“ህወሓት ወደ አገር በሚገቡ መንገደኞች ገንዘብ ለማስገባት እየጣረ ነው” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ ካወጣን በኋላ ዛጎል “በአሜሪካ “ገንዘብ – ውሰዱልን” የቅርብ ወዳጆችን ግንኙነት በጠሰ” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ዘገባ ለንባብ አብቅቷል። አሁንም የኢትዮጵያን መንግሥት ለማሳሰብ የምንፈልገው ይህንን የተቀናጀ ሥራ እያከናወኑ ያሉት ህወሓቶች መሆናቸውን ነው።
ከዚህ ሌላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ድንበር ኬላዎች ከጎረቤት አገር ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ ይገባል ከሚለው እሳቤ በተጨማሪ በቦሌ በኩልም እየገባ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባዋል። ስለዚህ በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮጵላን ማረፊያ በተጓዦች በተለይም በበረራ ሠራተኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል እንላለን።
በአሜሪካ “ገንዘብ – ውሰዱልን” የቅርብ ወዳጆችን ግንኙነት በጠሰ
“እንዴት ብትንቁን ነው” ሲል ባለቤት ቁጣ የተሞላ ምላሽ ሰጠ። ባልና ሚስት የቆየ ወዳጆቻቸው ቤት ሄደው እንደ ሃበሻ ወግ ከተጋበዙ በኋላ “ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ውሰዱልን” ብለው ሲጠይቃሉ። እንግዶቻቸውን እየጋበዙ ያሉት ቤተሰቦች ምን ያህል እንደሆነ ይጠይቃሉ። እንግዶች “ሁለት መቶ ሺህ” ሲሉ ይመልሳሉ።
ጥያቄው የቀረበላቸው ሰዎች በመደነቅና በተደበላለቀ ስሜት “ሁለት መቶ ሺህ ዶላር?” ሲሉ በመገረም ማብራሪያ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። “አይደለም የኢትዮጵያ ብር” ሲሉ እንግዶች ይመልሳሉ። ከዚያም አንድ ሁለት ይባባሉና ይካረራሉ። ጥያቄው የቀረበላቸው ቤተሰቦች በተለይም ባል “እንዴት ብትንቁን ነው” ሲል ቅሬታውን በቁጣ ያሰማል። በዚያው የቃላት ልውውጡ በርትቶ በሚስት ሸምጋይነት እንግዶች ቤቱን ለቀው የሄዳሉ። ነገሩ እንዲህ ነው።
ለረዥም ዓመታት አሜሪካን አገር የኖሩ እናት ከእርጅና ጋር በተያያዘ ስለተዳከሙና ስለታመሙ “ለአገሬ አፈር አብቁኝ” በማለት ልጃቸውን ወትውተው ወደ አዲስ አበባ ለማምራት ከሁለት ቀን በፊት ጉዞ ነበራቸው። በጣም ስለተዳከሙ ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ በሰላም እንዲደርሱ ለእሳቸው ድጋፍ ስለማድረግና ስለ ጉዞው ከማሰብና ከመጨነቅ ውጪ ሌላ ሃሳብ አልነበራቸውም። ጉዞው ረዥምና የስንበትም ዓይነት በመሆኑ!
በዚህ መሃል ነበር የቀድሞ ወዳጆቻቸው ልጅ እናቱን ይዞ ወደ አገር ቤት እንደሚያመራ በመስማታቸው ለጉብኝት የሄዱት። ይሁን እንጂ ጉብኝቱ ሁለት ዓላማ ያለው ነበረው። መሰናበትና ብር መላክ። ለዚህም ውለታ ክፍያ መስጠት።
ድርጊቱን በስልክ የተከታተለች ለዛጎል እንደነገረችው ሁለት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ አሮጌ ብር ወደ አገር ቤት ለመላክ የቀረበው ጥያቄ መጨረሻው የበርካታ ዓመታት ወዳጅ ቤተሰቦችን አለያይቷል። ወዳጅነታቸው ተበጥሷል። በደከሙ እናት ሻንጣ ውስጥ በመደበቅ ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄድላቸው የጠየቁት ሰዎች ሌላም ብር እንዳላቸው፣ ብሩንም በተለያዩ ጊዜያት ወደ አሜሪካ ንብረት ሸጠው እንዳመጡት አስረድተዋል።
ታሪኩን ያስረዳችው “ተደፈርን” ያሉት ቤተሰቦች ዘመድ ስትሆን ይህንን መረጃ ከሰማች በኋላ ፊንላንድና ሎንደን ከባልደረቦቿ ጋር በዚሁ አስገራሚ ጉዳይ ስትወያይ እነሱ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄው እንደሚቀርብ ጠቅሰው ይህንን ጉዳይ የኤርፖርት ሃላፊዎች እንዲሰሙ ቢደረግ መልካም እንደሆነ እንደነገሯትና ለዛጎል ለመግለጽ እንዳነሳሳት ገልጻለች።
“ማሰብ የተሳነን ይመላል። እናት የደከመባቸውን ቤተሰቦች በህገወጥ ገንዘብ ውሰዱልን። ወሮታ እንከፍላለን ማለት ፍጹም ሰዋዊ አይደለም። ሰው ራሱ ህገወጥ መሆኑ ሳያንሰው ሌሎችን ህገወጥ ለማድረግ መድፈሩ ያስገርማል” ብሎ እናቷ የደከሙባት ዘመዷ ባለቤት መናገሩንና እልህ መጋባቱን የገለጸችው ሴት፣ ከድንበር ጥበቃ ባልተናነሰ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዦች፣ እንዲሁም የበረራ ሰራተኞች ላይ ጠንካራ ፍተሻና ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ መክራለች።
ከሁሉም በላይ ግን በአሜሪካና በአውሮፓ የኢትዮጵያ ብር በግለሰቦች እጅ እንዳለ ማረጋገጧ አንዳስገረማት፣ ይህም ገንዘብ በአየር መንገድ በኩል ስለመውጣቱ ጥርጥር እንደሌለውና ማምከን የሚቻለውም የወጣበትን ቀዳዳ በመድፈን እንደሆነ አመልክታለች። ሕዝብ ገንዘብ መቀየር የተፈለገበት ምክንያት ግልጽ ከሆነለት በተመሳሳይ የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ወደ ጎን በማለት ወደ ህግ በማቅረብና ጥቆማ በመስጠት ሊተባበር እንደሚገባም አመልክታለች። ለወደፊቱም በተመሳሳይ መረጃ ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማትል አስታውቃለች።
ጥቆማ ሰጪዋ የሰዎቹን ስምና የመኖሪያ ከተማ የገለጸች ቢሆንም ከማተም ተቆጥበናል። መንግስት የብር ኖት እንደሚቀየር ይፋ ካደርረገ በኋላና በፊት ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ውስጥና የተለያዩ አገራት የብር ኖቶች በፍተሻ ኬላዎች ላይ መያዛቸው ሪፖርት ሲደረግ መሰንበቱ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ከ113 ቢሊዮን ብር በላይ ከመንግሥት ባንክ ቁጥጥር ወይም ስርዓት ውጪ እንደሚንቀሳቀስ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ህገወጥ የብር ኖት ገበያው ላይ መሰራጨቱ አንድ ላይ ተዳምሮ የአገሪቱን የግሽበት መጠን እንዳናረው ባለሙያዎች ሲናገሩ፣ መንግሥትም ይህንኑ አውቆ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።
የብር ኖት ለውጡ ይፋ ከሆነ በኋላ ውሳኔውን እጅግ አክርረው የሚቃወሙ ወገኖች መሰማታቸው ጉዳዩን አስገራሚ እንዳደረገው ከተለያዩ ባለሙያዎች እየተደመጠ ነው። ማንም ተቃዋሚም ሆነ የመንግሥት አካል ህገወጥ ገንዘብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያሽመደመደና ለሽብር ተግባር እየዋለ ባለበት ወቅት የመንግሥትን ውሳኔ መቃወሙ “ሕገወጥ ገንዘብና ህገወጥነት ይሻለኛል በማለት አገሪቱ ላይ ማፊያ እንዲፈነጭ መፈቀድ ነው” በሚል ክፉኛ ተተችቷል። (@ዛጎል፥ ፎቶው በርግጥ ቦሌ የተከሰተ ሳይሆን ለማሳያነት የቀረበ ነው)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply