
ከሰሞኑን ከትግራይ ክልል አንድ ምሥጢራዊ ሰነድ ሾልኮ ወጥቶ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል። በማኅበራዊ ሚዲያዎችም በርካቶች እየተቀባበሉት ይገኛሉ።
ምሥጢራዊ ሰነዱ ፥ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር (በብዛት ኤርትራውያን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር የሚመለከት) እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተጠና ሰነድ ሲሆን በ4 ክፍሎች የተከፋፈሉ 69 ገፆች አሉት።
በሰነዱ በጥናት የተለዩ የወንጀል ተግባራት ፦
* ሥልጣን ያለአግባብ በመጠቀም
* በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በመያዝና በማዘዋወር (መኒ ላውንደሪንግ money laundering)
* ሰው ማፈንና መሰወር
* በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ከአገር ወደ አገር ማዘዋወር
* የመንግሥት ስራ ምቹ ባልሆነ መንገድ መምራት
* ኃላፊነት ባልተገባ መንገድ በመጠቀም
* ሙስና
መፈፀማቸውን ያረጋግጣል።
በሰነዱ በተጠቀሱ የወንጀል ተግባራት በሠራዊት አመራር ያሉ የነበሩ የጀነራል መዓርግ ካለቸው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እስከ ቀበሌ አመራር ያሉ አስተዳዳሪዎች ነጋዴዎችና ሌሎች የሚገኙባቸው 231 ተጠርጣሪዎች በስምና አድራሻቸው ተጠቅሷል።
ሰነዱ በሕገ-ወጥ መንገድ የተዘዋወሩ ኤርትራውያን ስም የተዘዋወሩበት ቦታና ቀን፣ ያረፉባቸው ሆቴሎች እንዲሁም ለሕገወጥ ዝውውሩ ገንዘብ ገቢ ያደረጉባቸው የባንክ የሂሳብ ቁጥሮች ሰፍረዋል።
የጥናት ሰነዱ የሰው ማስረጃ፣ የድምፅ ቅጂ፣ እንዲሁም በድብቅ የተቀረፀ ምስል ያካተተ እንደሆነ ይዘረዝራል።
በሰነዱ በቀንደኛ ተጠርጣሪነት ከተጠቀሱት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ የሆኑት ተወልደ ገ/ትንሳኤ (ዕምበብ) በቅርቡ ከአገር መውጣታቸው ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ከፋና ቴሌቪዥን በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ጽህፈት ቤት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በቅርቡ ፋና ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሯቸውን ንግግሮች አስመልክቶ የተቃውሞ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫው አቶ ጌታቸው ለፋና ቴሌቪዥን የሰጡትን ቃለመጠይቅ “የሕግ ልዕልና ለማረጋገጥ ያለመ ሳይሆን የሕዝቡን የትግል ታሪክና ቀጣይነት የሚያጎድፍና የሚያጨልም በቂም በቀል የታጨቀ ነው” ሲል ገልፆታል።
“በሥልጣን ቆይታቸው የታዩ ወድቀቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ አካል ሲያላክኩና ከሳሽ ሲሆኑ ሰንብተዋል “ያለው ጽ/ቤቱ” ይህ ወደ ሚድያ ፕሮፓጋዳ የወረደ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው” ብሏል።
የጽ/ቤቱ መግለጫ ፤ አቶ ጌታቸው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስመልክቶ በብዙ ጥረት ተጠንቶ ወደ እጃቸው የገባ ኮፒ ያልተደረገ ሰነድ በወቅቱ ተጠያቂነት ሳያረጋግጡ ቀርተው አሁን በማህበራዊ ሚድያ እንዲሰራጭ አደርገዋል ሲል ይከሳል።
“ይህ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ሊያጠቋቸው የፈለጓቸው ግለሰቦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጎዳ በጥናቱ ተሳትፎ የነበራቸውና አካላትና ቤተሰቦቻቸው ጭምር ለአደጋ የሚያጋልጥ የነውር ነውር ነው” ሲል በምሬት ወቅሷል።
“የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመሆናቸው ብቻ ያወቁትን ምሥጢር እንደ አንድ የሕዝብ ብሔራዊ ጉዳይ እሰከ መጨረሻ መጠበቅ ሲገባቸው ለርካሽ ገበያ ማቅረባቸው ማንነታቸው ያሳየ ተግባር ነው” ሲል አቶ ጌታቸው ረዳን ወርፉዋቸዋል።
የፕሬዜዳንት ጽ/ቤቱን መግለጫ ተከትለው ወድያውኑ ምላሽ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ “የተጠናው ጥናት ተተንተርሶ ወደ እርምጃ እንደማይገባ ስላወቅኩኝ ወደ ሚመለከተው የበላይ አካል መረጃውን ልኬዋለሁ” ብለዋል።
ሚንስትሩ “በጥናት ሰነዱ መሰረት ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ከሚገባ ተጠያቂዎች አንዳንዶቹ ከአገር ወጥተዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
“‘ሰው መሸጥ (slave trading in modern parlance) ለትግራይ ሕዝብ የማይመጥን ወንጀል ነው’ የሚል አገላለጽ በፕሬዜዳንት ጽሕፈት ቤት በወጣው መግለጫ የለም” ያሉት አቶ ጌታቸው “ሰነዱ ግለሰቦችን ከማጥቃት ባለፈ የሕግ ልዕልና እንዲረጋገጥ ያለመ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ “በጥናት ሰነዱ የተቀመጠው ሐቅ ነው ጥቂት ወንጀለኞች ለማዳን ሲባል በሕዝብ ስም መነገድ ይቁም” ብለዋል። (@tikvahethiopia)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply