የዛሬዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ስበት ማዕከል የሆነው አፄ ምኒልክ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ጥሎ አልፏል። ዘመናዊት ኢትዮጵያ ስንል ከጨረቃ የመጣች እያልን ሳይሆን ግዛታዊ ቅርጿ ሲጠብና ሲሰፋ የነበረችው ኢትዮጵያ በአንጻራዊ ዝማኔ መመራት የጀመረችበት አስተዳደራዊ ዘመን መገለጫ ማለታችን ነው።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ ቅርጽ ከሞላ ጎደል የአፄው የንግሥና ዘመን ውጤት ናት። ከምንም በላይ የጥቁር ዘር የነጻነት ምልክት የሆነው የአድዋ ድል በምኒልክ መሪነት የመጣ ነው። በርግጥ ድሉ የአባቶቻችን የመደማመጥና የመተባበር ውጤት ነው። ምኒልክን አልባ የአድዋን ድል ማስመዝገብ ይቻል (ይሆን) ነበር ብሎ ማመን ይቻላል። ይሁንና በታሪክ የምናውቀውን የአድዋን ድል ያለ ምኒልክ ማሰብ ክርስትናን ያለክርስቶስ፣ እስልምናን ያለነብዩ መሐመድ እንደማሰብ ያለ ቅዥት ነው።
ይህ የታሪክ ሀቅ የማይዋጥላቸው ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ ያላቸው ተገንጣይ ብሔርተኞች እንዳሉ ይታወቃል። አሁንም ቢሆን ማንነትን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ እስካልቀረ ድረስ ይህ አይነት ምልከታ መቀጠሉ ጭራሹኑ እየሰፋ መሄዱ አይቀርም። እውነታው ግን ምኒልክ ከኢትዮጵያም አልፎ የመላ የጥቁር ዘር የነጻነት ምልክት መሆኑ ነው። ከምኒልክ ውርስ ጋር አለመታረቅ በበታችነት የሚሰቃይ ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ አንዳች አትራፊ ነገር የለውም። እናም ታረቀው ምኒልክን!
ሃሮልድ እንደሚለው፣ የታሪክ አረዳድ ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነገር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለች ጠመዝማዛ የታሪክ ጉዞ ባሳለፈች አገር ብሔራዊ መግባባት የለም ሲባል ዘርፎቹ ብዙ ናቸው። ከዘርፎቹ ውስጥ ግን ታሪክ ቀዳሚው ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር ከዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ፤ አገር የማቀናት ዘመቻዎች ጋር ተያይዞ ከተፈጠሩ ችግሮችና ተንከባላይ የትውልድ ዕዳዎች ታጋች (hostage) ከመሆን ይልቅ መታረቅ አለብን።
ምዕራባዊያን በሥልጣኔ ወደፊት መጓዛቸውን ያላቆሙበት ምስጢር ከታሪካቸው ጋር ስለ ታረቁ ነው። የታሪክ መሰረቶች ላይ የሚቆሙ ልዩነቶችን መሻገሪያው ብቸኛ መፍትሔ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ብቻና ብቻ ነው። ከምኒልክ ጋር የመታረቂያው አንዱ መንገድ ይሄው ነው!
ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ከታሪካችን ጋር እንድንታረቅ ድልድይ ይሆነናል። ያኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም የባህል ቡድኖች (በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅና በምዕራብ ያሉትን) እንዲያካልል ማድረግ ይቻላል። ታሪካችንም የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” በሚል ሳይሆን ዜግነታዊ መሰረት ባለው መልኩ አካቶነት ያለው የጋራ ታሪክ ማንበብ እንችላለን። ይህ መንገድ… በደም የተዋጀው ቆይታችን በእኩልነት ስሜት አንድነታችን በፅኑ መሰረት እንዲቆም ያደርገዋል። ያኔ ኢትዮጵያዊነት የብዙሃኑ ስሜት ይሆናል። በዚህ አግባብ የኢትዮጵያዊነት መገለጫውን ፈልጎ የሚያጣ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ኃይል አይኖርም።
ወደ አባ ዳኛው የአመራር ጥበብ ስንመለስ፡- የምኒልክ ድል የእርሱ እና የብርሃናማዋ ንግሥት ብቻ አልነበረም። በምኒልክ የንግስና ዘመን ለተመዘገቡ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች፤ ዋልታና ማገር የነበሩ አባቶችን ውለታ መርሳት የሚቻል አይደለም። ራስ ጎበና ዳጬ፣ ደጃች ባልቻ ሳፎ፣ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ መኮንን ወ/ሚካኤል ጉዲሳ፣ ራስ ዳርጌ፣ ራስ ወልደገብርኤል፣ ራስ መንገሻ አንቲከም፣ ራስ ሚካኤል (መሐመድ አሊ)… እያልን ከምንዘረዝራቸው ታላላቅ የጦር አበጋዞች ከአማራው፣ ከኦሮሞና ከደቡብ የተውጣጡ የአገር ምስረታው የፊት መስመር ተሳታፊዎች ናቸው።
እንደራስ ጎበና ዳጬ ያለ ጀግና የጦር አበጋዝ ሰባት ግዛቶችን (የደቡብና የምዕራቡን) (ጥንተ-ርስትና ግዛቶቹን) የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ችሏል። ዛሬ ላይ “ምኒልክ የእኛ ብቻ ነው” ሊሉ የሚቃጣቸው የታሪክ ኑፋቄ የተጫናቸው ዝንጉዎች የምኒልክ ብርቱ ቀኝ እጅ የነበሩት የጦር አበጋዞች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የደከሙትን ድካም፣ የከፈሉትን ዋጋ ከዚህ አንጻር በአደባባይ እየካዱ መሆኑን ይሰመርበት።
ምኒልክ ዘር አይመርጥም፣ ስበቱ ‘ፖወር’ ነው። ከብዙ ማሳያዎች አንድ፡- የራስ ጐበና ዳጬ ልጅ ወዳጆ ጐበና የምኒልኳን ሸዋረገድን አገባ፤ በውጤቱም ወሰንሰገድ የተባለ ልጅ ተወለደ። ይህ ልጅ በአሥራ አራት አመቱ ባይቀጭ የምኒልክ አልጋ ወራሽ ይሆን ነበር። በዚህ አግባብ ምኒልክ ለጐጃም ሰው ሳይሆን ለቱለማ ኦሮሞ ይቀርባል። ከበጌምድር ሰው ይልቅ የሸዋ ኦሮሞ የምኒልክ የመጀመሪያ የንግስና ዘመናት የኃይል ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። የመንዝም ሆነ የየጁ ገበሬ ለምኒልክ ገባር ኢትዮጵያዊ ነበሩ። የአድዋ ሰውም ሆነ የወላይታ እኩል የምኒልክ ገባሮች ናቸው። ሌላውም እንደዛው!
በምኒልክ ሃውልት ላይ ተጽፎ የሚነበበው መልዕክተ-ምኒልክ ምን ይላል መሰለህ፦ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው”። አየህ ምኒልክ ግዛታዊነትን የሥልጣን መወጣጫ ብቻ ሳይሆን ያደረገው በግዛቲቱ የሚታመኑለትን መሳፍንቶችም ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪነት ማውጣጣት ችሏል። ከጀምሩ በቴዎድሮስ ቤት ታላቅ ራዕይን ወርሷልና በሰከነ አመራሩ ኩምሳ ሞረዳንም ሆነ አባ ጅፋርን በጥበብ ገባሪው ማድረግ ችሏል።
እንደዚያኛው ቴዎድሮስን መንገድ መርቶ እንደሸጠው መካር አልቦ ንጉሥ (አጼ ዮሃንስ) “ሰማይ አምድ የለው፤ እስላም አገር የለው” የሚል አዋጅ አላስነገረም፤ ይልቁንስ በየደረሰበት ስፍራ ሁሉ “ሁሉም ባባቱ ይደር” የሚል አዋጅ ነበር ያስነግር የነበረው። አባ ጅፋር ምኒልክን ያከበረው ለምን ይመስልሃል? ‘እኔን ምሰል’ እንደማይለው ቀድሞውንም አውቆታል-ጅፋር ነፍሴ! እንጅማ ለ“ካፊር” ይገብር ነበር? የማይሆነውን!!
ሲጠቃለል፡- ምኒልክ የዘመኑ መሪ ብቻ ሳይሆን፤ ጥቁር ሰው መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ፤ የነጮች ጌታ! የአድማሳዊ ስብዕና ባለቤት ነበር!!
መንጋው ብዙ ብዙ ሲል ወደን አይደለም ዝንተ-ዓለም ምኒልክ የምንለው!
[‘ከአንድ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት አለች’ የሚለው አባባል መነሻው ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ነው። ያለ እቴጌዋ ፥ ምኒልክ የጥቁር ዘር ብርሃን መሆን ባልቻለ ነበር። ካላመንክ በ Chris Prouty የተፃፈውን “Empress Taytu and Menilk 1883-1910” መጽሃፍ ፈልገህ አንብብ]
ምኒልክ ጥቁር ሰው፤ የነጮች ጌታ!! ምንጭ፡ Gulilat Geletaw
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply