ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሳንጃ ከተማ በሁለት ባጃጆች ተጭኖ በድብቅ ወደ ጎንደር ከተማ ሊገባ የነበረ 76 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥና 19 ሺህ ጥይት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ሽጉጡና ጥይቱ በቁጥጥር ሥር የዋለው በላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ “ኢትዮጵያ ካርታ” በተባለው ቦታ መሆኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ሚዲያ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር እንየው ውብነህ ተናግረዋል።
ትናንት ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ በባጃጆች ተጭኖ ወደ ጎንደር ከተማ ለማስገባት ሲሞከር የፀጥታ ሃይሉ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል።
ሽጉጡና ጥይቱ በሰሌዳ ቁጥር 1-25591 እና 1-39321 አ.ማ በሆኑ ሁለት ባለ ሦስት እግር ባጃጆች አማካኝነት ተደብቆ በመጓጓዝ ላይ ሳለ እንደተገኘ ኮማንደሩ ገልጸዋል።
ኮማንደር እንየው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የአንደኛው ባጃጅ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በህግ እየታየ ይገኛል።
ከህገ ወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ የተጠናከረ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ያለውን ትብብር እንዲያጠናክርም ኮማንደሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply