በተለያየ የቅጽል ማዕረግ የሚሞሸረው ጃዋር መሐመድ “ስለቀጣዩ የፖለቲካ ሂደትና አዲስ ስትራቴጂ” ለመነጋገር አዲስ አበባን ሲለቅ በምርጫ እንደሚሳተፍ ለሚከተሉት ሁሉ መልዕክት አስተላልፎ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ “ጠቅላይ ሚኒስትር” በሚል ደጋፊዎቹንና እየለመነ አበል የሚሰጣቸው የሚዲያ ባለሟሎቹ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።
አዲስ ፓርቲ ያቋቁም ወይም ካሉት ፓርቲዎች ጋር የመቀላቀል ሃሳብ እንዳለው ለጊዜው እንዳልወሰነ፣ ነገር ግን ወደ ምርጫ የመግባቱ ጉዳይ ያለቀለት እንደሆነ ጃዋር ያስታወቀው ከምርጫው በፊት የድምጽ ስሌትን በማስላት እንደሆነ በይፋ አስታውቆም ነበር።
በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች፣ በካናዳ፣ በኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ጀርመንና እንግሊዝ የቅስቀሳ ዘመቻውንና የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባሩን ካከናወነ በኋላ ለጀርመን ድምጽ በሰጠው ቃለ ምልልስ ወደ ምርጫ ለመግባት አለመወሰኑን ይፋ አድርጓል።
የኦዲፒ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ ጃዋር በምርጫ እንደሚወዳደር ይፋ ማድረጉን ተከትሎ “እናመስግናለን አያቶላ” ሲል የጃዋር ውሳኔ ህግን ለማስከበርና በጨዋታው ህግ ለመዳኘት፣ ብሎም የጨዋ ጨዋታ ለማካሄድ ጠቃሚ ውሳኔ ሲል አስተያየቱን በራሱ ፌስ ቡክ ግርጌ አስቀምጦ ነበር።
ጃዋር “ተከበብኩኝ” ማለቱን ተከትሎ ነውጠኞች ለገደሏቸው 86 ወገኖችና ለደረሰው ውድመት ተጠያቂ እንደሆን በተደጋጋሚ ጣት የተቀሰረበት፣ ከዚሁ ነውጥ ጋር በተያያዘ በእምነት ቤቶች ላይ በደረሰ አስነዋሪ ጥቃትና የእምነት ተቋማት ቃጠሎ፣ የተደራጀ መሪ ባይኖረውም በሄደበት እየደረሰበት ያለውን ተቃውሞ አስቀድሞ ለመሸሽ፣ አጀንዳ ለማስቀየርና ከፍተኛ ገንዘብ ለመሰብሰብ “ጠቅላይ ሚኒስትር” እንደሚሆን ያወጀው ጃዋር፣ የገንዘብ ለቀማውን ካጠናቀቀ በኋላ በምርጫው እንደማይወዳደር ፍንጭ መስጠቱ መነጋገሪያ ሆኗል።
“ስሜ ሌሊሴ ነው” ያለችን የሜኖሶታ ነዋሪዋና የጃዋር ተከታይ “ዜናው አስገርሞኛል። ጃዋር 350 ድምጽ እናገኛለን። መንግሥት እንሆናለን” ብሎ ነበር በሳምንት ውስጥ ምን ተፈጠረ?” ስትል ግራ በመጋባት ትጠይቃለች። በካናዳ በተመሳሳይ ጃዋርን ማግኘት የቻለው ሱሌይማንም እንደሚለው “የጃዋር ሥራ ልክ ዕቁብ በልቶ እንደመካድ ነው፣ ያስገርማልም” ብሏል።
ጃዋር እና ህወሃት ተመሳሳይ “የፍቅር” ቋንቋ ማውራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ሁለቱም መደመርን ይኮንናሉ። የብልጽግና ፓሪቲ መቋቋሙን ያወግዛሉ። የፌደራሊስ ኃይሎች የሚል ኅብረት በማቋቋም ተመሳሳይ ዓላማ ለማራመድ እየሠሩ መሆናቸውን ይነገራል። ሥራም ጀምረዋል። የጃዋር ሚዲያ አውታሮችም ይህንኑ እየዘገቡ ነው። ይህንኑ ቡድን የሚቀላቀሉ አካላትን ቃለ ምልልስ በማድረግ እየመለመሉ ይገኛል።
“የፖለቲካ ንግዱ ጦፏል። ብራንዱ ‘ፌዴራሊስት’ ይባላል። ለገበያ የቀረበዉ ደግሞ የሲዳማ ክልልነት ነዉ። ነጋዴዎቹ ‘የሲዳማ ክልል መሆን ለፌዴራሊስት ኃይሎች ተጨማሪ አቅም ነዉ’ ይሉናል። ይህ አባባል እዉነት ይመስለኛል። ግን ዋነኛ ጓደኛቸዉ ደግሞ ህወሓት ሆኗል። የአፋር እና የሱማሌ ቋንቋዎችም ለፌዴራል የሥራ ቋንቋነት መታጨት ነጋዴዎቹን ቅር ያሰኛል። ታዲያ ምን ማለት ይቻላል? አንድ ሰዉ ወይም ቡድን ፌዴራሊዝምን ለ27 ዓመታት ካፈነዉ ህወሓት ጋር ወዳጅ ሆኖ የአፋርን፣ የሶማሌን እና የሌሎች ወገኖችን ወደ መሀል መምጣት እየተቃወመ እንዴት ራሱን “የፌዴራሊስት ኃይል” ብሎ ይጠራል? ገበያተኛዉስ እንዴት ይህን ይገዛል? በጣም ይገርማል” ሲሉ አቶ ታዬ ደንደአ በወቅቱ የምርጫውን ምናባዊ ስሌት በሾርኔ ቢያስታውቁም ዛሬ ነገሮች መቀየራቸው ጃዋርን ውሳኔ አልባ እንዳደረገው እየተሰማ ነው።
የሲዳማ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ክልሉን እያስተዳደረ ያለው አካል ለዶ/ር ዐቢይና አመራራቸው እጅግ ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ ብልጽግናን እንደሚቀላቀሉ ይፋ ማድረጋቸው፣ አምስቱ አጋር ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ብልጽግናን መቀላቀላቸው፣ ከህወሓት በቀር ሶስቱ እህት አማች ድርጅቶች መስማማታቸውና የሁሉም ውሳኔ በማተም መታተሙ ጃዋር ያሰላውን 350 ወንበር ስሌት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ ለጃዋር መሐመድ ማፈግፈግ እንደዋና ምክንያት እየተጠቀሰ ነው።
በተደጋጋሚ “አበደን” በማለት በሄደባቸው ስብሰባዎች ሲያስጨበጭብና ሲያስጮህ የከረመው ጃዋር ሲጀመር (ፓስፖርቱን) “ወርውሬ አፍንጫቸው ላይ እጥለዋለሁ” ያለውም የአሜሪካ ዜግነት ለመቀየር የጀመረው አንዳችም ሂደት እንደሌለ እናውቃለን የሚሉ “ጉዳይ የዕቁብ መብያና፣ ከዚያም “አበደን አልከፍልም” እንደ ማለት ነው” ሲሉ የስላቅ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
ሰለሞን ጋዲሣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የማይሽር የቅርብ ጊዜ ጠባሳ ከጣለው ህወሓት ጋር ተመሳሳይ አቋም በማራመድ ላይ የሚገኘው ጃዋር፤ “ለዑካን ልከን ይቅርታ እንጠይቃለን” ካለበት ቀን ጀምሮ ከሙሉ ቤተሰቦቹ ጋር አቋም በመያዝ ለጃዋር ጀርባቸውን እንደሰጡ ለጎልጉል አስታውቋል።
ሰለሞን ጉዳዩን በቅርብ እንደሚከታተል በመግለጽ ጃዋር የገንዘብ ማሰባሰቡን ዘመቻ እያጠቃለለ ባለበት ሰዓት አቶ ለማ መገርሳን ወደ ቪኦኤ መላኩን ያምናል። “ጃዋር የአቶ ለማ ቃለ ምልልስ ለምን ታፈነ፣ እንዳይተላለፍ ተደረገ” በሚል ዘመቻ ማካሄዱ ጉዳዩን እሱ እንዳቀነባበረውና አቶ ለማ ምን እንዳሉ መረጃ እንዳለው ያረጋግጣል። ቪኦኤ ወሬውን አመጣጥኖና ከሌላኛው ወገን የአጸፋ መልስ ጠብቆ ለማቅረብ ሙያዊ ግዴታውን እንዳይወጣ አስቀድሞ የጮኸው አቶ ለማን ዶ/ር አብይ በኦሮሞ ዘንድ እንዲጠሉና የብልጽግና ፓርቲ ኅብረት ውስጥ ጉልህ ሚና የሚጫወተው ኦዲፒ እንዲፈረከስ ታስቦ ነው።
ለጃዋር ቅርብ የሆኑ ለጎልጉል ወዳጅ እንደገለጹት አቶ ለማ በቃለምልልሳቸው ወቅት ለልዩነታቸውና ለቅሬታቸው ያቀረቡት ምክንያት የላላ፣ ውሃ የማያነሳና በታሰበው ደረጃ የፖለቲካ ትኩሳት የፈጠረ አለመሆኑ፤ ቃለምልልሱ እንደጠበቀው አቧራ አለማስነሳቱ ጃዋርን ክፉኛ አሳዝኖታል።
“እንደ አገር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል” በሚል የተመሠረተው “የኦሮሞ አመራር ጥላ” የተሰኘ መድረክ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ አንድነትና ነፃነት ግንባር፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል። የዚህ መድረክ ሰብሳቢ የተደረጉት አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። በዚህ አደረጃጀት ደግሞ አቶ ሌንጮ ለታ፣ አቶ ገላሳ ዲልቦ እና ዶ/ር ዲማ ነገዎ ደግሞ አማካሪዎች ተደርገዋል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድና አቶ አበራ ቶላ የዚህ አደረጃጀት አስተባባሪዎች ሆነው ተመርጠዋል።
ሰለሞን ይህንን ካስታወሰ በኋላ አቶ ለማ “ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር መክሬ ወደፊት እወስናለሁ” ማለታቸው በእነ ጃዋር ገፊነት አሁን እንዲመሩት የተደረገውን የፓርቲዎች መድረክ በገሃድ ወደ ምርጫ ይዘው እንዲሄዱ የተበጀ መንገድ መሆኑንን እንደሚያሳይ ይጠቁማል።
ጃዋር ዜግነቱን ቀይሮ ወደ ምርጫ ለመግባት ፍላጎቱ እንኳን ቢኖረው የማስፈጸሚያ ሂደቱ ከሚፈልገው ጊዜ አንጻርና ሚዲያውን ለማንም ለመልቀቅ ስለማይፈቅድ አቶ ለማን ይዞ በእርሳቸው አማካይነት በትግሉ ወቅት የተንቦራጨቀበትን የኦዲፒ አደረጃጀት ቆርጦ የመውሰድ ፍላጎቱ የቆየ መሆኑንን ሰለሞን በበርካታ ማስረጃዎች አስደግፎ ያብራራል። አንዱና ትልቁ ማሳያ በሁሉም ጉዳይ በትሩ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ሲወርድ አንድ ቀን እንኳን አቶ ለማ አለመነካታቸው ነው።
በኦሮሚያ የርዕሰ መስተዳድር ዘመናቸው ግድያ፣ መፈናቀል፣ እንዲሁም እጅግ የተወሳሰበ አስተዳደራዊ ክሽፈትን ማስተካከል አቅቷቸው የነበሩት አቶ ለማ፤ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ ከተተኩ በኋላ አሳሳቢ የነበረው ዜጎችን ማፈናቀል መገላታትቱ የአቶ ለማን የመምራት ብቃት ማነስ ያሳየ ለመሆኑ ማሰረጃ የሚያቀርቡ አሉ።
ሰለሞን እንደሚለው “የሚሰማኝ ካጣሁ ቆየሁ” በማለት የተናገሩት አቶ ለማ፤ ብቃት የሌላቸው፤ ሃሳብ አመንጭተው ሃሳባቸውን ለመሸጥ የማይችሉ መሆናቸውን በራሳቸው አንደበት ይፋ ማድረጋቸው አይከፋም ባይ ነው። ሲያስረዳም “ሃሳብ አፍልቆ፣ ለሚቃወመው ሃሳብ አማራጭ አቅርቦ የማይታገል ከፍተኛ አመራር በሃሳብ ገበያ የተሸነፈ ነው” በዚህ መመዘኛ ጃዋር አቶ ለማን እንዳሻው ቢያደርጋቸው አይገርምም ሲል ያክላል።
የቪኦኤዋ ዘጋቢ ሌሊሴ ከአዲስ አበባ ስታናግራቸው መሠረታዊ ጥያቄ አለማቅረቧና አለመከራከሯ እንጂ ከዚህም ባለፈ እርሳቸውን ጠልቅ ብሎ የማየት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ሰለሞን አክልሏል። በመጨረሻም አቶ ለማ ከኦዲፒ የተወሰነ ኃይል ወስደው ድርጅቱን የመሰንጠቅ ሚናቸውን ለመወጣት ካልሞከሩ የሚያሳብ ነገር እንደሌለ፣ ከሞከሩ ደግሞ የማዕከላዊ ኦሮሚያና የሸዋ ኦሮሞ ድጋፍ ሊነፍጋቸው እንደሚችል ግምቱን ሰጥቷል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply