በመከላከያ ሰራዊት መስዋዕትነት ከህወሓት እየተላቀቁ በሚገኙት አካባቢዎች የአሸባሪው ህወሓት ድብቅ ገመና መጋለጡን ቀጥሏል።
የሽብር ቡድኑ ቁንጮ አመራሮች አስገድደው በጦርነት ላሰለፏቸው ታጣቂዎች እንኳ ምንም አይነት ርህራሄ እንደሌላቸው በጨርጨር የተገኘው ጅምላ መቃብር ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ከጨርጨር ከተማ በስተምስራቅ በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎችና የጦር አመራሮች የጅምላ መቃብር ስፍራ የተገኘ ሲሆን፥ ይህም የሽብር ቡድኑ ቁንጮ አመራሮች በትግራይ ህዝብ ደም በስልጣን ለመቆየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማሳያ ሆኗል፡፡
የጅምላ መቃብር ስፍራው መለያ ኮድ ያለውና በአንዳንዱ መቃብር ከ3 እስከ 5 አስከሬን በጋራ የተቀበረበት ሲሆን፥ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎቹን የቀበራቸው እንደ ኃላፊነታቸው እና ማዕረግ ደረጃቸው በመቃብራቸው ላይ ምልክቶችን በማድረግ ነው።
ተዋጊ የሚባለውን ኃይል በአንድ መቃብር ውስጥ ከ3 እስከ 5 እስከሬን እንዲሁም ለብቻቸው ኮድ ተሠጥቷቸው የተገኙ የመቃብር ስፍራዎች ደግሞ የአመራሮች መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የሞቱ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በአንድ ዋሻ ውስጥ አስክሬናቸው በሬሳ ሳጥን ውስጥ የተገኘ ሲሆን፥ በዋሻ ውስጥ በሬሳ ሳጥን የተገኙት አስከሬኖች በልዩ ሁኔታ የተቀመጡ በመሆኑ ውጊያውን ሲመሩ የነበሩ የሽብር ቡድኑ አመራሮች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
የተገኘው የጅምላ መቃብር ስፍራ በሶስት የተከፈለ ሲሆን፥ የመጀመሪያው የቡድኑ ታጣቂዎች የተቀበሩበት እንዲሁም ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የሽብር ቡድኑ መካከለኛ አመራሮች እና ጦርነቱን ሲመሩ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች የተቀበሩበት ስፍራ ነው፡፡
አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ አሰቃቂ የክህደት ጥቃት በመፈጸም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኖ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት ጥቃቱን ተከትሎ በወሰደው ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ መቀልበስ የቻለ ሲሆን፥ የተናጥል የተኩስ አቁም በማወጅም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል፡፡ (ኢዜአ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply