• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ዳግም ተገናኘን!

January 8, 2018 05:12 pm by Editor 1 Comment

… “ያሰብኩት ተሳካ ያለምኩት ደረሰ፣

ሃሳቤም ተሟላ መንፈሴም ታደሰ፤…”

ለዛሬዋ ጽሁፌ መግቢያነት የመረጥኳት ግጥም፣ በእውቁ ድምጻዊ በጥላሁን ገሠሠ ከተቀነቀኑት አያሌ የማኅበራዊ ዘርፍ ዘፈኖች አንዱ የሆነው ዘፈን አዝማች ናት(በሃሳባችሁ ዜማውን እያስታወሳችሁ ተከተሉኝ፤ በተለይ ከአጃቢ የሙዚቃ መሳሪያዎች መካከል ጎልታ የምትሰማዋን፣ የአየለ ማሞን የማንዶሊን ዜማ እያዳመጣችሁ)።

… ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት “አማኒ ኢብራሂም — ’ያልታወቀው‘የጥበብ ሰው” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ቢጤ በኢትዮጵያውያኑ ድረ-ገጾች (በኢትዮ-ሚድያ፣ በኢኤምኤፍ፣ በቋጠሮ፣ በጎልጉል…) ላይ ለንባብ አብቅቼ ነበር።

ጽሑፉ እንደወጣ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ከሰላሣ ዓመታት በላይ የትና እንዴት እንዳለ ያላወኩትን፣ በሙዚቃ ሙያ በእጅጉ የተካነውን፣ ሁሌም ብዙዎች በአርዓያነት የሚጠቅሱትንና የቀድሞ መምህራችን የነበረውን ጋሼ አማኒ ኢብራሂምን በስልክ አገኘሁት። (በዚህ አጋጣሚ ዘርፈ-ብዙ መረጃዎችን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በማቀበልና አለኝታ በመሆን ያላሰለሰ አገልግሎት ለሚያበረክቱት ድረ-ገጾቻችን የላቀ ምስጋና ይድርሳቸው!)

…በድምጽ ተገናኝተን ባወጋን በዓመቱም በአካል ለመገናኘት በቃን። ከጋሼ አማኒ ጋር ብቻም ሳይሆን፣ ከሰላሣ ዓመታት በፊት አብረን ከተማርናቸው ጥቂት የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ጋርም ጭምር!

ይህ እውን ሊሆን የበቃው ደግሞ፣ ጥቂት የቀድሞ የያሬድ ምሩቃን፣ አምና በላስ ቬጋስ ከተማ ተሰባስበን፣ አንድ የመገናኛ ዝግጅት ለማድረግ በመወሰናችን ነበር። በላስ ቬጋስ ከተማ ነዋሪ ከሆኑት አስር ያህል የያሬድ ምሩቃን አምስቱ በቋሚነት ዓመቱን ሙሉ ተንቀሳቅሰን፣ ኦክቶበር 25 እና 26 ቀን 2017 ያገናኘንን ዝገጅት አደረስነው።

መነሻ ዓላማችን፣ የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ምሩቃን ማኅበርን ለሟቋቋም መሰረት መጣል ነበር። ሊቋቋም የታሰበው ማኅበር ዓላማ ብለን ያስቀመጥናቸው ነጥቦችም፣ “…በተማሪነት የህይወት ዘመናችን ያሳላፍናቸውን ትዝታዎች የምናድስበት፣ ከፊሎቻችን በሙያው ዙሪያ በስራ ዘመን በቆየንባቸው ዓመታት ያዳበርናቸውን ጥልቅ የሆኑ የጓደኝነት ፍቅርና ቤተሰባዊ መቀራረብ በተሻለ መልኩ የምናጠናክርበት፣ ለት/ቤቱ የበኩላችንን ድጋፍ የምናደርግበት፣ በሙያው ዙሪያ መሰራት ይገባቸዋል ብለን የምናምንባቸውን በውስጣችን የሚመላለሱ መልካም ሃሳቦችን በጋራ በመምከር የምናምንባቸውን በውስጣችን የሚመላለሱ መልካም ሃሳቦችን በጋራ በመምከር የምንተገብርበት፣ በህይወት ያሉትን መምህሮቻችንንና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ባለሙያዎችን የክብር ዕውቅና የምንሰጥበት፣ በህይወት የሌሉትን ደግሞ የምንዘክርበት፣…” የሚሉ ነበሩ።

ከየግል ኑሯችን የምትተርፈንን ጊዜ እያብቃቃን ለዝግጅቱ መሳካት ጥረት አደረግን። በቅድሚያ ለዝግጅቱ ማከናወኛ የሚሆን ገንዘብ ከየራሳችን ኪስ እንድናወጣ ተወሰነ። ከቁጥራችን ማነስ የተነሳ፣ ጫናው ከፍተኛ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ፣ የሙዚቃ መሣሪያ በእጃችን እያለና መጫወት እየቻልን፣ ለምን የምናውቃቸውን ድምጻዊያን እንዲተባበሩን በመጠየቅ የገቢ ማግኛ ምሽቶችን አንፈጥርም የሚል ሃሳብ ብቅ አለ። እንዲህ አይነቶቹን ሃሳቦች በማፍለቅ የታወቀው የተሻገር ይልማ ሃሳብ ነበር፤ ሃሳቡም ቅቡልነትን አገኘ፤ ወደ ተግባርም ተለወጠ።

በየሁለት ወሩ ልዩነት ሁለትና ሶስት ድምጻዊያንን ለትብብር በመጠየቅ፣ በሁለት ሬስቶራንቶች ተባባሪነት የሙዚቃ ምሽት ዝግጅቶችን አደረግን ።(በዚህ አጋጣሚ-ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ከተለያዩ ስቴቶች ወደ ቬጋስ በመምጣትና ያለምንም ክፍያ በነጻ ለእኛ ዝግጅት መሳካት ከፍተኛ አስተዋጸዖ ላበረከቱልን ድምጻውያን፣ አያሌው መስፍንና አለም ከበደ፣ ንጉሤ ቦጋለና ገነት አባተ፣ ቤዛ ታደሰና ፋሲካ ዲሚትሪ፣ እንዲሁም የከተማችን ነዋሪ ለሆነው ወጣት ሚኪ ዜማ የከበረ ምስጋና ይድረሳቸው!)

ይህ ሁሉ ተደርጎ ቋት ባይሞላም፣ በተገኘው ደገስን። ወደ ዝግጅቱ መዳረሻ ሳምንት ላይም፣ ከውጭ የሚመጡት የያሬድ ምሩቃን እንግዶቻችን ወደ ላስ ቬጋስ መግባት ጀመሩ፤ ዶ/ር እዝራ አባተ (ከኢትዮጵያ)፣ ኃይሉ ካሣዬ (ከጀርመን)፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው (ከካናዳ)፣ በድሉ ተክለ-ማርያም ከባለቤቱ ከኢሌኒ ጋር( ከሎንዶን)፣ ጥላሁን ሲሣይ (ከጀርመን)፣ በኃይሉ ክፍሌ (ከካናዳ)፣ ከሃገር ውስጥም፣ የክብር እንግዳችን ጋሼ አማኒ ኢብራሂም (ከሜሪ ላንድ)፣ ምስክር ከፍያለው (ከካሊፎርኒያ)፤ ላስ ቬጋስ ካለነው የያሬድ ምሩቃን ጋር ሲደመሩ፣ የቬጋስ ከተማ ወደ አስራ ሰባት የሚሆኑ የያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት ምሩቃንን ማስተናገድ ያዘች።

ኦክቶበር 25፣ 2017 ረቡዕ ዕለት ምሽት ላይ በፓላስ ስቴሽን አዳራሽ፣ ያሬዶች፣ ቤተሰቦቻቸውና ጥቂት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታደሙ። በቅርቡ ላለፈው መምህራችን ለአቶ ሰሎሞን ሉሉ እንዲሁም አስቀድሞ ላለፉ መምህራን፣ ተማሪዎችና በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩን የጥበብ ሰዎቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደረገ።

ዝግጅቱን በቀልድ እያዋዛ የሚመራው ፋንታሁን ሸዋንቆጨው መድረኩ ላይ ተንጎራደደበት ፣ ታዳሚው በደስታ ሳቅ አወካ…፤ ቬጋሶችን ወክሎ ሰሎሞን አባተ የእንኳን ደህና መጣችሁ አጭር ንግግር አደረገ። መድረኩ በሙዚቀኞችና በመሳሪያዎቻቸው ተሞላ፤ ታምሬ ወልደየሱስ (ቤዝ ጊታር)፣ ረዘነ ሃብቴ(ሊድ ጊታር)፣ ሳምሶን ጁፋር (ድራም)፣ እዝራ አባተ ( ኪ-ቦርድ)፣ ዳዊት አብርሃም (ቴነር ሳክስ)፣ ሰለሞን አባተ (አልቶ ሳክስ)፣ ተሻገር ይልማ (ሳውንድ ሲስተምና ዲጄ)፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው (ድምጻዊ)።

“…ክበር ተመስገን የኛ ጌታ፣ …ክራሬን ብቃኘው፣ ..የከርሞ ሰው..” በድምጽና በመሳሪያ ቅንብር ስራዎች አዳራሹ ደመቀ፤ ስለ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤታችን የተዘጋጀው ጽሁፍ በዶ/ር እዝራ አባተ ቀረበ፤ በየመሃሉ የጌትነት እንየው (በነጻ ገበያ) እና የበእምነት መላኩ (በማንነታችን እንድመቅ)ግጥሞች ተነበቡ፤ የያሬድ ትውስታ በግጥምና በመነባንብ ተደመጠ። አዳራሹ በደስታ እንደተሞላ፤ ሳናውቀውና የዕለቱን ዝግጅት ሳንጠግበው ሰዓቱ ተገባደደ። የዕለቱ ዝግጅት ፍፃሜ ሲቃረብ አንድ ነገር ይቀረን ነበር፤ የእለቱን የክብር እንግዳችንን ጋሼ አማኒ ኢብራሂምን ማክበርና መሸለም።

ጋሼ አማኒ ኢብራሂምና ዶ/ር እዝራ አባተ

እምናከብረውና እምናደንቀው፣ በመምህርነቱና በጥበብ የፈጠራ ስራዎቹ አማካኝነት፣ መልካም አርዓያነት ያለው አሻራ በተማሪዎቹ ላይ ያሳረፈው የክብር እንግዳችን ጋሼ አማኒ ኢብራሂም፣ በኛ አቆጣጠር ከ1970ቹ ጀምሮ በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት በመምህርነትና በርዕሰ-መምህርነት፣ በባህል ሚ/ር መስሪያ ቤት የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በአማካሪነትና በሃላፊነት፣ በሀገሪቱ ከፍተኛ የበዓላትና የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ በሙዚቃ ደራሲነት፣ አቀነባባሪነት፣ አዘጋጅነትና መሪነት፣ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከተ የጥበብ ሰው ነው። እነሆም! ከአያሌ ዓመታት መለያየት በኋላ፣ የቀድሞ ተማሪዎቹ ዳግም ስላገኘነው እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰማን፤ አከበርነው፤ ሸለምነውም።

በዝግጅታችን ላይ ከተገኙ ተጋባዥ እንግዶች መካከል የታወቁና በስራዎቻቸው የተከበሩም ነበሩ፤ በችሎታው የተደነቀውና አሉ ከሚባሉ ጥቂት ድራመሮቻችን አንዱና ዋናው የሆነው ድንቅ የድራም ተጫዋቹ ሳምሶን ጁፋር (ሳሚ)፣ ከዋሊያስ ባንድ መስራቾች አንዱ የነበረውና ከአያሌ የሀገርና የውጭ ሀገር የሙዚቃ ባንዶች ጋር የተጫወተው እውቁ ሊድ ጊታሪስት ረዘነ ሃብቴ፣ ለሕዝብ ባበረከተው የላቀ አግልግሎት በየወቅቱ የተለያዩ ሽልማቶች ባለቤት የሆነው፣ ጋዜጠኛና ሁለ-ገብ ባለሙያው የጸሐይ አሳታሚና ኤዲቲንግ ዳይሬክተር  ትሁቱ ኤልያስ ወንድሙ  ይገኙበታል።

ይህ የመገናኛ ዝግጅታችን የተሳካና ያማረ እንዲሆን፣ የአያሌ ወዳጆቻችንና ቤተሰቦቻችን ድጋፍ አልተለየንም። ያገኘነውን ደስታ እንድንጎናጸፍ ካገዙን ጥቂቶቹ፣ ከአበባ ማበርከት እስከ ፎቶ ማንሳት አገልግሎት የሰጠችው ማኅልየ ሰለሞን፣ ዝግጅቱን ሙሉ በፎቶግራፍ የቀረጸው ናቲ፣ እንግዶችን በማመላለስና ቁርስ በመጋበዝ የተባበረው ሐብታም፣ የዝግጅቱን ተሳታፊዎች በሙሉ ወደ መኖሪያ ቤቷ ጠርታ ራት ያበላችው እውቋ የውዝዋዜ ባለሙያ ገነት አፍለይ፣ ወጪዎቻችንን የተጋሩልን፣ አብይ-አቢሲንያ፣ ሜሞ፣ ሉሲ፣ እናት ገበያ፣ ፣ ላዕከ፣ ገብርኤል፣ አብርሃም ሊሞ፣…እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉና ምግብ በየቤታቸው እየሰሩ የጋበዙን ቤተሰቦች ባለውለታዎቻችን ናቸው።

በሁለተኛው ቀን (ኦክቶበር 26፣ 2017)ያሬዶች ብቻችንን ከተምን። በትናንትናው ዝግጅት ሊቀርብ ታስቦ በጊዜ እጥረት ያደረውንና ኃይሉ ካሳዬ ከሃገር ቤት ቀድቶ ያመጣውን፣ ስለጋሼ አማኒ፣ የቀድሞ ተማሪዎቹና የስራ ባልደረባዎቹ ምስክርነት የሰጡበትን አጭር ቪድዮ ተመለከትን። ከሃገር ቤት ብዙ ጊዜ የራቅን፣ በቪድዮው ላይ የምናያቸውንና የምናውቃቸውን እነ ገዛኸኝ ኃይሌ፣ ሰለሞን ሉሉ፣ በቀለ ደብሬ፣ ዓይናለም ወልዴ፣ ፍቅርተ ደሳለኝ፣ አክሊሉ ዘውዴ፣ ኩስያ ጦሎንጌ፣ ወሰንየለህ መብረቁን ስንመለከት ተመሰጥን። ስለ ጋሼ አማኒም የሚያውቁትን የስራ ጥንካሬና ዲሲፕሊንም በስሜት ሲመሰክሩ አደመጥን።

ከምሳ መልስም በተከታዩ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባን ተወያየን። ከአስራ ስምንት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎችን ጨምሮ ዳግም ለመገናኘትም ወሰንን። በቁምነገሩ ማግስት ዘነበወርቅ ገዛኸኝና ባለቤቷ ሞገድ ጠረጴዛ የሞላ ቁርስ አስተናገዱ፤ ከቁርሱም በኋላ ጨዋታው ደመቀ፣ ሙሉ ቀን ተሳቀ፤ በማያባሩት የፋንታሁን ሸዋንቆጨው ቀልዶችና ያለፉ ትዝታ ወጎች እንባችንን እየጠረግን በሳቅ አወካን፤ የመንፈስ እርካታ እንደ ዓመት ስንቅ ተሸመተ፤ ከባቢው በደስታ ተዋጠ። በነጋታውም ሐብታሙ ቤት ተደገመ፤ ቤተሰብአዊነት ነገሰ…።

የመለያያችን ዕለት ደረሰ፤ የመጨረሻዋንም ምሽት በአበሻ ሬስቶራንት ውስጥ አደመቅናት። በየጨዋታውና ሳቁ መሃል፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው፣ የጋሼ አማኒን የድሮ መዝሙሮችን አዝማቾች እያዜመ አስታወሰን፤ “…ያራዊቶቿ አይነት፣ ኒያላ ዋልያ፤ ውበት ተፈጥሮዋ ልዩ መመኪያዋ…”፣ የእናት ሀገር ፍቅርን ሲያሰርጹብን የኖሩትን እነዚያን ውብ ህብረ-ዝማሬዎች ስናስታውስ፣ ሩቅ.. ዓመታት ወደኋላ ተመልሰን መዝሙሮቹን ስንዘምር የቆምንባቸውን  ቦታዎች ሁሉ  እስከምናስታውስ ድረስ  በትዝታ የነጎድን ነበርን። ጋሼ አማኒ ለሰጠን ጥንካሬና በራስ የመተማመን መንፈስ አመሰገንነው፤ አርዓያነቱን አከበርነው፣ የተሰማንን ሁሉም ነገርነው፤ በሁላችንም ፊት ላይ የደስታ ፍካት ገጽታ ይነበብ ነበር፤ ጋሼ አማኒም ተደሰተ፤ ለአንድ መምህርና ታላቅ ወንድም ከዚህ በላይ ምንስ ሊያስደስተው ይችላል…?!

የከርሞ ሰዎች ይበለን!

(የያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ምሩቃን)

ጌታቸው አበራ
ሕዳር 2010 ዓ/ም
(ኑቬምበር 2017)

ከዝግጅት ክፍሉ፤ ይህ ጽሁፍ ከወራት በፊት መታተም የነበረበት ቢሆንም በመረጃ መጓደልና ከእኛ በኩል በተፈጸመ ስህተት ሊዘገይ ችሏል። ይህንን በመፈጸማችን ጸሐፊውን ጌታቸው አበራንና መረጃውን በማዘግየታችን ያዘናችሁብንን ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን። ገጣሚ ጌታቸው አበራን ለዚህ ጽሁፋቸው፤ ለላኩልን ፎቶዎች ብቻ ሳይሆን ለትዕግስታቸውም ከልብ እናመሰግናለን።


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Literature, Social Tagged With: amani, Ethiopia, Left Column, music, yared

Reader Interactions

Comments

  1. Mulugeta Andargie says

    January 10, 2018 05:31 am at 5:31 am

    ጌታቸው አበራ!! እኔ የማውቀው ጌታቸው መስለሀኝ ምናልባትም በስመ ሞክሼነት: እደማውቅህ አድርጌ ጥቂት ገለጣና ወረፋ: ማለትም በምታራምደው ፖለቲካ ተናበናል!! አሁንም ቢሆን መቶ በመቶ ግምቴን አላነሳሁም!! ሙሉ ለሙሉ እስከማጣራ ድረስ “አይትሃዝለይ!!!“

    Reply

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ፍፁም ብርሃኔና ታምራት የማነ በቁጥጥር ሥር ዋሉ April 16, 2021 10:06 am
  • “ለአንድ ፓርቲ የማደላ ከሆነ ሄጄ እዚያው ፓርቲ እገባለሁ” ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ April 16, 2021 08:45 am
  • “ተዋግተን አይደለም ስንተኛ ብንውል እንኳን መቀሌና አዲስ አበባ አይገቡም” ጄኔራል ባጫ April 14, 2021 09:06 am
  • የስኳር ፋብሪካዎች ተሽጠው ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ተወሰነ April 14, 2021 08:53 am
  • “ኤርትራዊ ነን” በማለት የመኖሪያ ፈቃድ ሲቀበሉ የኖሩ የትግራይ ሰዎችን መለየት ተጀመረ April 1, 2021 02:01 am
  • ምርጫ ቦርድ የኦነግን ጥያቄ ውድቅ አደረገ April 1, 2021 01:15 am
  • “እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ መንግሥት ኮሮጆ አይሰርቅም” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ April 1, 2021 01:09 am
  • መንግሥት ካልደረሰልን አሁንም ግድያ ይኖራል – ነዋሪዎች April 1, 2021 01:04 am
  • በትግራይ ሊዘረፍ የነበረ የእርዳታ እህል ተያዘ April 1, 2021 12:39 am
  • “በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አልደራደርም” March 24, 2021 01:22 am
  • “ከዚህ በኋላ ህወሓት ማለት በነፋስ የተበተነ ዱቄት ነው” ጠ/ሚ/ር ዐቢይ March 23, 2021 11:28 pm
  • እነ ስብሃት ነጋ ጥያቄያቸው ውድቅ ሆነ March 23, 2021 10:23 pm
  • በርግጥ ኢትዮጵያ ዝናብ አዝንባለች? March 23, 2021 10:15 pm
  • አሜሪካ በሴናተሯ አማካይነት “ለቅሶ” ደረሰች March 21, 2021 08:57 pm
  • ቪኦኤ በወለጋ ሆሮ ጉድሩ ለተጨፈጨፉ ኦነግ ሸኔን ከደሙ ንጹህ አደረገ March 19, 2021 04:32 pm
  • ባልደራስና የአብን የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ March 18, 2021 01:56 pm
  • ኤርሚያስ ለገሰ “የወያኔ የፕሮፖጋንዳ ሰራተኛ እያለ የለመደው የቁጥር ጫወታ አለቀቀውም” March 17, 2021 09:54 pm
  • በትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተካሄደ ነው – የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት March 17, 2021 04:54 am
  • ምርጫ ቦርድ ከፈቀደለት ኦነግ በምርጫው እንደሚወዳደር አስታወቀ March 17, 2021 04:30 am
  • በዓለምአቀፍ ሚዲያ ዘጋቢዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው March 15, 2021 11:25 am
  • በሲዳማ/ሀዋሳ 128 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ፤ 2 መትረየስ ከ8,129 ጥይት ጋር ተያዘ March 15, 2021 10:13 am
  • የአክሱም ጅምላ ጭፍጨፋ ተብሎ የተሰራጨው ፎቶ የሐሰት ሆነ March 15, 2021 09:26 am
  • በትግራይ ትምህርት ቤቶች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ March 15, 2021 09:04 am
  • በማይካድራ የጅምላ መቃብር ተገኘ፤ በህወሓት የተገደሉት ቁጥር ከ1300 እንደሚበልጥ ተነገረ March 15, 2021 08:54 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule