ስለ አዲስ አበባ ፍትኅ የሚጠይቅ የማኅበራዊ መገኛ ዘዴዎች ዘመቻ ዛሬ በዋናነት በትዊተር ላይ ተጀመረ።
ዘመቻው ዛሬም እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ የገለጡ ሲኾን፦ “በአዲስ አበባ የታየውን የመሬትና የኮንዶምንየም ምዝበራ በመቃወም” ፍትኅ ለመጠየቅ የተጀመረ መኾኑንም አክለዋል።
በዘመቻዉ ላይ “#ፍትህለአዲስአበባ”፤ “#አዲስአበባ” እንዲሁም “#ኢትዮጵያ” የሚሉ አሰባሳቢ ቃላት (ሐሽታጎች) ጥቅም ላይ ውለዋል።
የዘመቻው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ከተማ “ተፈጸመ” ያሉትን አድሏዊ አሠራር እና በደል በመዘርዘር ተቃውሟቸውን እና ቅሬታቸውን ሲያስተጋቡ ተስተውለዋል።
የዘመቻው አስተባባሪዎች ባሰራጩት ጽሑፍ፦ “በኢ/ር ታከለ ኡማ አስተዳደር ዘመን በአዲስ አበባ የታለያዩ አድሎአዊ አሠራሮች፤ ጥቅመኝነት፤ የህዝብን ሃብት ማባከን የመሳሰሰሉ ጥፋቶች ተስተውለዋል” ብለዋል።
ግድፈቶች ብለው ከዘረዘሯቸው ነጥቦች መካከል፦ “በዋነኛነት የሚጠቀሰው የመሬት ወረራና ፍትሃዊ ያልሆነ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ” መኾናቸውን አስምረውበታል። “እነዚህን ግድፈቶች አውጥተው ሲቃወሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት አራማጆች የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እና እስር ሲደርስባቸው” ማየታቸውንም አክለዋል። አዘጋጆቹ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናትን ዋቢ በማድረግም “ይህንን የሚያረጋግጥ ሆኗል” ብለዋል።
ኢዜማ ከሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ከተከለከለ በኋላ “በአዲስ አበባ ከተማ የሚፈፀም የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ ጋር በተያያዘ” ጥናት ማድረጉን ገልጦ የጥናት ውጤቱን ይፋ አድርጎ ነበር።
ኢዜማ በጥናቱ ከ250ሺ ካሬ በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ ወረራ የተያዘ መኾኑን፤ ከብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለተገባ መንገድ ለግለሰቦች መተላለፋቸውን እንደሚያሳይም የማኅበራዊ መገናኛ ዘመቻው አዘጋጆች በጽሑፋቸው አክለዋል። የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በማኅበራዊ መገናኛ አውታራቸው ባሰራጩት መልዕክት በአስተዳደራቸዉ ዘመን ተከሰተ የተባለውን ምዝበራ እና አድሏዊ አሠራር አስተባብለዋል።
“ለ20ሺህ አርሶ አደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተም ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ ነው” ብለዋል። አስተዳደራቸው በወቅቱ የወሰደውን ርምጃም፦ “ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ጠንካራ የሆነ ርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው”ም ብለዋል። “ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሠራ ህንጻ ዘበኛ እና ተሸካሚ ሆነው ከቀሩ 67ሺህ አባወራዎች መሃል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20ሺህ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም። ስህተትም ከሆነ ለ67,000ውም አለመስጠታችን ነው። ከዚህ ውጭ በሕገወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም አይነት ቤት የለም” ብለዋል።
የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዘመቻው አስተባባሪዎች፦ እንደ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ እንባ ጠባዊ ተቋም እና ሌሎች የሰብአዊ ድርጅቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በዋናነት “አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጫና እንዲያደርጉ መጠየቅ” ግባቸውን መኾኑን ጠቅሰዋል። በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ከዚሕ ቀደምም ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በተለይ አኹን እስር ላይ በሚገኙት አቶ እስክንድር ነጋ በኩል ተደጋጋሚ መግለጫዎች ሲሰጥ እና ተቃውሞው ሲስተጋባ መቆየቱ የሚታወስ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ወገኖችም ቅሬታቸዉን ሲያሰሙ ነበር።©ጀርመን ድምፅ
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply