እንደ መግቢያ
በታወቀ ምክንያት የኢትዮጵያ ታሪክ አወዛጋቢነት ቀጥሏል፡፡ “ታሪክ የሞተ ፖለቲካ ነው” የሚለው አባባል ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አይሰራም፡፡ ይልቁንስ “ታሪክ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም ሊቀጥል የሚችል ፖለቲካ ነው” በስሜት በሚነዳ የዘውግ (የዘር፣ የጎሣ) ፖለቲካ ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ባሉ የታሪክ ውርክቦች ውስጥ ይበልጥ አትራፊው ገዥዉ ኃይል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ታሪክ የአሸናፊዎች ደንገ-ጡር በሆነችባት ኢትዮጵያ ገዥው ኃይል ለአገዛዙ በሚያመቸው መልኩ ታሪክን በርዞና ከልሶ ሲያቀርብ ታሪክን ሳያላምጡ የሚመጡ ደቃቅ “ፖለቲከኞች” በርክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ በአጥቂነትና በተከላካይነት የሚበየን የውዝግብ መድረክ ሆኗል፡፡ የአንድ ዘውግ ጉዳይን ሁልግዜ በተጠቂ ስሜት፤ ሌላኛውን ዘውግ በአጥቂነት የማየት ዝንባሌም በታሪክ ትንተና ውስጥ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከታሪካችን የሚያግባባንን ማግኘት ተስኖናል፡፡ ጭራሹን ጉልህ የልዩነታችን መስክ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ከሰሞኑ በምኒልክና በአድዋ ድል ዙሪያ ሶስት ጠርዞች፤ በሁለት ጐራ የተከፈለ ዱላ ቀረሽ “ክርክር” (እንደ እውነቱ “ዘለፋ” ማለት ይቀላል) በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲንፀባረቅ እየተስተዋለ ነው፡፡ የአገራዊ የጋራ ማንነታችንና የብሄራዊ እሴቶቻችን ንጣፍ መሰራት ሊሆን የሚችለው የዓድዋ ድል በዓል በዚህን ያህል መጠን የልዩነታችን ቀይ መስመር አስማሪ መሆኑ የሰከነ የውይይት ባህል እየራቀን ለመሄዱ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ብዙዎቹን የአካዳሚውን መስመር ሰዎች እንደሚያስማማው “የኢትዮጵያ አገራዊ ታሪክ ዘመንና መቼትን ተሻግሮ የሚጠቀስ ሰፊ እና ረጅም ዕድሜ አለው” ከአናሳ ዘውግ በመምጣታቸው ሁሌም ቢሆን የበታችነት ስሜት በሚያሰቃያቸው የህወሓት ስዎች ሲገለፅ እንደኖረው የኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ መቶ ዓመት ብቻ የሚቀነበብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የተዋለደው ወጥ ይዘት ባጀበው ቀጣይ ተግባር ሳይሆን ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ የኃይል ግፊቶች የግዛት ወሰኑን በማጥበብና በማስፋት ሂደቶች መሀከል የተፈጠረ ነው፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ሲባልም የትላንቷ ኢትዮጵያ ቅጥያ እንጅ ከጠፈር የመጣች ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የህወሓት “ኢትዮጵያ የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት” የሚለው የጉርምስና ሀተታ ከፖለቲካ ፍጆታነት የሚሻገር አይደለም፡፡
የታሪክ ሊቃውንቱ “ታሪክ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ ነው” ሲሉ ቢደመጥም፤ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪክ የትውልዱ የልዩነት ማስመሪያ ቀይ ቀለም ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለዘውግ ፖለቲካ ማፋፋሚያ አይነተኛ ማገዶ ነው፡፡ ታሪክ ለየዘውጉ (በ“ጨቋኝ” “ተጨቋኝ” ትርክት) ዘውጋዊ ንቃት መፍጠሪያነት አንጂ ከዚህ በተሻገረ መልኩ የአገራዊ ውህድ ህላዌ መጋቢና ደጋፊ ሆኖ ሲገለፅ አይስተዋልም፡፡
የማንነት ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ ጐልቶ በሚታይበት ኢትዮጵያ፤ በአገር ግንባታ ሂደቶች የታዩ ክስተቶችን በተመለከተ የሦስት ዘውጐች ሊሂቃንና ተከታዮቻቸው የበረታ ፉክክር ይስተዋልበታል፡፡
ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ጉልህ የመገፋት ሂደት ውስጥ እየተዋለደ የመጣውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን ለማቅናት እየተውተረተረ የሚገኘው የአማራ ብሄርተኝነት፤ ግማሽ ክፍለ ዘመንን በሚሻገር መልኩ ተደክሞበት ዛሬም በውል ያልፀናው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እና “የብቻ ሥልጣኔያችን ነው” የሚሉትን ሥልጣኔ ከአክሱም ሃውልት ፍርስራሽ ግርጌ መፈለግ የሚቀላቸው የአፄ ዮሐንስ ዘውድ አስመላሽ የትግራይ ብሄርተኞች በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ጫፍና ጫፍ የተወጠረውን የታሪክ ውርክብ በማጦዝ ወደረኛ የታሪክ ዘውግ ሙዚቃዊ ድርሰት /genre/ ፈጥረዋል፡፡
የምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ የወል ማህበረሰቦች (Cultural communities) በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ አገር ግንባታ ሂደቶች የታዩ ውስን ማህበራዊ መለንቀጦችን እያስታወሱ ቢያኮርፉም፤ ከላይ እንደተጠቀሱት ሦስቱ (የኦሮሞ፣ አማራና የትግራይ) ዘውጐች በታሪክ ውርክቡ ውስጥ ሚዛኑን የሳተ የጉርምስና ሀተታ ሲያቀርቡ አይስተዋልም፡፡ አልፎ አልፎ ከሲዳማና ከወላይታ የሚመዘዙ ብሄረተኞች የሚኒልክን አገር ግንባታ ሂደት ሲነቅፉ መስተዋላቸውን ሳንዘነጋ፡፡ ከሚኒልክ የደቡብ ዘመቻዎች ተጠቃሹ የጉራጌ ዘመቻ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና የምኒልክን የአገር ግንባታ ሂደት የጉራጌ ልሂቃን እንደ ሌሎቹ ብሄረተኞች አግንነው ስብከት ሲያሰሙ አይስተዋልም፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን ይጀምራል፡፡ የዳግማዊ ቴዎድሮስ የአንድነት ህሳቤ ባልተጠበቀ መልኩ የተቀጣጠለው አገራዊ ራዕይ (አንድነቷ የተጠበቀ፣ ማዕከላዊ መንግስቷ የተጠናከረ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የመመስረት ህልሙ) በመሳፍንቱ እምቢተኝነት፣ በካህናት ልግመት፣ በቴዎድሮስ የበዛ የቅጣት በትር፣ . . . በመጨረሻም በናፒየር በተመራው የእንግሊዝ ወታደራዊ ዘመቻ ቢመክንም በቀጣይ በነገሡት ነገሥታት (የውስጥ ሽኩቻቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ሊቀጥል ችሏል፡፡ በአፄ ዮሐንስ የዳር ድንበር ተከላካይነት ለጥቆም በንጉሰነገሥት ምኒሊክ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ከነሳንካዎቹ እውን መሆን ችሏል፡፡
ትውልድ የሚረግመው ጀግና!
ከምኒልክ የቀደሙት ሁለት ነገሥታት የተቻላቸውን ያህል ቢጥሩም ማዕከላዊ መንግስቱን በሚቆምና አገሪቷን ወደ ዘመናዊነት በማሻገር አፄ ምኒልክ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ነው፡፡ አፄው የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ ዘመኑ ያስገደደውን አማራጭ ሲወስደ የተጐዱ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ የማይካድ እውነት ነው፡፡
ይሁንና የአገር ግንባታ ሂደት ከደምና ከላብ ውጪ ከቶውንም ተከውኖ አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ እንደ ሰማይ ከዋክብት በሥልጣኔና በምርምር ስርጸት የራቁን የምዕራቡ ዓለም አገራት እንደ አገር ለመቆም የበዛ የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ አፈጣጠርም አብርሃም ሊንከን ከደከመላት አሜሪካ፣ ኦቶማን ቢስማርክ “ነፍጥና መስዋዕትነት” በሚል ከተዋደቀላት ጀርመን አልያም ከጣልያን ወይም ፈረንሳይ . . . አፈጣጠር የተለየ ክስተት አላስተናገደም፡፡ የፈሰሰው የደም መጠን ይለያይ እንደሆን እንጂ አገራቱ በነፍጥና በመስዋዕትነት የመቆማቸው እውነት ለመካድ የማይመች ዓለምአቀፋዊ ጉዳይ ነው፡፡
እርግማን አንድ፤ “ምኒልክ ሂትለር ነው”
ከኦሮሞና አማራ ፊውዳል ቤተሰብ እንደተወለደ በህይወት ታሪኩ ዙሪያ የተሰናዱ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ አፄው የሸዋ ንጉሣዊያን የዘር ግንድ ውስጥ የተገኘ በመሆኑ በመሬት ማስፋት /land power/ የሚያምን፤ ይህን ተከትሎ በሚገኘው የሰውም ሆነ የተፈጥሮ ሐብት የተሻለ ሥርዓተ-መንግስት እንደሚያነብር የተረዳ መሪ ነበር፡፡
በአፄው የንግስና ዘመንም ሆነ የንጉሠ ነገሥትነት ጊዜ በአገር ማቅናቱም ሆነ የውጪ ወራሪ ኃይልን በመመከቱ ዘመቻ የድል ከፋች አውራ የጦር አበጋዞቹ ውስጥ የኦሮሞ ራሶች ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በብዙዎቹ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች የምኒልክን ጨካኝነት አጉልተው ለማውጣት የሚጠቀሙባቸው ዘመቻዎች ሁለት ናቸው፡፡ የአርሲና የጨለንቆ ዘመቻዎች፡፡ ቀሪ የኦሮሞ ግዛቶች (ወለጋ (ኩምሳ ሞረዳ)፣ ጅማ-ግቤ (አባ ጅፋር) . . . ) በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን በገዛ ፈቃዳቸው ለምኒልክ የገበሩ መሆናቸው ይሰመርበት፡፡
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከዘውግ ፖለቲካ የታሪክ አተረጓጎም አኳያ በአጨቃጫቂነቱ የሚነሳውን የአፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት እና ለስድስት ተከታታይ ዓመታት (1872-1878/79) የዘለቀው የአርሲ የመከላከል ፍልሚያ ነው፡፡ ከዓመታት ፍልሚያ በኋላ በራስ ዳርጌ እና በራስ ወልደ ገብርኤል የበረታ ዘመቻ አርሲዎች በራቸው ተሰበረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ክስተት “የኢትዮጵያ ታሪክ የዘነጋው ነው” የሚሉን የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን ፕሮፌሰር አባስ ገናሞ (The history of Arsi, 1880-1935) በሚል ሥራው ላይ “የአርሲ ህዝብ በራስ ዳርጌ ጦር አልቆ ኃይሉ ከተዳከመ በኋላ ዳግመኛ እንዳይነካና ለነፃነቱ እንዳይዋጋ ለመቀጣጫ ብለው ወንዶችና ሴቶችን ከአሰላ በስተ ሰሜን በሚገኝ አኖሌ በተባለ ሥፍራ ላይ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ወንዶች በራስ ዳርጌ ትዕዛዝ የቀኝ እጃቸው እንዲቆረጥ ታዘዘ፡፡ ወራሪዎች የቆረጧቸውን እጅ በወንዶቹ አንገት ላይ እንዲንጠለጠል ተደረገ፡፡ በዚሁ መሰረት ሴቶችም ቀኝ ጡታቸውም እየተቆረጠ እንደወንዶቹ በአንገታቸው ላይ እንዲንጠለጠል ተደረገ፡፡ (ገጽ 45) ትርጉም” እያለ ይተርክልናል፡፡ ፕሮፌሰሩ ይህን ሲተርክልን አንድም የታሪክ ሰነድ በማስረጃነት አይጠቅስም፡፡ የታሪክ ማስረጃዬ የሚለውም ሥነ – ቃላዊ ትውፊትን ብቻ ነው፡፡ በታሪክ ሙያ መስፈርቶች ተቀባይነት የሚኖረው ታሪካዊ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ የምኒልክ “የጡት ቆረጣ” ተረክ ዛሬ ላይ ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ከአዲስ አበባ 150 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ውሃና መብራት በሌለባት አኖሌ ሃያ ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሐውልት ተገንብቷል፡፡
“በአርሲ ዘመቻ ራስ ዳርጌ ቄጤማ እየበተነ መላ አርሲን ተቆጣጠረ” የሚል ትርከት (narrative) የለም፡፡ ምንም በማይካድ መልኩ በአርሲ ዘመቻ ራስ ዳርጌ እና ራስ ወልደ ገብርኤል የአርሲ ጀብደኛ ተዋጊዎችን ለመቅጣት በአንድ ቀን አራት መቶ የሚደርሱ አርሲዎችን ቀኝ እጃቸውን እንደቆረጡ በአያሌው ቀኖ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጐመው የፋዘር ማርሻል ዲ.ሳልቫይች /The Oromo, an Ancient people, Great African Nation/ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህ መፅሐፍ አፍቃሪ ኦሮሞ የሆነው ፈረንሳዊው የኃይማኖት ሰው ከአርሲ ዘመቻ ጥቂት ዓመታት በኋላ አርሲ ደርሶ ከነዋሪዎቹ የሰበሰበውን መረጃ አካቶ የፃፈው መፅሐፍ ነው፡፡ በሰውየው መፅሐፍ ውስጥ “የሴቶች ቀኝ ጡት ተቆረጠ” የሚል መረጃ ፈፅሞ የለም፡፡ በጊዜው ይህ ድርጊት ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ይህ የኃይማኖት ሰው ድርጊቱን ከመፃፍ ምን የሚያግደው ኃይል ነበር?
ሰውየው ጽፎት ተርጓሚው ዘለለው የሚል መከራከሪያ እንዳይቀርብ እንኳን ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የትርጉም ሥራውን የሰራው አያሌው ቀኖ ኦሮሞ በመሆኑ ለክርክር አይመችም፡፡
የአርሲ ዘመቻ ከተፈፀመ ከሰማንያ አመታት በኋላ አርሲ ላይ የወለደው ፕሮፌሰር አባስ ገናሞ ግን ሥነ ቃላዊ ትውፊትን ብቻ መነሻ በማድረግ የምኒልክ ጦር በአርሲ ዘመቻ ጊዜ “የሴቶችን ጡት ቆርጧል” ይለናል፡፡ መቼም ለታሪክ ምርምር ዋና ወሳኝነት ያለው አስተማማኝ መረጃ ወይም የታሪክ ምንጭ ሰነዶች (በሙያው መስፈርቶች ተቀባይነት ያላቸው ታሪካዊ ማስረጃዎች) መሆናቸውን መካድ ያስተዛዝባል፡፡
በጊዜው የአገር ቤት ፀሐፍት የነበሩትን እነ ፀሐፊ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴንም ሆነ ዘግይተው የደረሱትን ህዝባዊ ታሪክ ፀሐፍትን “የተጉለት ደብተራ” ማለት የሚቀላቸው የዘውገ ብሔርተኞቹ “እውነት ከእኛ ዘንድ ብቻ ነች” በሚል “ለቅኝ ግዛት” ሃቲት በሚያመች መልኩ ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ በመያዝ ትውልዱን መራር ትውስታዎችን ከብዜት (ፈጠራ) ታሪክ ጋር በመጋት የተነጠለ ምልከታ ማስረፅ እንደ ስትራቴጂ ተያይዘውታል፡፡ ውጤቱም ሐውልትን ያዋለደው ጥላቻና እልህ የተጫነው ፖለቲካዊ እርግማን በሚኒልክ ላይ ማዝነብ ሆኗል፡፡
የግማሽ ቀኑ የጨለንቆ ጦርነት …
“ከ1855 ጀምሮ ሐረርንና አካባቢዉን ይገዛ የነበረው ሼክ ሙሐመድ ኢብን ዓሊ ኢብን አብድል አል ሽኩር ይባል ነበር፡፡ እርሱም ለመጀመሪያ ጊዜ ራውፋ ፓሻ ከዘይላ መጥቶ ሐረርጌ ግዛት በገባ ጊዜ ተዋግቶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የግብፆቹ ትጥቅ ዘመናዊ ስለነበረ መመከት ባለመቻሉ ልጁን ሐጂ የሱፍን በቅድሚያ ልኮ ለግብፅ ከዲቭ ገባርነቱን መግለጽ ግዴታ ሆነበት፡፡ ነገር ግን የግብፅ ጦር ወደ ሐረር ከተማ ለመግባት ሲጓዝ በዙሪያው ያሉት ኦሮሞዎች የአላ፣ የጀርሲ፣ የባሊሌ፣ የአቡራ . . . ነገዶች ተሰብስበውና ጠንክረው በእግርም በፈረስም እየጋለቡ በጦርና በቀስት ሰባት ሰዓት ያህል ከግብፆች ጋር ተዋግተው በመጨረሻ ሲሸነፉ እነሱም እንደአገር ልማድ ሴቶቻቸውን ልከው መገበራቸውን አስታወቁ፡፡ ቀጥለውም መሪዎቹ በየተራ እየመጡ ለራውፋ ፓሻ እጃቸውን ሲሰጡ፤ የግብፅ ባንዲራ አሚሩ ቤት ላይ በገሃድ ተሰቅሎ ሐረር በግብፅ አገዛዝ ሥር መሆኑ ታወጀ” (ተክለ ፃዲቅ ፣ አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 287)፡፡
ሐረር በዚህ መልኩ በግብፅ ከተያዘች በኋላ ለአስር አመታት ያህል በግብፆች ተገዝታለች፡፡ በዚህ ጊዜ ምኒልክ በወሎ በኩል የጀመረውን አገር የማቅናት ዘመቻ ወደ ደቡብ ፊቱን እያዞረ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆንም ምኒልክ የሸዋ ንጉስ እንጂ ንጉስ ነገስት አልነበረም፡፡
በተክለፃዲቅ አገላለፅ ፍሬያማ በሆነው አየሩ ለሰውነት ተስማሚ በሆነው ሰፊ የሐረር ግዛት ላይ ፈረንሳይም ጣሊያንም የቅኝ ግዛት ምኞታቸውን ዓይን ሳይወረውሩ አልቀረም፡፡ ምኒልክ ስትጠብና ስትሰፋ የኖረችውን ኢትዮጵያን እያሰበ፣ መሐመድ ኢብን አሊ ጋዝ አህመድ (ግራኝ አህመድ) ከምስራቅ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ለ15/16 ዓመታት ጠቅልሎ የገዛትን ኢትዮጵያ እያስታወሰ ፊቱን ወደ ሐረር ቢያዞር በምን መለኪያ እንደ ግብፆች “ቅኝ ግዛት” ሊባል ይችላል?
ግብፆች በሐረርም በዘይላም በሌላውም የኢትዮጵያ ዙሪያ ግዛታቸውን ለአስር ዓመታት ቢያስፋፉም በሱዳን የመሃዲስቶች አጥቂነትና በኩፊት የኢትዮጵያዊያዉን አሸናፊነት የተነሳ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ውድቀት ስለገጠማቸው ያለ አስገዳጅ ጦርነት ሐረርን ለመልቀቅ ተገደዱ ፡፡ (ተክለፃዲቅን ያጤኗል)
በዚህ ጊዜ (ግንቦት 1878) የሐረር ተወላጅ ባላባቱ አሚር አብዱላሂ የሐረር ገዥ ሆነ፡፡ ጣሊያን ሐረር ላይ ዓይኗን ጥላ ነበርና ምኒልክ ጣሊያንን መቅደም ግድ አለው፡፡ አሚሩ ገዥ በሆነ በሰባተኛው ወር በወርሃ ታህሳስ 1879 የሚኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ ወደ ሐረር ፊቱን አዞረ፡፡
የአፄው የጦር ሜዳ ውሎ ዘጋቢ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ የጨለንቆን ጦርነት እንዲህ ይተርከዋል “. . . አሚር አብዱላሂ ዛሬ (ታህሳስ 29) በዓለ ልደት (ገና) ነውና ክርስቲያኖች አይሰለፉም /አይዋጉም/ ብሎ መክሮ ጦሩን ጠቅልሎ ሰናድሩን /ባለጠመንጃውን/ ከፊት መድፎቹን ከመካከል፣ ቀስተኛውን ከኋላ ከዚያ ቀጥሎ ፈረሰኛውን ጋሻኛውን አሰልፎ በአምስት ሰዓት ወደ ሰፈር መጣ ንጉሡ መነጥራቸውን ከዙፋናቸው ፊት አቁመው ሲመለከቱት ከሰፈር ማዶ ያለውን ቁልቁለት ወርዶ ከደኑ ለጅሐድ /ለቅዱስ ጦርነት/ ሲመጣ አዩት፡፡
በዚህ ጊዜ በቁጣ . . . ሰራዊታቸውን “ሄደህ በለው” ብለው አሰልፈው ሰደዱት፡፡ . . . አሚር አብዱላሂም መድፎቹን ማስተኮስ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከመኳንንትም ከቤት አሽከሮችም ከሰራዊትም አጫሪው ፈረሰኛ ሄዶ ገጠመው በዚያ ጊዜ ፅኑ ውጊያ ሆነ፡፡ የንጉሱ ሰራዊት መድፎቹን እጅ አድርጐ /ማርኮ/ አዞረበት፡፡ የግንባሩም ሲዘልቅና ሲገጥመው አሚር አብዱላሂ ድል ሆነ (ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምንልክ፤ ገጽ 145)”
“የተደበቁ የግፍ ታሪኮችን ፈልፍለን አውጥተናል” የሚሉን እነ ገመቹ መልካ እና ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህ በውጊያው “አጤ ምኒልክ በእጃቸው በገባው የአውሮፓ ነፍጥ እንደልባቸው ቢጠቀሙም የኦሮሞ ልጆች ለሐገራቸው ነፃነትና ለክብራቸው ሞትን ሳይፈሩ እየተፋለሙ የጀግና ሞት ሞተዋል፡፡ ቅኝ ገዥዎች የኦሮሞን ልጆች ደም ረግጠው በማለፍ በድዋንበር ፈረስ መጋላ በሚባለው አደባባይና በአምስቱም (የሐረር) በር የንጉሱን ባንዲራ (የአቢሲንያን ባንዲራ) ሰቀሉ” (ኦሮሚያ የተደበቀው የግፍ ታሪክ፤ ገጽ 82) ይሉናል፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ሐረር ላይ የግብፅ ባንዲራ ለአስር ዓመታት መውለብለቡን በቁጭት ስሜት ቀርቶ በለዘብተኝነት እንኳ በመፅሐፋቸው ውስጥ ያልገለፁልን እነ ገመቹ መልካ የንጉሱ (የአቢሲንያ) ባንዲራ ሐረር ላይ መውለብለቡን እጅግ በቁጭት ስሜት ይተርኩልናል፡፡ ሐቁ ግን የምኒልክን የደቡብም ሆነ የምስራቁን ዘመቻ በድል ፋና ወጊነት የተወጡት የመንዝ ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ፈረሰኞቹ የሸዋ ኦሮሞዎችም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡
ገመቹ መልካና ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህ ከላይ በተጠቀሰ የጋራ መፅሐፋቸው የጨለንቆ ጦርነት ላይ 4000 (አራት ሺህ) ተዋጊ በአሚሩ በኩል እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡ እውነት ነው፡፡ ሌሎች የታሪክ ፀሐፊዎችም የተሳታፊው ቁጥር ላይ ልዩነት አይስተዋልባቸውም፡፡ በጨለንቆ ጦርነት ላይ “አልቋል” የተባለው የሰው ህይወት መጠን ግን ዛሬም ድረስ አከራካሪ ነው፡፡ ኮብላዩ “ሚኒስተር” ጁነዲን ሳዶ “በጨለንቆ ጦርነት አንድ መቶ ሺህ የሀረር ሰዉ አልቋል” ይለናል፡፡ የሚጠቅሰዉ ታሪካዊ ሰነድ ግን የለም፡፡ ከርሱ የተሻለ የተቆርቋሪነት ስሜት ያላቸዉ እነ ገመቹ መልካ እንኳ ይህን በድፍረት አልጻፉም፡፡ ምኒልክ በድል አድራጊነት ሐረር እንደገባ አንድ አዋጅ አስነግሯል፡፡ “እስላሙና ኦሮሞው እንደ አባቱ ይደር” ይላል፡፡ ከዚህ አዋጅ ተነስተን በጦርነቱ ተሳታፊ ከነበሩት የአሚሩ ወታደሮች ባለፈ የከተማው ነዋሪ ላይ የደረሰ ውድመት ያለ አይመስልም፡፡ የከፋ ውድመት ቢደርስ በጊዜው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ቦረሊ የተባለው የፈረንሳይ መንገደኛ ኢትዮጵያን በተመለከተ በፃፈው መፅሐፍ ውስጥ ጉዳዩን ለማካተት የሚቀድመው አልነበረም፡፡ ግማሽ ቀን ያልተሻገረው የጨለንቆ ጦርነት ወራትና አመታትን ከተሻገሩት የደቡብ (በተለይም የጉራጌ፣ የከፋ፣ የወላይታ፣ የሲዳማ . . .) ዘመቻዎች አኳያ (በንጽጽር ሲታይ) እዚህ ግባ የሚባል አይደለም (“የአንድ ሰው ሞት አሳዛኝ (ትራጄዲ) የብዙዎች ግን ቁጥር (ስታቲስቲክ)” ነውእያልን እንዳልሆነ ልብ ይሏል)፡፡ መቼም ኢትዮጵያ በጦርነት የተፈጠረች አገር ነችና ጦርነትን ከጦርነት ማነፃፀር ለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የመንግሥት ምስረታ (የስቴት ፎርሜሽንን) ባህርይን እዚህ ላይ ያጤኗል፡፡ ለዚህ ጦርነት መታሰቢያ በሚል ለነገ አገራዊ ዕዳ ሊያመጣ የሚችል “የመታሰቢያ ሐውልት” ሐረር ላይ በሃያ አምስት ሚሊዮን ብር ተገንብቷል፡፡ ያው የብሄርተኝነት መቀሰቻ ከሆነው አንዱ ከትላትን የሚጐተቱ መራር የጦርነት ታሪኮችን በብዜት መልኩ ለትውልዱ መጋት ነው፡፡ (እ)የተገነቡ ያሉ ሐውልቶችም ከዚህ የተሻገሩ አላማ የላቸውም፡፡
የነገሩ ምፀት ደግሞ ከምኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ በኋላ አድዋ ላይ ወራሪውን የጣሊያን ኃይል በተባበረ ክንድ ድል የነሱት ኢትዮጵያውያን ከአርሲና ከሐረር የተውጣጡ ፈረሰኞች ፣ ቀስተኞች እና ጋሻኛ የድሉ ባለቤት (ተሳታፊ) መሆናቸው ነው፡፡
የእነዚህ ከሐረር – ዓድዋ ፣ ከአርሲ – ዓድዋ. . . በባዶ እግራቸው ዘምተው ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የተዋደቁ የኦሮሞ አባቶችን የዓድዋ ተጋድሎ በአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ማወደስ አልሆንልህ ያላቸው የኦሮሞኛ ሙዚቃ አርቲስቶች (ቀመር የሱፍና ሹክሪ ጀማል) “ምኒልክ የአፍሪካ ሂትለር” ብሎ ለመዝፈን ግን አይሰንፉም፡፡ ነገሩ ግልፅ ነው! ዓድዋ ላይ ከአዋጊነት እስከ ጭፈራ ከፈረሰኛ እስከ እግረኛ ድረስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በመዋደቅ ኮከብ ሆነው የዋሉትን የኦሮሞ አባቶች በኦሮምኛ ሙዚቃ ማወደስ ጠርዘኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ዋነኛ ማጠንጠኛ የኦሮሞን ጥያቄ በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የሚቀነብበው በመሆኑ ከ“ቅኝ ግዛት” ሃቲቱ ጋር በቀጥታ የሚላተም በመሆኑ ዓድዋን የሚያስታውሱ (የሚዘክሩ) የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን ልናዳምጥ አልታደልንም፡፡
ለጠርዘኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጀናስ የኦሮሞዎች የዓድዋ ተሳትፎ ራሱን በቻለ ሬጅመንት የሚታይ እንደሆነ “The Battle of Adwa, African victory in the age of Empire” ሲል በሰየመው መፅሐፉ የሚገልፀው ነገር አይዋጥላቸውም፡፡ የኦሮሞ ፈረሰኞች በዓድዋ ጦርነት ጊዜ “ወደ ሸለቆው ሲወርዱ በድንገት የገነፈለ ጥቁር ባህር ይመስላሉ” በማለት ጀግንነታቸውን የገለጹበት መንገድ ለእነርሱ “የአቢሲንያ ተረት ተረት ነው”፡፡
አለመታደል ሆነና ለጠርዘኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዓድዋ ላይ የዘመቱት የቀደሙት የኦሮሞ ተዋጊ አባቶች፤ ምኒልክ በርቀት መቆጣጠሪያ እያሽከረከረ የሚያፋልማቸው ሮቦት እንጂ ራሳቸውን ችለው፤ ማንነታቸውን ጠብቀው የተዋደቁ ብርቱዎች አይመስሏቸውም፡፡ በራሳቸው የቆሙ ብርቱዎች እንደነበሩ ቢያምኑማ የ“ቅኝ ግዛት” ሃቲትን ሲያነበንቡ ባልኖሩ ነበር፡፡ ይሄው ውድቅ አመለካከት አድዋን የመሰለ ወታደራዊ ድል ወደ ፖለቲካዊ ድል እንዳንቀይረው እንቅፋት ሆነብን!! ዛሬም በየጥጉ “የእኛስ የጉድ ነው” እያልን እናላዝናለን፡፡
የእርግማን አንድ፡ ማሳረጊያ
አርሲና ሐረር ሌሎችም የደቡብ አገር የማቅናት ዘመቻዎች በሁለቱም ወገን የደም ዋጋ ባስከፈሉ ውጊያዎች የተጠቃለሉ እንጂ በብላሽ ስጦታ (ወደው የገቡትን ሳንዘነጋ) ወይም በህዝብ ውሳኔ ወደ ምኒልክ ግዛት የተጠቃለሉ አይደሉም፡፡ በወቅቱም ሰብዓዊ ጥሰቶች በገባሪው ወገን አልደረሱም ብሎ መከራከር ትርፉ ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡ ምኒልክ በደቡብ ዘመቻ እጅ/እግር አልቆረጠም ብሎ በጨበጣ መከራከር የትም አያደርስም፡፡ ቀርቶ የታሪክ መዛግብት ማገላበጥ፤ በትንሹም ቢሆን “ፍትሐ-ነገስት”ን ማስታወስ የአባት ነው፡፡
የወደረኛውንና ጭፍራውን እጅ/እግር መቁረጥ በምኒልክ ጊዜ የተጀመረ ድርጊት ሳይሆን የዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ አባት የሆኑትን ሁለቱን የቀደሙ ነገስታት (ቴዎድሮስና ዮሐንስ) ጨምሮ የፊት መሳፍንትም ሆኑ ነገሥታት ፈጽመውታል፡፡ ከቶም አንዳንዶች አፍንጫ እስከ መፎነን፣ ምላስ እስከ መቁረጥ ደርሰዋል፡፡ (መስለብማ በየትኛውም መሳፍንት “የወግ” ነበር)፡፡
በጉልበት ሌላውን ማስገበር በመፈራረቅ የተከወነ ድርጊት ነው፡፡ በመስመር መሐል በመካከለኛው ዘመን የተካሄደውን የኦሮሞ መስፋፋት የፈጠረውን እልቂት የአባ ባህሪን፣ የአለቃ አጸሜንና የአለቃ ታየን ሥራዎች እያጣቀሱ ሁኔታዎችን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የታሪክ ሰነድ ባለሃብቱ ዶ/ር መርዕድ ወልደ አረጋይ ከዛሬ 45 ዓመት በፊት ለሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ማሟያው ያዘጋጀውን ጽሁፍ “Southern Ethiopia and the Christian kingdom 1508 – 1708, with special Reference to the Galla Migration and Their consequences” ላይ የተካተቱትን ወሳኝ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች መገምገሙ ለጋራ ቤታችን ይበጃል፡፡
“ሞጋሳ” እና “ጉዲፈቻ” በተሰኙ ማህበራዊ ሥርዓቶች የባህል ቅቤ ማቅለጫ ድስት (melting pot) ውስጥ የገቡትን የህብረተሰብ ክፍሎች ማሰብ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ ኦሮሞ በመካከለኛዉ ዘመን ሲስፋፋ የተዋጡ የማህበረብ ክፍሎችን ክዶ መከራከር የሚያዋጣ አይደለም፡፡
በነዚህና መሰል ጉዳዮች ውስጥ ኦሮሞ ገዥም ተገዥም ነበር፡፡ አስገባሪም ገባሪም ነበር፡፡ ቀላጭም አቅላጭም ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬ ላይ ኦሮሞ መስፋፋቱን ተከትሎ ከሟሟበት የገዳ ሥርዓ ውጪ ሌሎች የዘውጉ ማንነቶች ከሞላ ጐደል ህያው ናቸው፡፡ ይልቁንስ ኢትዮጵያን ቀስቶ በማዋቀሩ ረገድ በማህበራዊውና በኢኮኖሚያዊው መስክ ይበልጥ አቃፊ ደጋፊ ሆኗል፡፡ ተጠቃሚነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ቢወድቅም ቅሉ፡፡ ፖለቲካዊ ተሳትፎው ግን ዛሬም ድረስ የዛለው ጠርዝ የታከከው የልሂቃኑ ጉዞ ውጤት ነው፡፡ መቼም በጥንቸሎች የታሰረው ዝሆኑ ኦህዴድን እንደ ወሳኝ የፖለቲካ ድርጅት የመቁጠር ግዴታ የለብንም፡፡
አሜሪካውያን ከሚያከብሯቸው መሪዎቻቸው መካከል አብርሃም ሊንከን አንደኛው ነው፡፡ ጭራሹኑ እስከ መመለክ የደረሰ መሪ ነው፡፡ ይሁንና የደቡብ ግዛቶች ከሰሜኑ ለመገንጠል ጦርነት በከፈቱበት ወቀት አብርሃም ሊንከን የአንድነቱ ጠበቃና መሪ በመሆን ከፍተኛ ጦርነት መርቷል፡፡ በዚህ ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ አልቋል፡፡ አብርሃም ሊንከንን ግን አሜሪካዊያን በፀረ ህዝብነት አለያም በጨፍጫፊነት ሲያነሱት አይታይም፡፡
ለማናቸውም የኢትዮጵያ ዘመናዊ አገር ግንባት ሂደትና ፈተናዎች በዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ መቼት ውስጥ ተቀምጣ መታየትና መመዘን ይኖርባታል፡፡ አባ ዳኘው-ምኒልክም የዛሬ ዘመን መሪ ሳይሆን የራሱ ዘመን መሪ ነው፡፡ የንግስና ዘመኑ የሚመዘነው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መመዘኛ ነጥቦችን በተንተራሰ ሳይሆን እንደ ጊዜው ማዕቀፍ መታየት ግድ ይለዋል፡፡
ቻርለስ ቲሊ “ጦርነት አገርን ይወልዳል፤ አገርም ጦርነት ይወልዳል” ሲል የተናገረውን ኃይለ ቃል መምዘዙ እንድንግባባ ዕድል ይሰጠን ይሆናል፡፡ ካልሆነም የጀርመን አባት ቢስማርክ (አገራት በብረትና በደም ይመሠረታሉ) “states are formed by iron and blood” በማለት በተግባር አገሩን ለማዋሃድ የተጓዘበትን መንገድ ማስታወሱ የምኒልክን አገር የማቅናት ዘመቻ ግልፅ ያደርግልናል፡፡
በዚህ አግባብ ምኒልክ ከአገር መሃንዲስነቱ አኳያ “ነፍጥና መስዋዕትነትን” የአገር ማዋሃጃ ስልት አድርጎ የተጠቀመበትን መንገድ በትይዩ አስቀምጠን ስናይ ምኒልክ ለ“ሂትለር” ሳይሆን ለቢስማርክና ለአብርሃም ሊንከን ይቀርባል፡፡ ቆራጥ ዘመቻዎቹን ስንመረምር ደግሞ “እምዬ” የሚለውን የቁልምጫ ሥሙን ለመቀበል ይቸግረን ይሆናል፡፡ ምኒልክ “እምዬ” ቢቀርበት እንኳ የአገር ምህንድስና ዉሉ በደንብ የገባው states Man ነው፡፡ በምኒልክ ሃውልት ላይ ተጽፎ እንደሚነበበው ጽሁፍ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው”፡፡
እናም ሊንከን በአንድነት ጠበቃ ደግፎ ባቆያት አሜሪካን አገር ሚኒሶታ ግዛት አልያም ቢስማርክ በተዋደቀላት ጀርመን፤ በርሊን ውስጥ ሆት ዶግ እየበሉ፤ የካልዲስን ቡና እንደ ወረደ እያጣጣሙ ምኒልክ በነፍጥና በመስዋዕትነት ያቆማትን አገር ቢሳካ ለመግዛት ካልሆነም ለመገንጠል እየታገሉ “ምኒልክ ሂትለር ነው” ቢሉ አንድም ርባና ቢስ የትውልድ ፖለቲካዊ ርግማን ነው፤ ሌላም አላዋቂነትን በአደባባይ መግለጥ ነው፡፡
እርግማን ሁለት፡ “ምኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ”
በቀጣይ ዕትማችን የምንዳስሰው ጉዳይ ይሆናል!!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
aradw says
All that is listed may be the cause. But in today’s conflict the cause is competition for economic and political supremacy and mistrust. We know the Oromo region is central to politics and resources. The major political and economically wealthy cities are in Oromia. Oromia is geographically the center that holds Ethiopia. In my opinion the cause is who controls Oromia? Is it the Oromo people? Is it the Tigray minority or in the past the Amhars. For a long time we have seen mistrust between these three big nationalities. Mistrust is the product of history and subjugation.