘዙ መንታ ሰበዝ ናቸው፡፡ “ቅኝ ግዛት” vs “አገር ምስረታ፣ ማቅናት/ግንባታ” የሚሉ ተፃራኒ ትርጓሜዎች እንዳሉ ሁሉ፤ “አገር ሻጭ” እና “ባንዳ” የሚሉ የፖለቲካ እርግማኖች የዘመናዊት የኢትዮጵያ የታሪክ ገጽታ አካል ሆነው ቀርበዋል፡፡ ማንነትን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ ባለበት ሁኔታ እነዚህ ብያኔዎች ሊጠፉ የማይችሉ የታሪክ ፍም እሳቶች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ በገዥዉ ኃይል ፊት ታሪክ ትምህርት መሆኑ ቀርቶ ፍርድ ቤት ሆኗል፡፡
አፄ ዮሐንስ አራተኛ ከእርሱ በፊት እንደነበረው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም ሆነ ከኋላው እንደተከተሉት ነገሥታት በሚያሟግት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ያለፈ መሪ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስ ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ምኒልክ ወደስልጣን ለመውጣት ከተጓዘበት የዲፕሎማሲ መንገድ የሚለይ አደለም፡፡ ስልጣን የኃይል ሁሉ ማዕከል በሆነበት ቦታ ገባሪነትን መካድ ለኢትዮጵያ መሳፍንቶች የተለመደ ባህሪ ነበር፡፡ በውጭ ኃይሎች ድጋፍ የጦር መሳርያ አቅምን ማጠናከር፤ ጊዜና ወቅት ጠብቆ ወደ ንግሥና መንበር መውጣት፤ የዮሃንስ እና የምኒልክ መንታ ገፀ-ባህሪያት ናቸው፡፡
አፄ ሚኒሊክ “የጣልያን ተላላኪ ባንዳ ነበር” ማለት የሚቀናቸው የትግራይ ብሔረተኛ ልሂቃን የዮሐንስን የቀደመ የታሪክ እድፍ ተስቷቸው አይጠቅሱትም፡፡ የስዊዝ ሰው የሆነው ሙሲንጀር ፓሻ የጊዜው ያገር ጥናት ተጓዥ መንገደኛ ነበር፡፡ ይህ ሰው በምጽዋና በከረን አመታትን አሳልፈዋል፡፡ የወቅቱ ደጃች ካሳ (ዮሐንስ) እና የእንግሊዞችን ግንኙነት በማቃናት ቀዳሚ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ሰው አገናኝነት ከእንግሊዞች ጋር የተወዳጀዉ ደጃች ካሳ ለናፒየር ጦር የመቅደላ መንገድ ሁነኛ ጠቋሚ ነበር፡፡ ያለ አንዳች ግነት ስለ ሥልጣን ለውጭ ኃይሎች በመታመን (ባንዳ፡- ለባዕድ ሥርዓት ታማኝነትን ማሳየት) አስገባሪውን (አፄ ቴዎድሮስን) በመክዳት ባገኘው የጦር መሳርያ ድጋፍ ታግዞ ወደ ስልጣን የወጣው ቀዳሚው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ መሳፍንቶች ለአብነት በቴዎድሮስ ዘመን እንደ አገው ንጉሴ ያሉ መሳፍንቶች ከውጪ መንግስታት ጋር ቢፃፃፉም በውጭ ሀይሎች የጦር መሳሪያ ድጋፍ ወደ ሥልጣን ለመውጣት የተሳካለት መሳፍንት አልነበረም፡፡ ከዳጃች ካሳ (ዮሐንስ በስተቀር)!!
የአፄ ምኒልክ መንገድ ከዚህ ብዙ የራቀ መሆኑን መካድ ያስተዛዝባል፡፡ የአፄ ምኒልክ እና የጣልያኖች ግንኙነት ከአፄ ዮሐንስ የንግስና ዘመን ይጨምራል፡፡ ሚኒሊክ የዘር ሀረጉን የሚስበው ከአፄ ልብነ ድንግል ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የኃይለ መለኮት ልጅ በመሆኑ የመሀል ኢትዮጵያን ግዛት በመቆጣጠርና የደቡብ እና ምዕራብ ኋላም የምስራቅ ኢትጵያ ግዛቶችን በመጠቅለል ወደ ንጉሠ ነገሥትነቱ የመውጣት ምኞት ነበረው፡፡ ለዚህም ይመስላል አፄ ዮሐንስ ከነገሰበት 1964-1870 ዓ.ም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ለአፄ ዮሐንስ ሳይገብር የሥልጣን ተፎካካሪና የዙፋን ወደረኛ ሆኖ የተቀመጠ፡፡ በነገራችን ላይ በነዚህ ጊዜያት የአፄ ምኒልክ ማኅተም “ንጉሠ ነገሥት” ይል ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የአፄ ዮሐንስ ማኅተም “ንጉሠ ነገሥት” ይል ነበር፡፡ (ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ ተክለ ፃዲቅን፣ ሀሎርድ ማክስን ያጤኗል)
በሁለቱ ወደረኞች ማሀከል የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በውብ ብዕሩ “አንዲቷ ኢትዮጵያ በዮሐንስና በምኒልክ ተከፍላ የሁለት ነገሥታት ሀገር ሆነች፡፡ ሁለቱም በቤገ-ምድርና በጎጃም፣ በወሎ፣ በላስታ አውራጃ ላይ የውስጥ ፍልምያ ሲያሳዩ፤ እንደዚሁም የውጪ መንግስታትን ወዳጅነት አጥብቀው በደብዳቤና በየመልክቶቻቸው አማካኝነት ይሻሙ ነበር፡፡ ሁለቱም የውጭ ሀገር መንግሥታት ወዳጅነት የሚሻሙት አጠገባቸው ባሉት ሀገር ጎብኝና ነጋዴዎች ወይም ምጥዋ በሚቀመጡት ቆሲሎቻቸው ጎን ባላንጣን አስጠልቶ ራስን ለማስወደድ ነው (አፄዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት ፤ ገፅ 57)” ሲል ይገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ወደረኞች መሀል የነበረው የስልጣን ሽኩቻ መጋቢት 14 ቀን 1870 ዓ.ም ልቼ ላይ በምኒልክ ይቅርታ ጠያቂነት ዕርቅ ቢወርድም ተከታዮቹን አስራ አንድ ዓመታት (1871-1881) ምኒልክ የግዛት ወሰኑን ወደ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች በማስፋት የመሬት ይዞታውን (Land power) የግብር መሰብሰብ አቅሙን እና የጦር መሳሪያ ክምችት ሀይሉን በማጠናከር ስራ ተጠምዶ ነበር፡፡ ዓመታዊ ግብሩን በማስገባት ዮሐንስን የሚያዘናጋው ምኒልክ የጦር መሳሪያ ክምችቱና የሰራዊት ብዛት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡
ጣሊያኖች በእንግሊዝ ችሮታ ምፅዋን በቁጥጥር ስር አድርገው ወደ አገር ውስጥ በሚገባ ማንኛውም አይነት እቃ ላይ ተፅኖ ሲያደርጉ አፄ ዮሐንስ የምኒልክ ከጣሊያን ጋር መቀራረብ አልወደደውም ነበር፡፡ የምኒልክ እና የጣልያኖች ወዳጅነት በውጫሌ ውል የወዲያው ግፊት (immediate cause) ሆኖ እስከተፈጠረው የአድዋ ጦርነት ጊዜ ድረስ ቆይቶል፡፡
ጣሊያኖች የወቅቱ ጠላታቸውን አፄ ዮሐንስ እንዲዳከምላቸው አፄ ምኒልክን ለማቅረብ መሞከራቸው የቀኝ ግዛት መሀንዲሶች ዘዴ ይመስላል፡፡ ይህም ሆኖ በርከት ያለ የጦር መሳሪያ ያስታጠኩትን ምኒልክ መጠርጠራቸው አልቀረም፡፡ ይህን ጉዳይ የታሪክ ጸሃፊዉ ፕሮቲ ክሪስ “Empress Taytu and Menilek II” በሚል መጽሀፉ የወቅቱ የጣሊያን መንግስት ወኪል የነበረው አንቶሎኒ በምኒልክ የበዛ መሳሪያ ክምችት ያደረበትን ስጋት ለምኒልክ አንስቶ እንደ ተማፀነው ጽፏል፡፡ ለምኒልክ፣ ለጣይቱ፣ ለራስ ዳርጌና ለአዛዥ ወልደ ፃዲቅ እንዲሁም ለሁለት አስተርጓሚዎች እንደየ ማዕረጋቸው ሥጦታዎችን ካጎረፈ በኋላ ምኒልክ ያገኘውን መሳሪያ ጣሊያኖችን ለመውጋት እንዳይጠቀምበት በክርስቲያናዊ ደንብ መሃላ ይፈፅምለት ዘንድ ተማፅኖ ነበረ (ገፅ 57-8 ይመልከቱ) የውጫሌው ውል ተደራዳሪ እና ፈራሚ የነበረው ጣሊያናዊው አንቶኖሊ እንደሚለው 1880 ዓ.ም ላይ (ከውጫሌ ውል አንድ ዓመት ቀደም ብሎ መሆኑ ልብ ይሏል) ምኒልክ የደቡብ፣ የምዕራብ እና የምስራቅ የኢትዮያ ግዛቶችን ጨምሮ 196,000 (አንድ መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ) ሰራዊት እንደነበረው ሮቢስን “The Attempt to Establish a protectorate over Ethiopia” በሚለው መጽሃፍ (ገፅ 66) ይነግረናል፡፡
በነዚህ ጊዜያት ሁሉ አፄ ዮሐንስ በስም ደረጃ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሰሜን ኢትዮጵያና አካባቢው (ብቻ) የተገደብ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ የአፄ ዮሐንስ የንግሥና ዘመን ፍፃሜ ሦስት አመታት ሲቀረው ሚኒሊክ (የሐር ላይ ባንዴራውን ሲያውለበልብ) በግዛት ወሰን፣ በግብር ማሰሰባሰብ፣ በጦር መሳሪያ ክምችትና በዲፕሎማሲ የበላይበት አፄ ዮሐንስን ይበልጠው ነበር፡፡ የአፄው የንግሥና ዘመን እየተሸረሸረ የመጣ ለመሆኑ ምኒልክ በተለየ ሁኔታ የአስራ አንድ አመታት (1871-1881 ዓ.ም) የሥልጣን ግስጋሴ ይነግረናል፡፡ በነዚህ ጊዜያት አፄ ዮሐንስ የውጭ ኃይሎች ፍልሚያ ቢኖርበትም ምኒልክን ለማስቆም ከቶውንም አልሞከረም፡፡ ይህ ሁኔታ ከማዘንና ከርህራሄ የመጣ ሳይሆን የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የማህበራዊ መሰረት መጥበብ ተከትሎ ከተፈጠረ የአቅም መዛል የመጣ ነበር፡፡
የዛሬዋ ኤርትራ ይህንን ስያሜ ከመያዝዋ በፊት “ባህረ ነጋሽ፣ ምድረ ሌማሴን፣ ከበሳ” በመባል ትጠራ ነበር፡፡ ኤርትራ የሚለው መጠሪያም ሆነ ፖለቲካዊ ቁመና ያገኘችው ጣልያን የቀይ ባህር ጠረፍን ታክካ ወደ አካባቢው መዝለቋ ኋላም መስፋፋቷ ከተመዘገበበት 1879 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ (በተለይም የዘውዴ ረታን፤ የተከስተ ነጋሽን ሥራዎች ያጤኗል) በዚህም ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ነበር፡፡
ከ1864-1881 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ ታላላቅ ጦርነቶች (ተድአሊ፣ ኩፊት፣ ጉራዕ፣ ጉንደት {ጉንዳጉዲ}) ኢትዮጵያ በድል የተወጣችው በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ ወራሪው የግብፅ ኃይል በጉንደት እና በጉራዕ ተከታታይ ሽንፈት፤ ሌላ ጊዜ አውሳ ላይ በአፋሮች እጅ ወድቆ የግብፅ ጦር አፋር በረሃ ላይ የቀረው፤ በአፄ ዮሐንስ የንግስና ጊዜ ነበር፡፡ ጣልያን የአሉላን እጅ የቀመሠበት ውርድት በሮማ ፒያሳ ቺንኮ ቼንቶ (“የአምስት መቶዎች አደባባይ”) በሚል ያስታውሰዋል፡፡ ዮሐንስ በዚህና መሠል ድሎች የታደለ ቢሆንም አገር ውስጥ “የአቻዎች አውራ” በሚል ከያዘው የንጉሠ ነገሥትነት ማዕረግ የተሻገረ በራሱ አቅም የሚቆጣጠረው መሬት ከምኒልክ አንፃር የተዳከመ ነበር፡፡ የውጭ ኃይል ላይ ያስመዘገበው ድልም የግብፅን ጦር ከመጠራረግ ውጪ የጣልያንን ጦር ከምጽዋና ከአሰብ አካባቢ ማራቅ አልቻለም ነበር፡፡ በራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) የተመራው ጦር ዶጋሊ ላይ የጣልያንን ጦር ከመታ በኋላ ሀያ ሦስት ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ማትርቀው ምፅዋ በመሻገር የጣልያንን ጦር ያልወጋበት ሁኔታ በቀጣይ ጊዜያት ጣልያን የዶጋሊን ቁጭቷን በሰሓጢ ላይ (መጋቢት 1880) ያለምንም ወሳኝ ውጊያ ምሽግ ላይ አድፍጦ በመተኮስ የአፄ ዮሐንስ ጦር አታክቶ በመመለሱ ረገድ ተሳከቶለታል፡፡ (ባህሩ ዘውዴን፣ ተክለፃዲቅን፣ ሮሊንስንን…ያጤኗል) ለዲፕሎማሲ ሽፋን ጥለውት የወጡትን ሰሓጢን በኃይል መልሰው ያዙት ዮሐንስ እጁ ላይ የነበሩትን ድሎች መልሰው እንደጉም ይተኑበት እንደነበር የዶጋሊው ጦርነት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ምናልባት የዶጋሊው ድል በመቀጠል ጦሩ ወደ ምፅዋ የማዝመት ሁኔታ ቢኖር ድል ከኢትዮጵያ ጋር መሆን በቻለ ነበር፡፡
ሠላም ያልተገኘባቸው የአፄ ዮሐንስ ድሎች ኤርትራ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ለተስፋፊው የጣልያን ጦር ምቹ ጊዜ እየፈጠሩ እንደነበር ከዶጋሊ ድል በኋላ በአፄው መሪነት ሰማንያ ሺህ ጦር በማዝመት የተሞከረው የሰሓጢ ጦርነት የጣልያንን ይዞታ በማጠናከር የዮሐንስን የድል ተስፋ በማጨለም የተደመደመ መሆኑ ነው፡፡ ሰሓጢ ዮሐንስ ከጣልያኖች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተያየባት የስንብት ቦታ ሆነች፡፡
ዮሐንስ እጅግ በሚያስቆጭ መልኩ መተማ ላይ ሲሰዋ፤ በምፅዋ፣ አሰብ፣ አስመራ፣ ሰሓጢና ቆላማው ክፍል ተወስኖ የነበረው የጣልያን ጦር ያለምንም ጊዜ ማባከን የደጋውን ክፍል ወረረው፡፡ (ዘውዴ ረታን፣ ተክለፃዲቅን፣ ባህሩን … ያጤኗል) ቀደም ሲል በወቅቱ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ፍራንቺስኮ ክርስቲ “ኤርትራ” በሚል የተሰየሙና አካባቢዎችና የደጋውን ክፍል ጠቅልለው ከሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት ነጠሉት፡፡ የዮሐንስ ያልታሰበ ሞት ለምኒልክ የስልጣን በር ሲከፍት ለጣሊያን ጦር “ኤርትራ” የሚል ግዛት እንዲረከብ ዕድል ፈጠረለት፡፡ በተደጋጋሚ ጦርነት የደቀቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦር ከዮሐንስ ሞት በኋላ መበታተን ዕጣ ክፍሉ ሆነ፡፡
እስከዚህ የታሪክ ሂደት ድረስ ምኒልክ በኤርትራ ጉዳይ አንዳች የሚያገባው ነገር አልነበረም፡፡ ጣልያን በቀይ ባህር ዳርቻ የምትቆናጠጥበት ዕድልን ያገኘችው በ1862 ዓ.ም በጣልያናዊው ጂሴፔ ሳፔቶና “ሩባቲኖ” የተባለ የመርከብ ኩባንያ ጋር ተቀናጅተው ከአፋሩ ሱልጣን መሀመድ ሃሰን አሰብን ገዝተው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንኳን ምኒልክ አፄ ዮሐንስም ንጉሠ ነገሥት አልሆነም፡፡ የያኔዋ ኢትዮጵያ በአፄ ተክለጊዮርጊስ ነበር የምትመራው፡፡ የኋላ ኋላ ይህ የግል ይዞታ የነበረው ወደብ ወደ ጣልያን መንግስት ሲጠቃለልም ሆነ እንግሊዝ ከአፄ ዮሐንስ ጋር አድዋ ላይ “የሂወት ውል” እየተባለ የሚጠራውን ስምምነት ስትፈራረም እና እንግሊዝ በሶስት ወራት ልዩነት ስምምነቱን አፍርሳ ነሃሴ 1876 ዓ.ም ምፅዋን ለጣሊያን ስታስረክብ ምኒልክ በደቡብ ዘመቻ እንደተጠመደ ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ 150 ኪ.ሜ በማይሞላ ርቀት መቀሌ ላይ ተቀምጦ ሁኔታውን በቁጭት ያስተውል ነበር፡፡
አፍቃሪ ኢትዮጵያ የሆነው የታሪክ ጸሐፊ ሩቤንስን ከላይ በጠቀስነው መጽሃፉ እንዳለው ዮሐንስ ከእንግሊዝ ጋር ያደረገው “የሂወት ውል” አንድ ደካማ ጠላት (ግብጽ) በሁለት ጠንካራ ባላጋራዎች (የጣልያና የሱዳኑን የማሃዲ ንቅናቄ) መተካት ሆነ፡፡ በሂደት የታየውም እንግሊዝ ውሉን ወደ ጎን ገፍታ ምጽዋን ለጣልያን በመስጠት፤ ለጣልያን ወረራ በር ስትከፍት እስላማዊ ተሃድሶንና የሱዳን ብሄርተኝነትን አዳብለው ለተነሱት መሃዲስቶች ደግሞ በኢትዮጵውያንና በኢትዮጵያ ግዛት ላይ በበቀል ስሜት እንዲዘመቱ አደረጋቸው፡፡
የአፄ ዮሐንስ መካር አልቦ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ (የኃይማኖት ፖሊሲዉን ጨምሮ) እና ህብረት ያልታየበት የመተማ ጦርነት ዘመቻ የራሱን የኢትዮጵያን አንገት አስቆረጠ፡፡ የዮሐንስ የታሪክ ሽንፈቶች ለመከላከል ታጥቀው የተነሱ የትግራይ ዘዉጌ ብሄርተኛ ልሂቃን (ህወሓታዊያንና ዮሃንሳዊያን) የኤርትራን ጉዳይ ከምኒልክ ጋር ያዛምዱቱል፡፡ ህወሓት የበረሃ ማኒፌስቶውን ሳጋና ማገር በምኒልክና በአማራ ጥላቻ ላይ በማቆም፤ ሸዋን የስተቶች ሁሉ ቋት በማድረግ ትግራይን የምሉኼ በኩልሄዎች “አገር” (ልብ አድርጉ “አገር” ነው ያልነው!!) ያደርጋታል፡፡
ድህረ – ደርግን ተከትሎ የታሪክ ቅራኔዎችን በዞረ ድምር ሂሳብ ካላወራረድኩ የሚለዉ ህወሓት፤ በምኒልክ የደቡብ እና ምስራቅ ዘመቻዎች የደረሰውን ጥቃት እያስታወሱ ዛሬም ድረስ ቁጭታቸው ያልበረደላቸውን ዘውጌ ብሄርተኞች እያስተባበሩ በምኒልክ ላይ ፖለቲካዊ እርግማን ማውረድ ሥራቸው አድርገውታል፡፡ መንግስታዊ የመዋቅር ድጋፍ ያለው ይሄው ፖለቲካዊ እርግማን ምኒልክን “ኤርትራን የሸጠ” በሚል ከአድዋ ድል ለመነጠል እስከመሞከር የደረሰ የታሪክ ኑፋቄ ስብከት አደባባዩን ተቆጣጥሮታል፡፡
በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ የሚያስተኩረውን የውጫሌን ውል ለኤርትራ መሸጥ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡ የትግራይ ብሄርተኛ ልሂቃን የዮሐንስ “የሂወት ውል” ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ማስታወስ አይፈልጉም፡፡ ዛሬ ላይ ብርቅ የሆነው የህብረት ስሜት ትላንት በአባቶቻችን አብሮነት (ህብረት) የታየበትን የአድዋን ድል አሳንሶ በማቅረብ የመበሻሸቂያ መድረክ አድርገውታል፡፡
100ኛው የአድዋ ድል በዓል ሲከበር “ድሉ የትግራውያን እንጂ የሌሎች አይደለም” በሚል አይናቸውን በጨው አጥበው በአደባባይ ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ላይ ተገልብጠው “አድዋ ተቀጥላ ድል እንጂ ዋና ዋና ድሎች በአጼ ዮሃንስ ጊዜ የተገኙት ናቸዉ” በማለት (በዘንድሮዉ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ አድዋ ከተማ ተገኝቶ ንግግር ያደረገዉን የትግራይ ክልል ኃላፊ አባይ ወልዱን የንግግር ይዘት ያስታዉሷል) ከታሪክ ጋር መላተማቸዉን ቀጥለዋል፡፡ በአጼ ዮሃንስ የንግስና ጊዜ የተገኙ ድሎችን ከፍ አድርጎ ለማድረግ በምኒልክ መሪነት የተገኘዉን የአድዋን ድል ማሳነስ ምን የሚሉት የታሪክ ድህነት ነዉ? በመሀል ቤት በተለያዩ አመታት በሁሉም አዉደ ዉጊያዎች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ህይወታቸዉ ያለፈ አባቶች ተረስተዋል፡፡ ሥም አልባ ጀግኖች አስታዋሽ የላቸዉም፡፡ ታሪክን በዜግነት ማዕቀፍ ሳይሆን በዘዉግ መነጽር ማየት የሚቀላቸዉ የህወሓት ሰዎች፤ ጊዜና ሁኔታዎች ፈቅደዉ የአድዋ ድል በአጼ ዮሃንስ መሪነት የተገኘ ቢሆን (ኑሮ) ይሄኔ ድሉ በአፍሪካ ደረጃ እንዲከበር የኢትዮጵያን ህዝብ ካዝና ከማራገፍ አልፎ ለክፉ ቀን ያስቀመጡትን የግዙፉን ኤፈርት ትልቅ በጀት ይዞ ለድል መታሰቢያዉ በድምቀት መከበር እንዲቀሳቀስ ባደረጉ ነበር፡፡
ምኒልክ ላይ ፖለቲካዊ እርግማን ማዉረድ የዮሃንስን የታሪክ ሽንፈቶች የሚያጠፋ ይመስል፤ ትዉልድና የታሪክ ትርጓሜ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲፈስ ማድረጉን ተያይዘዉታል፡፡ ይህ የኑፋቄ መንገድ የነገዋን ኢትዮጵያ በተለይም ትግራዋያንን በመነጠል የሚጎዳ እንጂ ምኒልክን የሚያረክስ አይደለም፡፡ ምኒልክ በስጋ ቢሞትም ኢትዮጵያ እስካልተበተነች ድረስ በመንፈስ ይኖራል፡፡ የምኒልክን የአንድነት ስሜት ጊዜና ወቅቱ በሚጠይቀዉ ማህበራዊ ዕድገት መሰረት በመግራት ኢትዮጵያን ወደከፍታዋ ለማዉጣት አቅሙም ፍላጎቱም የሌላቸዉ የህወሓት ሰዎች፤ ከሙት ሥርዓት ጋር ራሳቸዉን እያላተሙ በምኒልክና በዘመኑ ጀግኖች ተጋድሎ የቆመችዉን ኢትዮጵያ መበዝበዛቸዉን ተያይዘዉታል፡፡ የነገሩ ምጸትም ይሄዉ ነዉ፡፡ ምኒልክን እየረገሙ በረከቱን ለብቻ መብላት፡፡
ዶ/ር ዘዉዴ ገብረ ሥላሴ ኦክስፎርድ ዮኒቨርስቲ ባሳተመለት “Yohannes IV of Ethiopia; A political Biography” በሚል ሥራዉ፤ በ1879 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አጼ ዮሃንስ ለምኒልክ በጻፈለት ደብዳቤ “… በእግዚአብሔር ቸርነት ጣሊያኖች ተዋርደዉና ተንቀዉ ይመለሳሉ” (ገጽ፤199 ላይ ይመልከቱ) ብሎት ነበር፡፡ አጼ ዮሃንስ በርግጥ ስለ ጣልያኖች በዓለም ፊት መዋረድና መሸነፍ በትንበያ መልክ የጻፈዉ ደብዳቤ ልክ ነበር፡፡ አጼዉ ባያሳካዉ እንኳ አባ ዳኘዉ መሪነት በዘመኑ የወንድ የሴት አርበኞች ብርታትና የተዋጣለት ቅንጅት ጣሊያንን ድል መንሳት ተችሏል፡፡ በትግረኛ ቋንቋ “ኢይጥዕሞ መዓር…” እንዲሉ የትግራይ ብሄርተኛ ልሂቃን በተለይም የህወሓት ሰዎች፤ የምኒልክና የዘመኑ ጀግኖች ድል አይጥማቸዉም፡፡ ነገሩ ጣማቸዉም አልጣማቸዉም ምኒልክ ከነሰብዓዊ ድክመቱ ዓምዳ ዉዳድ ለኢትዮጵያ (ለኢትዮጵያ መሰረትና ምሰሶ) ነዉ!!
ለመሆኑ አጼ ዮሃንስ ከምኒልክ የተሻለ መሪ ነበር? ታሪኩ ይህን አያረጋግጥም፡፡ የአጼ ዮሃንስ ለባዕድ ሥርዓት (ለእንግሊዝ) የማደግድግ ነገር ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነውና ይህን አንዘረዝርም፡፡ ከ1870-1875 ዓ.ም ድረስ በነበሩ ዓመታት አጼ ዮሃንስ በትግራይ፣ በወሎ፣ በዋጅራቱ፣ በራያና አዘቦ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች በሙሉ በግድ ኦርቶዶክስ ክርስትናን እንዲከቀበሉ “ሰማይ ዓምድ የለዉ፤ እስላም ሀገር የለዉ” የሚል አዋጅ አወጀ፡፡አዋጁ ግልጽ ነዉ፡፡ ክርስትናን ያልተቀበለ የመሬት ባለቤት ሊሆን አይገባም፤ በያኔዋ የኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥም መኖር አይችልም ለማለት ነዉ፡፡ ቀሳዉስትን ከጦር ሠራዊቱ ጋር ይዞ የዘመተዉ አጼ ዮሃንስ፤ በጊዜዉ ያደረሰዉን አጠቃላይ ክስተት በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ የሚገኘዉ “ታሪከ ነገሥት” እንዲህ ይተርክልናል “መከራዉን የፈሩ እስላሞች በልባቸዉ ሳያምኑ ባፋቸዉ ብቻ ‹አምነናል› እያሉ ተጠመቁ፡፡ ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በስዉር ካፋቸዉ እያወጡ እስከ መጣል ደረሱ፡፡ መከራዉን ያልፈሩት እስላሞች ግን ‹ክርስቲያን ከመሆን ሞት ይሻለናል› እያሉ እኩሉ በሞተ፣ እኩሉም በእስራት፣ እኩሉም በመወረስ፣ እኩሉም ካገር እየወጡ በመሰደድ ተቀጡ (ታሪከ ነገሥት፤ገጽ 75 ላይ ይመልከቱ)”፡፡
ከዚህ የማይፋቅ የታሪክ ማስረጃ እንደምንረዳዉ አጼ ዮሃንስ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የከፋ ቅጣት ማድረሱን ነዉ፡፡ የአጼዉ የኃይማኖት ፖሊሲ ጸረ-እስልምና እንደነበር ለንግስት ቪክቶሪያ በላከላት ደብዳቤ ላይ በግልጽ አስቀምጦታል “ባገሬ አዘቦ የሚባል የኦሮሞ እስላም አገር አለ፡፡ ከርሱ ሽፍታ ተነሳብኝ፡፡ እርሱን ለማጥፋት ዘመትሁ፡፡እርሱንም በእግዚአብሔር ኃይል አጠፋሁት” ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ በተፈራረቁ ነገስታት እንደተበደሉ የማይካድ እዉነታ ነዉ፡፡ የአጼ ዮሃንስን ያህል ያስጨነቃቸዉ ንጉሥ ግን ከቶዉንም ያለ አይመስልም፡፡ በሀበሻ ምድር ሙስሊሞችን ብቻ እየለየ እንዲያሳድድ ተፈቶ የተለቀቀ እብድ ዉሻ ይመስል የወሎ ሙስሊሞችን እንዲህ አራቆቷቸዋል “(አጼ ዮሃንስ) አልጠመቅም ያለዉን እስላም ወሎ ከረሙ፡፡ ከእስላም ወገን በኃይማኖቱ የጸናዉና ጉልበት ያለዉ ወደ መተማ እየተሰደደ ከድርቡሽ ጋር ተደባለቀ፡፡ እኩሉም ወደ ሐረርና ቀቤና፣ ወደ ጅማ ተሰደደ፡፡ በዚሁም ምክንያት በያዉራጃዉ ሁሉ ሽፍታ ብቻ ሆነ፡፡ በየጅረቱም ሁሉ መጋደልና የሰዉ ደም መፍሰስ ሆነ (ታሪከ ነገሥት፤ ገጽ 60)”፡፡
የአጼ ዮሃንስ የከረረ የኃይማኖት ፖሊሲ መነሻዉ ግልጽ ይመስላል፡፡ የአጼዉ መሰረት ትግራይ ነዉ፡፡ በትግራይ ዉስን የሠራዊት ኃይል የጊዜዋን ኢትዮጵያ ማስከበር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ወዲህም ለአጼ ቴዎድሮስ የዉድቀት መፋጠን የካህናቱ እጅ እንዳለበት ተረድቷል፤ ኃይማኖታዊ ፖሊሲዉን ተከትሎ ከአዉሮፓ መንግሥታት የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያገኝ አስቦ ነበር፡፡ (ለንግስት ቪክቶሪያና ለንጉሥ ዊልያም አራተኛ እንዲሁም ለፈረንሳይ መንግስት የላከቸውን የደብዳቤ ይዘቶች ያጤኗል) በዉጤቱ ግን ዛሬም ድረስ በዞረ ድምር የታሪክ ቅራኔ ቁስል ያልሻረ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቂምና መሃዲስቶችን በተቀላቀሉ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ትብብር መተማ ላይ በተካሄደዉ ጦርነት የንጉሠ ነገሥትነት ዘመኑን አሳጠረ፡፡ አልፎ ተርፎም የጎንደርና አካባቢዉ ህዝብና ታሪካዊ ቅርሶች ወደሙ፡፡
አጼ ዮሃንስ የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከምኒልክ ጋር አደመብኝ በሚል ለራሱ እንኳን ኋላ ላይ ሲያስበዉ የዘገነነዉን እልቂት በጎጃም ገበሬዎች ላይ ፈጽሟል፡፡ አጼ ዮሃንስ የቅጣት ሰይፉን መዞ ፊቱን ወደ ጎጃም ሲያዞር የጎጃም ገበሬዎች፡-
“በላይኛዉ ጌታ በባልንጀራዎ
በቅዱስ ሚካኤል በባልንጀራዎ
በጽላተ ሙሴ በነጭ አበዛዎ
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ”
የሚል ተማጽኖ ቢያሰሙም ከመዐቱ አልተረፉም፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ “አጤ ምኒልክ” በሚለዉ መጽሃፉ “የትግሬ ወታደር ቄሱን ተበተስኪያን፣ ገበሬዉን ከዱሩ፣ ነጋዴዉን ተመደብሩ እያወጣ ጨረሰዉ (ገጽ፣ 54)”፤ “ጎጃምን የመሰለ ደግ አገርም ሦስት ወር ሙሉ በትግሬ አንበጣ ተደመደመ” (ገጽ፣52) በሚል በወቅቱ የደረሰዉን እልቂትና ዉድመት ይገልጸዋል፡፡ አጼ ዮሃንስ ለራስ ዳርጌ በጻፈዉ ደብዳቤ “በእኔም በድሃዉም ኃጢአት እንደሆን አይታወቅም አገሩን (ጎጃምን) ሳጠፋ ከረምሁ” (ኀሩይ ወልደ ሥላሴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፤ ገጽ 179 ይመልከቱ) በማለት ጸጸቱን ይገልጻል፡፡
በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ሂደት ወስጥ ብዙ ሰብዓዊ ጥፋት እንደደረሰ መካድ አይቻልም፡፡ ነገሥታቱ ከሰብዓዊነት አኳያ “አለማወቅ” የሚባል ሰብዓዊ ጉድለት እንደነበረባቸዉ “ፍትሐ ነገስት”ን በማስታወስ መረዳት አይከብድም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የነገሥታቱ ሠራዊት ይህ ነዉ የሚባል ቋሚ ደመወዝ የሌለዉ በመሆኑ ዘመቻ በወጡ ቁጥር ቅጥ ካጣ ጭካኔቸዉ ጋር የገበሬዉን ንብረት መዝረፍና ማዉደም የሰርክ ተግባራቸዉ ነበር፡፡ በዚህ መሰል አሰቃቂ ሂደት የተጨፈለቁ የማህበረሰብ ክፍሎች፤ ጉዳት የደረሰባቸዉ ወገኖች መኖራቸዉ እሙን ነዉ፡፡ እንደዚህ ባሉ ዘመቻዎች የቀደሙትን ነገሥታት ገትተን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራትች አባቶች የሆኑት የቴዎድሮስ፣ የዮሃንስ እና የምኒልክ ሠራዊት በተፈራራቂነት በገባራቸዉ ላይ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በጊዜ ሂደት መጠኑ እየቀነሰ ቢሄድም ገባሮቹ በባርነት ተፈንግለዋል፡፡ መሬታቸዉንም ተነጥቀዋል፡፡ ባህላዊና ሰብዓዊ ክብራቸዉ የተረገጡም አሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የዚህን ሁሉ ግፍ መደባዊ ይዘት መረዳቱ ላይ ነዉ፡፡
ታሪክን ገልብጦ ማንበብ የሚቀላቸዉ የህወሓት ሰዎች በዘመናዊት ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገር ምስረታ ሂደት ዉስጥ የደረሱ ጥፋቶችን ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ በዳይነት (አማራ) ጋር ብቻ ለማያያዝና ቂምን ወደ ትዉልድ ለማሻገር ሥርዓተ-ትምህርት ከመቀየር ሐዉልት እስከ መስራት ድረስ የዘለቀ እኩይ ድርጊት ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዉጤቱም አገራዊ የጋራ ማንነቶችን (የጋራ ጸጋና መከራዎቻችን፤ ድልና ሽንፈቶቻችን) እየጠፉ አካባቢያዊ ማንነት አለቅጥ ተወጥሯል፡፡ እንዲህ ያለዉ አዝማሚያ መጨረሻዉ አገር በመበተን የሚቆም ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሁኔታችን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበ ሆኗል፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ባህል በአሳዛኝ መልኩ እየበረታ የመጣ ክፉ በሽታ አለ፡፡ እርሱም ኃላፊነት መዉሰድ አለመቻል፡፡ ይህ ክፉ ልማድ ከ1960ዎቹ ትዉልድ የጀመረ ቢሆንም በድህረ-ደርግ በአደባባይ ዘዉጋዊ ልባስ አግኝቶ ማንነትን የታከከ ታሪክ ትርጓሜ ተንተርሶ አገሪቷን ወደ ብተናና እልቂት እየገፋት ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳይ ዛሬ ላይ ከቁጥጥራቸዉ ቢወጣም የህወሓት ሰዎች በተጠና መልኩ ሲተገብሩት የኖሩት ጉዳይ ነዉ፡፡
ለህወሓት ሰዎች ታሪክ ትምህርት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነዉ፤ አንዱን ንጉሥ ኮንነዉ ሌላዉን የሚያጸድቁበት፡፡ ከሦስት አመት በፊት የአጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ቀን የትኛዉም ዩኒቨርስቲም ሆነ እንደ ባህልና ቱሪዝም ያሉ መንግስታዊ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ ሳያከብሩት አልፏል፡፡ አሳፋሪዉ ነገር “የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር”ም የገዥዎችን ቁጣ ፈርቶ ዝምታን መርጦ ማለፉ ነበር፡፡ በጊዜዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (እንደ ሥርዓቷ) ሰማያዊ ፓርቲ በየግላቸዉ አቅማቸዉ በፈቀደ መጠን አክብረዉት ነበር፡፡ በአንጻሩ መጋቢት 2/2009ዓ.ም የትግራይ ክልል ደራሲያን ማህበርና መቀሌ ዩኒቨርስቲ በመተባበር የአጼ ዮሃንስን 128ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ በደመቀ መልኩ አክብረዉታል፡፡ ዮሃንስ ከነሰብዓዊ ጉድለቶቹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር፡፡ በተለያዩ አዉደ ዉጊያዎች ከዉጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በጀግንነት ተፋልሟል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ደንበር ላይ የተዋደቀ ብቸኛዉ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነዉ!! በዚህና መሰል ጉዳዮች ታሪክ ከነድል-ሽንፈቶቹ ሲያሥታዉሰዉ ይኖራል፡፡ጥያቄው ለዮሃንስ የተሰጠዉ ክብር ለምኒልክ ሲሆን ለምን ይነፈጋል? የህወሓትና አክራሪ የትግራይ ብሄርተኞች ዮሐንስ የፈጸመዉን ሰብዓዊ ጥፋት ወደ ጎን ትተዉ በታሪክ ፍርዳቸዉ ነጻ ሊያወጡ ሲሞክሩ፤ ስለ ምኒልክ ለምን የብዜትና ፈጠራ ታሪኮችን በፖለቲካ ርግማን መልኩ ሲያዘንቡ ይታያል? ዮሃንስ በፈጸመዉ ጭፍጨፋ ታሪክ ነጻ ካወጣዉ ምኒልክንስ ታሪክ ስለምን ይኮንነዋል?
ለዚህ ነዉ ለህወሓት ሰዎች ታሪክ ትምህርት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነዉ የምንለዉ፡፡ ዮሃንስን ከፍ አድርጎ ምኒልክ ላይ የፖለቲካ ርግማን የሚያወርድ የመቀሌ ችሎት!! በመስመር መሀል የትግራይ የአካዳሚያ ልሂቃን፣ ህዝባዊ የታሪክ ጸሃፍት፤ የ“አረና ፓርቲ አመራሮች” እና ብዙሃኑ የትግራይ ወጣቶች የመቀሌዉ የታሪክ ፍርድ ችሎት አጨብጫቢዎች መሆናቸዉን ስንታዘብ አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር እንደተሳነን ይገለጽልናል፡፡
የከረረ ዘዉጌ ብሄርተኝነት የክፉ ዉሾች ጉሮኖ ነዉ፡፡ ከታሪክ ዝንባሌ የመነጨ ሲሆን ደግሞ የአሳሞች ጋጥ ይሆናል (የጆርጅ ኦርዌል፤ Animal farm ላይ ያሉትን አሳማዎች ያስታዉሷል) አገራዊ ጅግኖቻችን እያወረድን ዘዉጋዊ ጀግና ማድረጋችንን ከቀጠልን የአድዋ ድል መንፈስ ፍጹም እየራቀን እንጅ እየቀረበን ሊመጣ አይችልም!!
(በቀጣይ ዕትማችን ከአድዋ ድል በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ከአዲሱ የአማራ ዘዉጌ ብሄርተኛ ቡድን ላይ የታዘብናቸዉን እና የጽሁፉን ማጠቃለያ እናቀርባለን)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply