ከ698,000 በላይ ተከታዮች ያሉትና ‘Mereja TV’ የሚል ስያሜ ያለው የፌስቡክ ገጽ ከነገ ጀምሮ “በአማራ ክልል ለ10 ቀናት የሚቆይ ዘመቻ የኮቪድ ክትባት በሚል ምንነቱ ያልታወቀ ክትባት ሊሰጥ መሆኑ ተገልጿል” የሚል መረጃ ማሰራጨቱን ተመልክተናል።
ገጹ በተጨማሪም ህብረተሰቡ ክትባቱን እንዳይወስድ የሚያሳስብ መልዕክት ማከሉን አስተውለናል።
መረጃ ቲቪ የተባለው ይህ የፌስቡክ ገጽ ይህን ይበል እንጅ በአማራ ክልል እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ለ10 ቀናት ሊሰጥ ስለታቀደው ክትባት የአማራ ክልል ጤና ቢሮና የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ባለፉት ቀናት በተናጠል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ መስጠታቸውን ተመልክተናል።
በመግለጫዎቹም የክትባቶቹ ምንነት የተገልጸ ሲሆን ዘመቻ አገር አቀፍ ስለመሆኑን ተብራርቷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በትናትናው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከሚያዚያ 24 እስከ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም በክልሉ ሁሉም ዞኖች የማህጸን በር ካንሰር እና የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባቶችን በዘመቻ መልክ እንደሚሰጥ እና ህብረተሰቡ እንዲከተብ ጥሪ ማቅረቡን ተከታትለናል።
በመግለጫው መሰረት በመጀመሪያዎቹ 4 ቀናት ዕድሚያቸው ከ14 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የሚሰጥ ሲሆን ይህም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በጊዜያዊ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል። በቀሪዎቹ 6 ቀናት ደግሞ የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት ይሰጣል ተብሏል።
በተመሳሳይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሰጠው መግለጫ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የማህጸን በር ካንሰር እና የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባቶችን በዘመቻ መልክ ለ10 ቀናት እንደሚሰጥ ማስታወቁን ተከታትለናል። ሀገር አቀፉ የክትባት ዘመቻም በአንዳንድ ክልሎች ከሚያዚያ 17 ጀምሮ መሰጠት መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን በሁሉም ክልሎች እስከ ሚያዚያ 24 መሰጠት እንደሚጀምር በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጾ ነበር።
በከዚህ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የክትባት ዘመቻውን በይፋ መጀመሩን ዛሬ በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገጹ ማስታወቁን ተመልከተናል።
@EthiopiaCheck
ሥርጉተ says
ዬአማራ ህዝብ የትኛውንም አካል ማመን አያስፈልገውም። ስለዚህም ክትባቱ ባን ሊደረግ ይገባል።