የሚዲያ አውታሮች ከውስጥም ከውጭም፣ የመንግሥትም ሆኑ የግል፣ የተገዙም ሆኑ በሊዝ የተያዙ፣ በደመ ነፍስ የሚጓዙትን ጨምሮ ሆን ብለው አስበውበትም ሆነ ሳያውቁት የጃዋር ሰለባና አንደበት ሆነዋል። አንዳንዶቹ በሳል የሚባሉት የሚዲያ አውታሮች ተቆጣጣሪ ኤዲቶር ያላቸውም አይመስሉም። “በድንገት በጃዋር ላይ በለሊት ከበባ መደረጉን ተከትሎ” እያሉ እሳቱ ላይ ነዳጅ ያርከፈክፋሉ። የዘገቡ መስሏቸው የጃዋር አፈቀላጤ በመሆን በትጋት ያገለግላሉ።
ጃዋር “ተከበበ ” የተባለው በማን ነው? ማን ከበበው? እንዴት ተከበበ? ስንት ሠራዊት ከበበው? ለምን ተከበበ? በሚል ማጣራቱ ቢቀር እሱ ያለውን ጠቅሶ መዘገብ እንዴት ለአንድ ሚዲያ ይከብዳል? ከደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋና ቁሳዊ ጥፋት ለማምለጥ እየዋለ ሲያድር ከሚባለው ውጪ “በሌሊት ጠባቂዎቼ እንዲነሱ ታዘዘ” የሚለውን ጠቅሶ ለመዘገብ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
ጃዋር ሳይከበብ “ተከበብኩ” ማለቱን ተከትሎ የተነሳው የመንጋ አድማ የተጨፈጨፉትን ንጹሃን ነፍስ ማሳነስና ጃዋርን ከተጠያቂነት ለማዳን “መከበቡን ተከትሎ” በሚል መዘገቡ ብቻ ሳይሆን መንጋውን በመቃወም በሌላ በኩል የተሰለፉና ዋጋ ከፍለው የከተማቸውን ሰላም ማስጠበቅ የቻሉትስ ለምን ሽፋን አላገኙም? በግልጽ በአደባባይ ወጥተው “ኢትዮጵያ አገራችን” በማለት እያዜሙ የዜግነት ግዴታቸውን የተወጡትና የጥፋት መንጋውን ፊትለፊት የተጋጠሙትን ለምን መዘንጋት አስፈለገ? በተለይ “ተዓማኒው ቪኦኤ”፣ “ቢቢሲ አማርኛ”፣ ወዘተ ይህንን መዘንጋታቸው፤ ዘገባዎችን ለማመጣጠን አለመቻላቸው “ለምን” ተብሎ ሊያስጠይቅ የሚችል ነው።
የኦነግ ሸኔን የተባለ ተዋጊ፣ ዘራፊና ወንበዴ ቡድን ጫካ ለጫካ እየፈለጉ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚያናገሩት በምንዛሬ የሚከፈላቸው የሚዲያ አውታሮች ምነው ቦሌ ጃዋር መኖሪያ ሰፈር የሚኖሩ ነዋሪዎች በአእምሮ ቢሱ መንጋ በየአስር ሜትሩ ሲበረበሩ ለምን ይሆን ዝምታን የመረጡት? ለምንስ ይሆን በወጉ ሽፋን ያጣው?
“ቤታችንን በሩቁ እያየን እንመለሳለን። ዕቃ ማውጣት፣ ልብስ መቀየር አቅቶን ንብረታችንን በሩቅ እያየን አለን። በቃ መኖሪያችን ለጊዜው የእኛ አይደለም። ልጆቻችን በየሆቴሉና በየዘመድ ቤት ናቸው። ለአንድ ሰው ሲባል የሰፈሩ ሰላማዊ ነዋሪዎች፣ ታማሚዎች፣ ህጻናቶች፣ አረጋዊያን ዜጎች ለምን ይሰቃያሉ? ምን ባጠፉ ይህ መከራ ይደርስባቸዋል? አክቲቪስት ማለት ለሌሎች ተቆርቋሪ መሆን ማለት ከሆነ ጃዋር ለምን የሌሎች ስቃይ አያሳዝነውም? ዳሩ ምን ያደርጋል…? ”
ይህን ያሉት አንድ ሲፈርዳባቸው ጃዋር ጎረቤታቸው ሆኖ መከራ እያዩ ያሉ ዜጋ ናቸው። እኚህ ሰው ብዙ ተናግረዋል። ጃዋር ማሰብ ለተሳናቸው ጀሌዎቹ በሬ እያሳረደ፣ ጫት እያቀረበ፣ ውሃና ተጨማሪ ጠንከር ያሉ መጠጦችን እያስጋዘ ይቀልባል። ነዋሪዎች ፍትህ ማግኘትና ለረዥም ዓመታት ከኖሩበት ቤታቸው መግባትም መውጣትም ተከልክለው አሉ። “ታላላቆቹ” የሚዲያ አውታሮች በዕቅድም ይሁን ባለማወቅ የጃዋር ኦ.ኤም.ኤን. መጋቢ ሚዲያ ሆነዋል።
ሚስት እቤት ባል ውጪ ሆነው በአንድ በመቶ ሜትሮች ርቀት በስልክ ከማውራት በቀር ሳይገናኙ መሽቶ ነግቷል። አንድ የስኳር በሽተኛ እናት ሃኪም ቤት መሄድ አቅቷቸው ተዘርረው ተገኝተዋል። ይህ እዚያው ከተማ መሃል የሆነውን እነ ኦ.ኤም. ኤን. የማያዩት እነ ቪኦኤና ቢቢሲም የዘነጉትን ማኅበራዊ ቀውስ ነው።
አዳማ ላይ የሆነውን የዘገበው የቪኦኤ ዘጋቢ ጃዋር “ሌባ፣ አሸባሪ፣ ዘረኛ” እየተባለ ሲወገዝ ሰምቶ ለምን የዘገባው አካል አላደረገውም? አዳማ ምን ተከስቶ ነበር? በዚያው ከተማ ጥቃት ቢደርስበትስ ምን ያስደንቃል? በዚህ አሳዛኝ ወቅት ሚዛናዊ መሆን እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ አነጋጋሪ ባይሆንም አብዛኞቹ የሚዲያ አውታሮች ሳያስቡትም ሆነ አስበውት የጃዋር አጀንዳ አራማጅ ሆነዋል። ሥራቸውን በትክክል የሚሰሩ የሉም ማለት ሳይሆን ሥራቸውን ጃዋር በሚፈልገው አግባብ፣ ቁመናና ልክ የሚሠሩት በርክተዋል ለማለት ነው።
“ተሸካሚነት” የሚዲያዎች በሽታ መሆኑ እየተሰማ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ትዝታ በላቸው የምትባለው የቪኦኤ ባልደረባ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ክ ኃላፊ የሆኑትን ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስን ስታናገር እሳቸውን የማይመለከት፣ እሳቸው ከሚመሩት የዕርቅ ጉዳይ ጋር የማይገናኝ የህገ-መንግሥትን መቀየር ጉዳይ አንስታ ስታናገራቸው ነበር። ጉዳዩ የማጅራት መቺ ፖለቲካ የሚያራምዱ “ህገ-መንግሥቱ ሊቀየር ነው። አሀዳዊ አገዛዝ ሊመለስ ነው” በሚል ህዝብ በስህተት ቅስቀሳ እየነዱ የሚያደርሱት ጥፋት ለትዝታ በላቸው ካልታያት እሷም “ተሸካሚ” ሆናለች ማለት ነው። የተሸከመችው ደግሞ የነውጥ አራማጅና ፈልፋይ የሆነውን ጃዋርንና ኮብላዮቹን አተራማሾች ከመሆን አያልፍም።
ልምድ ያላቸው የሚዲያ መሪዎች ወቅቱን በመቃኘት ሪፖርተሮች በጥንቃቄ እንዲዘግቡ፣ አሻሚና በተፈለገው ሁኔታ ሊሰነጣጠቅ የሚችል ጉዳይ እንዳይሸፍኑ፣ ህዝብን ማዕከል አገርን መርህ እንዲያደርጉ፣ እንዲሁም የቀጥታ ሪፖርቶች ሳይተላለፉ በመመርመር አደጋን ለመከላከል ሊሰሩ በተገባ ነበር።
ዛሬ የሚዲያ ሞኖፖሊ ይዞ መንግሥት የሆኑ አካላት የሚረጩትን ቅስቀሳ እውነቱን በማቅረብ ማጥራት ሲገባ በዕልህ፣ በቂም፣ በማን ከማን ያንሳል ፉከራ፣ ዜና በማጮህ ሳንቲም ከመልቀምና የመበልጸግ አባዜ ቅድሚያ አግኝቷል። በዚሁ ሳቢያ ሁሉም ወገን የሚተፋው መርዝ መከረኛው ህዝብ ላይ እየተረጨ የአገሪቱን ህዝብ ለመከራ ዳርጓል፤ እየዳረገም ነው። በወደ ቀልብ መመለስ ካልተቻለ ገና ይብሳል።
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ባለው መረጃ /ወደፊት በስፋት የሚሠራበት ይሆናል/ ትናንት ከባለሥልጣናት ጋር ተጣብቀው አገሪቱን ሲዘርፉ የነበሩ አጭበርባሪ “ባለህብት” እና አጫፋሪዎች ሆቴላቸው ውስጥ በክብር እንግድነት እንዲቀመጡ የተደረጉ ከዳያስፖራ የሄዱ የሚዲያ ባለቤቶች አሉ፤ በስማ በለውና በሹክሹክታ ወሬ ከፍተኛ የዩቲዩብ ተከታታይ ካላቸው መካከል አንዱን ከግብረአበሩ ጋር እየቀለቡ መርዝ ለማስረጨት እየሠሩ ነው። ሃብት ለመዝረፍ ያላቸውን ትርምስ በዚሁ የአሉባልታ ሚዲያ እየረጩ መንግሥትንና ዜጎችን ለማሳሳት እየሠሩ ነው።
ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጀምሮ በዝርፊያ፣ በወንጀል የተጨማለቁ ማፍያዎች ከግል ፍላጎታቸውና ከነበራቸው የሸፍጥ ታሪካቸው ለመሸሸግ እየሰሩት ያለውን ተግባር ወያኔንን በማስደብደብ ቢያስጀምሩትም ዓላማቸው ግን እነሱም ላይ ሹክሹክታው እንዳይነሳና ለውጡ ፊቱን እንዳያዞርባቸው ምሽግ ለማበጀት መሆኑን ጎልጉል እዚያው ምሽጉ ሥር ካሉ ምንጮች ለማረጋገጥ ችሏል። በጥቅሉ አብዛኛው የሚዲያ አውታሮች ምን ያህል እንደዘቀጡና ለመዝቀጥ የተመቸ ባህሪ እንዳላቸው ለማሳየት እንጂ ዝርዝር ጉዳዩን ለመተንተን አይደለም።
“ለማን ይነገራል? ማንስ ይሰማል? ማንስ ይናገራል? እንዴትስ ይነገር? ግራ የሚያጋባ ዘመነ አውሬነት። ግደሉ ብሎ ማቅራራት፣ ለመግደል ማቅራራት፣ የሰውን ልጅ ሲጨፈጭፉ ማቅራራት፣ የሰውን ልጅ ገድለው አስከሬን ሲጎትቱ ማቅራራት፣ ማሽካካት። ከበሮ መምታት። ቀሪ አለ የሚል ቀረርቶ ማስተጋባት። አገር በደም እንድትጣጠብ ያደረገ የመንደር ወንበዴ የሚዲያ ሽፋን የሚያገኝበት አገርና ሚዲያ!” ይላሉ ጎልጉል ያነጋገራቸው የደብረዘይት ነዋሪ አቶ በድሩ።
ጃዋር ቲቪ፣ ሬዲዮ፣ መጽሄት፣ ጋዜጣ፣ ማኅበራዊ አውታሮች፣ ስውር እጆች፣ መጠኑ የማይታወቅ ሃብት፣ በውል የማይታወቅ አጀንዳ፣ ተለዋዋጭ አቋሙን የሚያፈስባቸው ነፍስ ያላቸው ቁሶች እያሉት ሌሎች የሚዲያ ባለቤቶች እሱን በመረጃ አስደግፈውና ሚዛናቸውን ጠብቀው ከማጋለጥና በእሱ ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት አገርና ህዝብ እያወደሙ ያሉትን ኃይላት ይፋ ከማድረግ ይልቅ ለእሱ ኃይልና ብርታት ሲሆኑት እንደሚታይ አቶ በድሩ ቅሬታቸውን በሃዘን ይገልጻሉ።
ጃዋር ቤተክርስቲያን እንዲቃጠል የሚያዘው ለምንድ ነው? መስጊድ እንዲቃጠል የሚያደርገው ለምንድን ነው? ህዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያናክስ አጀንዳ የሚያራምደው ለምንድን ነው? ጃዋር አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ሃብቱን ወንድሙ ግብጽ አገር ከለላ አገኝቶ በነበረ ልጅ ወንድም ስም ያደርጋል፤ ለምንስ ዛሬ አምስት ሺህ የኦሮሞ ወጣቶችን ካስፈጀ በኋላ ከህወሓት ጋር ተወዳጀ? ለምንስ የህወሓት የዲጂታል ወያኔ ስምሪት ኃላፊዎች ጃዋርን አሁን በይፋ ደገፉት? ስለምንስ “ጊዜው አሁን ነው” አሉ? እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች እያሉ እንዴት ያልተከበበውን “ተከበበ” ለማለት ሚዲያው ተጣደፈ?
ጃዋር “ቄሮን የሥልጠና ማኑዋል አዘጋጅቼ የትግል ስልት ያሰለጠንኩት እኔ ነኝ” ሲል ባደባባይ ነግሮናል። ጃዋር “ቄሮ” እያለ የሚጠራውን ኃይል ከጃዋር ከሚወርድ መመሪያ ውጪ ምንም እንደማያከናውን አስረግጦ እስኪታክተን መንገር ብቻ ሳይሆን ይህንን ክሬዲት ማንም ሊወስድበት እንደማይችል በማህተም አትሞ አሳውቆናል። እናም አስከሬን እንዴት እንደሚጎተት፣ እንዴት በሜንጫ ሰው እንደሚቀላ፣ እንዴት ህጻናት እንደሚቃጠሉ፤ እንዴት አባትና ልጅ አንድ ላይ በድንጋይ ተወግረው ከሞቱ በኋላ እንዴት እንደሚጨፈጨፉና በአስፋልት ላይ እንደሚጎተቱ ማኑዋሉን ያዘጋጀው እሱ ነው። ሌላም ሌላም ማኑዋሎች አሉ።
ይህ ሁሉ ጉድ እያለ እንደ እነ ደጀኔ ጉተማ አክቲቪስት፣ ተንታኝ፣ ተመራማሪ፣ ምሁር፣ እያሉ የለቅሶ ደራሽና የአሸንዳነት ሚና መጫወት ዛሬ እጅግ እንደሚያሳዝን፣ ከሞቱት ሃዘን በላይ እንደሚያም ነው አቶ በድሩ በአስተያየታቸው መካከል የሚጠቅሱት።
“ጃዋር መሀመድ የህጻናት ደም፣ የእናቶች ዋይታ፣ የንጹሃን ነብስ ይፋረድህ፣ አንተ ክፉ፣ ቀልብህን የሳትክ ንክ፣ ደም አወራራጅ፣ ነብሰ በላ፣ የድሃ ጠላት … ” እያለች በናዝሬት ከቀብር በሁዋላ ትራገም የነበረች ሴት እንኳን እድሉን ባታገኝ ፍሬዎቻቸውን የተነጠቁ እናቶች ቁጥር ቀላል አይደለምና የሚዲያ አውታሮች ፊታችንን ወደ እነሱ እናዙር።
ጎልጉል ባለው መረጃ ጃዋር አሁን ችግር ተደራርቦበታል። በዚህም የተነሳ የሚቀልባቸውን ጋዜጠኞችና የሚከፈላቸውን አሸንዳዎቹን በማሰማራት የማስተባበያ ፕሮፓጋንዳ ለመጀመር እየተጣደፈ ነው። መንገድ በማዘጋቱና ሰዎች በማስጨፍጨፉ ጃዋር ኃይል ያገኘ የመሰላቸው ዜጎች፤ ከሚያስቡት በላይ ጃዋር ብርክ ውስጥ ነው፤ ተጨንቋል፤ ከውስጥም ከውጭም ተወጥሯል። እናም ድርድር ጠያቂ ሆኖ በውስጥ ይወተውታል። በፊትለፊት ወጥቶ “ከተፈለገ እንጨርሰው ማለት ነው” በሚል ህወሓት ያለመለትን የመፈንቅለ መንግስት ቅዠቱን ለማስፈራሪያ ያቀርባል።
ከዚህ በታች ያለው የአቶ ታዬ ደንደአ መልዕክት ብዙ ይጠቁማል፤
“የቸገረ ነገር !! በማይሆን ጊዜ አስጠሊታ ችግር ውስጥ ገባን፤ በጣም ያሳፍራል ፤ እሚናገሩትን ያሣጣል/ ይጠፋል፤ ብዙ ሰዎች ለምን ዝም አልክ ይሉኛል፤ እውነት አላቸው። በእንዲህ ያለ ወቅት ሃሣብ መስጠትን አንዱ ከአንዱ መጠበቅ ያለ ነገር ነው። ዳሩ ግን አንዳንዳንዴ የምትናገረው ነገር ቢኖርህም እንዴት እንደምትናገረው ታጣና ትቸገራለህ። ለሐገርና ለሕዝብ መስዋዕት የሆኑ ታጋዮችን ስታሞግስ አድገህ፤ እኔን “ጀግናውን” ለማዳን እናንተ ሙቱ! የሚል ስትሰማ እስቲ ምን ትናገራለህ? ይሁንና በመደመር መፅሃፍ መውጣትና በሰላም ኖቤል ሽልማት በተፈጠረ ቅናት አማካኝነት በተነሣ የአንድ አባት ልጆችን በጎሣና በሐይማኖት ተከፋፍለው ሲባሉ ስታይ አንጀትህ ያራል፤ ራስህን ትጠላለህ! በእንዲህ አይነት ጊዜ ነገር (መናገር) ትጠየፋለህ” ትርጉም በአለማየሁ አበበ።
ስለዚህ ወዳችሁም ይሁን “በጃዋር ፍቅር ተነድፋችሁ”፣ ተገዝታችሁም ይሁን የጥቅም ተካፋይ ሆናችሁ የጋዜጠኛነት ሙያችሁን በሚገባው ልክ ለመወጣት የቸገራችሁ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ የሚዲያ ባለቤቶች፣ ተቀጣሪዎች፣ ወዘተ አደብ ግዙ። ከጃዋር ጋር በመሆን አገር ለማፍረስ የምታደርጉትን ሁሉ የምንከታተል ስለሆነ እኛም አገራችንን ለመታደግ ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን። እናንተ ለጥፋት ስትቆሙ እኛ ለልማት ለመቆም ምንም አይከብደንም።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Leave a Reply