የቀረቡ ጥያቄዎች በጥቅሉ፤
- ከኦነግ ሸኔ፣
- ከአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ፣
- ከሰሜኑ የሰላም ስምምነት፣
- ከዜጎች መፈናቀልና ግድያ፣
- ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ስለተከለከሉ ዜጎች፣
- አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሸጥ ከመቸገሩ ጋር በተያያዘ፣
- ወደ አዲስ አበባ ምርት እንዳይገባ ከመከልከሉ ጋር፣
- ከክልሎች የርስ በርስ መናበብ አለመቻል፣
- የሱዳን ወታደሮች ወረው የያዙትን የኢትዮጵያ መሬትና ያወደሟቸውን ንብረቶች የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች‼️
ሰላምና መረጋጋት
* የአገራችን የሰላምና መረጋጋት አሁን ያለው ከነበርንበት የተሻለ ነው፤ወደተሟላ ሰላም ለመሄድ በጣም በርካታ ስራ ይጠበቅብናል፤ * ተኩስ ሲቆም ግድያ ሲቆም ወዲያውኑ የሰላም አየር ይነፍሳል ማለት አይደለም፤ * ድህረ ግጭት የሚያሳድረው ቁስል ቶሎ የሚድን አይደለም፤
* የጦርነት ነጋሪን አብዝተው የሚጎስሙ ኃይሎች ያሉበት አገር ነው፤ እነዚህ ኃይሎች በርቀት ሆነው ጦርነትን የሚሰብኩ፤ ግጭት የሚፈበርኩ፤ አዛብተው ይዘግባሉ፤
* በዚህም ምክንያት የሰላም አየር ለማስፈን ፈተና ሆኗል፤ ሰላም አስፈላጊ ነው ብለን በጽኑ እናምናለን፤
* ሰላም እንደ ጦርነት ጀግንነት ይፈልጋል፤
* በጦርነት ጊዜ ሰዎችን በቀላሉ ማሰባሰብ ቀላል ነው፤ በሰላም ጊዜ ግን በአመክንዮ አሳምኖ ሰውን ማሳባሰብ ቀላል አይደለም፤
* እየተጓዘን ያለነው የተሟላ ሰላም ለማምጣት ነው፤ ሰላም አንጻራዊ ነው፤
ሚዲያ
* ሰው መርጦ መስማት አለበት፤ መርጦ ካልሰማ መርዝ ይወስዳል፤
* የሚዲያ ነጻነት ማለት የማባላት ጦርነት የመቀስቀስ ነጻነት ማለት ነው ወይ፤ አይደለም፤
* ነጻ ሚዲያ ማለት መንግስት ሳንሱር ከሚያደርግ ሳነሱሩን እኛ እንሸከማለን እኛ እናደርጋለን ማለት ነው፤
* የእኛ ሚዲያዎች ከነጻነት አጠቃቀም አንጻር በስፋት ራሳቸወን መፈተሽ አለባቸው፤
* ያልሞተ ሰው ይገድላሉ፤ ያጋጫሉ፤ ይሾማሉ፤ ይሽራሉ፤
* ግጭት መፍጠር ብቻ ሳይሀን ግጭት ያባዛሉ፤
* አሁን የሚታይ ግጭት ከሌለ ታሪክ መዘው ያጋጫሉ፤
* እነዚህ ሚዲያዎች ከአንገት ላይ ሀብል ቆርጠው ለመውሰድ የሚፈልጉ ናቸው፤
* እነዚህን ሚዲያዎች ባለማድመጥ ልንቀጣቸው እንችላለን፤
* መርጠን እንስማ ህግ እናስከብር፤ በጋራ ግፊት እናድርግ
የአዲስአበባ_ጸጥታ ጉዳይ
* በነፃ መዘዋወር መብት ነው ማንም ሰው ህጋዊ በሆነ መንገድ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ተዘዋውሮ * መስራት መብቱ ነው፣
* ይህ መብቱ እንዲከበር አብዝተን መስራት ይኖርብናል፣
* አዲስ አበባ ውስጥ በዚህ ሁለት ዓመት ያለው ፍልሰት ካላፉት አምስት ስድስት ዓመታት ይበልጣል፣
* በቅርቡ በተጠና ጥናት አዲስ አበባ አከባቢ በህገወጥ መንገድ በላስቲክ ቤት ሚኖሩ 96 በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደሉም፣
* አዲስ አበባን የብጥብጥ ማዕከል ማድረህ አለብን፤ ሁከት ካላስነሳን መንግስትን መነቅነቅ አንችልም የሚሉ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሀይሎች በተቀናጀ መንገድ በርካታ ሙከራዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል፣
* ይህን ለማስቀረት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ውጤትም አምጥተናል፤ ምንም መረጃ ሳይኖረን የሰራናቸው ስራዎች አይደሉም
* ይህ ስራ በስጋት በአፈፃፀም ውስንነት ድብልቆሽ ውስጥ ያለ ነው
* በአንድ ቀን በአንድ ቀበሌ በአንድ ሰው ፊርማ አንድ ሙሉ ባስ መያዝ ችለናል፣
* መሳሪያ ገንዘብ ፈንጅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንይዛለን
* አዲስ አበባ ከገቡ ብኋላ ደግሞ አንድ አከባቢ ለመሰብሰብ በሚያደርጉት ጥረትም እንይዛለን፣
* አዲስ አበባ ውስጥ ብጥብጥ ሲነሳ ከወለጋም ይምጣ ከጎጃም ብጥብጥ የሚያስነሳው ሰውዬ የአንዲት ምስኪን እናት ልጅ ወይ ይቆስላል ወይ ይሞታል
* እነዚህ ሀይሎች ሰኔ እና ሰኞ የገጠመ የሚመስላቸው ህዝብ በዓላት በሚከበርበት ጊዜ አበል እየከፈሉ ሰው ያስገባሉ፣
* ይህን ማስቀረት ብዙ ጥረት ሲደረግ ቆጥቷል ወደ ፊትም ይቀጥላል
* የአዲስ አበባን ሰላም ለማስጠበቅ አዲስ አበባ ውስጥ ሁከት መፍጠር እንዳይችሉ የተጠናከረ ስራ ይሰራል፣
የዓመቱ ቀልድ – ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው የምትሰሩት
* ሙስና ላይ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ልማታችንን ለማፋጠን እንቅፋት ነው፤
* በውስጣችን የተንሰራፋ ስለሆነ፤ በቀላሉ የምንፈታው ጉዳይ አይደለም፤
* ትምህርትን የማስፋፋት ስራዎች እየሰራን ነው የጥራት ጉዳይ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፤
* የክልልነት ጥያቄ ህዝብን ልማት እናመጣልሃለን በሚል በመቀሰቀስ ይፈጠራል፤ ይሄ መስተካከል አለበት፤
* መልሶ ግንበታ ስራዎች በየአካባቢው ተጀምሯል፤ አቅምን ባገናዘበ መልኩ መሆን አለበት፤
* ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ መንግስት የከፈለውን ዋጋ ዓለም የሚያውቀው ነው፤
* ይሄንን መንግስት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው የሚሰራው ማለት የአመቱ ቀልድ ነው፤
* ኢትዮጵያን ለማፍረስ ነው የምትሰሩት ከተባለ አሁን ማን አሰቆመን ታዲያ፤ ይሄ ትክክል አይደለም፤
* ፖሊስንና መከላከያን የገነባንበት መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የማያውቅ ብዙ አገራት የሚቀኑበት አድረገን የገነባነው ኢትዮጵያን ለማጽናት ነው፤
* የኢትዮጵያ የመፍረስ ስጋት አልፏል፤ እንዲህ አይነት ስጋት አለን፤ የተሻለ ኃይል ገንበተናል፤
* እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ ከውጭ የሚመጣ ሃይልም አይችልም፤
* ነገር ግን ኢትዮጵያ ፈርሳለች የሚል ካለ በጭንቅላቱ ውስጥ ፈርሳለች፤ ይሄንን ምንም ማድረገ አይቻልም፤
* ለስብሰበ የመጡ የውጭ አገር ሰዎች የሚያነሱልኝ እንዴት ኢትዮጵያ በጦርነት በኮሮኖ ውስጥ እንዲህ ልታድግ ቻለች የሚል ነው፤
* አሁን ያለውን መንግስት መቀየር የሚቻለው ሻል ያለ ሃሳብ ያለው ሲመጣ ነው፤
* ዴሞክራሲን ለመገንባት የምናደርገወን መንገድ ተባብረን በቅንነት ካልገዛን የሚመጣው አምባገነናዊነት ነው፤ ይሄ ደግሞ አይተነዋል አይጠቅመንም፤
ሥልጣን ስለመልቀቅ
* ስልጣን ልቀቅ የሚለው ጥያቄ ጥሩ የሚሆነው በጋራ እንልቀቅ ቢባል ነበር፤
* ስልጣንን በሚመለከት በእኔ እና በሌላ ሚኒስትር መካከል የሚደረግ ድርድር የለም፤ ስልጣን የህዝብ ነው፤
* ማድረግ ያለብን የተሻለ ሃሳበ ይዘን ስልጣን ሰጪው ጋር እንቀርባለን እንጂ ምክር ቤት ላይ አይሆንም፤
* ስልጣን በኮሮጆ እንጂ በመናጆ አይሆንም፤
* በዓለም ላይ ፈተና አልቦ ችግር አልቦ አገር የለም፤ የችግራችን ባህሪ ግን ይለያያል፤
የሱዳን ጉዳይ
* ከሱዳን መንግስት ጋር ያለው ችግር ከንጉሱ ዘመን ጀመሮ የነበረ ነው፤
* ከሱዳን መንግስት ጋር ተነጋግረን ያለወን የድንበር ችግር ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁመናል፤
* የጋራ ስምምነት ያለበት የድንበር ማካለል እስኪኖር ሁለቱም ህዝበ እንዳይጉላላ በሚል ተወያይተናል፤
* ደቡብ ሱዳንን በተመለከተ ያጋጠመን 20 ሺህ ከብት እየነዱ ድርቅ አጋጥሞናል ብለው የመጡ አርብቶ አደሮች አሉ፤ ከዚህ ውጭ ለድንበር የሚያሰጋ አይደለም፤
* ላለፉት አራት አመታት ወለጋ አካባቢ ልማት እንዳይሰራ ሰው አንዲጎዳ ያደረገ ግጨት አለ፤
* መንግስት ይሄ ግጨት እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎት አለው፤ በፓርቲያችንም የሰላም ድርድር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፤
ኦነግ ሸኔ
* ሸኔን በሚመለከት ባለፉት ወራት 10 አካበቢ ሙከራ ተደርጓል፤ ችግር የሆነው አንደ የተሰባሰበ ሃይል አለመኖሩ ነው፤
* ሰላሙን የሚጠላ ሰው አለ ብዬ አላምንም፤ ጉዳዩ በሰላም አንዲፈታ አጠንክረን እንሰራለን፤
* መንግስት ከሁሉም የታጠቁ ሃይሎች ጋር ያለውን ችግር መፍታት የሚፈልገው በሰላም በመነጋገር ነው፤
* የዓለም ሁኔታ በፍጥነት እየተቀያየረ ነው፤ በዓለም ላይ እየተፈጠረ ያለው እንቅሰቃሴ እንደኛ ያለን አገር ይጎዳል፤ ስለሆነም ሰብሰብ ብለን ልንቋቋም ይገባናል፤
* እኛ የምንፈልገው ከኢትዮጵያ ያለፈ ትውልድ እንዲፈጠር ነው፤
* ኢትዮጵያ የምትገነጠልበት ጊዜ አልፏል የሚፈልግም ያለ አይመስለኝም፤ ይሄ ዘፈን አልፎበታል፤ እንተወው፤
የኦሮሞና የአማራ ጽንፈኞች
* ኢትዮጵያ የእገሌ የእገሌ አገር አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን አገር ነች፣
* ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት አለው፣
* በኦሮሞና በአማራ ውስጥ ያሉ ጽንፈኞች ሁልጊዜ እነሱ ብቻ የአገር ባለቤት የሆኑ ይመስላቸዋል፣
* በዚህ የተነሳ የማይገባቸውን ድርሻ ይናፍቃሉ፤ ይሄ አደገኛ ነገር ነው፣ የጋራ አገር እንገንባ፣
* ለዳሰነችም ለሌሎችም ሕዝቦች አገር የሆነ ኢትዮጵያ ብሎ የሚያምንባት አገር ከገነባን ኢትዮጵያ በቂ ናት፣
* ያለው አላስፈላጊ ሽሚያ ግን ጥፋት ያመጣል፣
* ብዝሃነትን በማቀፍ ችግሮችን በመፍታት መግለጽ ሲገባቸው በተቃራኒው የሚሄዱ ግለሰቦችና ቡድኖች መታረም አለባቸው፣
* በሁሉም አካባቢ ያሉ ሕዝቦች በሕገመንግስቱ መሰረት በልካቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የተጀመረ ስራ አለ፣
* ነገር ግን አሁን በየቦታው አልፎ አልፎ የሚታዩ ችግሮችና እንዲቀንሱና እንዲጠፉ መንግስት አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል የእናንተም ድጋፍ ቢታከልበት መልካም ይሆናል፣
ኢኮኖሚ
* የዓለም ኢኮኖሚ ላለፉት 100 አመታት አራት ጊዜ ፈተናዎች ገጥመውታል፤ አሁን ያለው አምሰተኛው ፈተና ነው፤
* አሁን እያጋጠመን ያለው ፈተና እአአ በ2008 ካጋጠመው ጋር ተመሳሳይነት አለው፤ ሰራተኛ ቅነሳ እየሰፋ መጥቷል፤
* በዓለም ላይ ያሉ ዋና ዋና ትላልቅ ባንኮች እየተጎዱ ነው፤ እነሱ ሲጎዱ እኛንም በጣም ነው የሚጎዱን፤
* የዋጋ ግሽበት በጣም የጨመረባቸው እንደ አርጀንቲና 100 በመቶ ያሉ አገራት አሉ፤
* የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ኮሮና በአገራት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንደፈጠረ አይኤም ኤፍ ሪፖርት አውጥቷል፤
* በዚህ ችግር ምክንያት 110 አገራት ችግር ውስጥ ናቸው፤
* የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ በዚህ ችግር ምክንያት ወደ ኢኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እያስገቡ ነው፤
* ይሄ ሁኔታ እኛን በከፍተኛ መጠነ ይፈትነናል፤ መዘጋጀት አለብን፤
* የዓለም ኢኮኖሚ እአአ በ2021 ስድስት ነጥብ አንድ በመቶ ነበር ያደገው በ2022 ሶስት ነጥብ 4 ሲሆን ዘንድሮ ግን ሁለት ነጥብ 9 በመቶ ብቻ ነው ያድጋል የተባለው፤
* እአአ በ2022 በሁለት ነጠብ 7 በመቶ ያደጉ ዘንድሮ አንደ ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ያድጋሉ ተብሏል፤
* የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸወን ዜጎች እንደሚጎዳ እንገነዘባለን፤
* ላለፉት 20 አመታት በኢትዮያ ውስጥ ያልተቋረጠ ግሽበት ነበር፤ ይሄንን ልንገታ አልቻልንም፤
አንድ ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍለናል፤
* በአምራችና ሸማች መካከል ያለውን ልዩነት መፍታት አልቻልንም፤
* ድሮ የነበረው ርዳታ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል፤ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም፤
* እንደ መፍትሄ የወሰድነው አቅርቦት እናሳድግ የሚል ነው፤
* አዲስ አበባ ላይ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ የሚመገቡበትን ማዕከል በአዲስ አበባ እየከፈትን ነው፤
* ከምግብ ማጋራት በተጨማሪ ከፍተኛ ድጎማ እያደረግን ነው፤
* ለነዳጅ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ፣ለማዳበሪያ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድረገናል፤
* በፍራንኮ ቫሉታ መንግስት 10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እየቻለ ትቷል፤
* ኢትዮያ ውስጥ ምርት እጥረት እያለ አይደለም የዋጋ ንረት የተፈጠረው፤
* አርሶ አደሩ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል በቤቱ ውስጠ ምርት ይዟል፤
* ከ50 አመት ወዲህ በታሪካችን ለስንዴ ዶላር ያላወጣነው ዘንድሮ ብቻ ነው፤
* በዘንድሮ ሰባት ወራት 210 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስበናል፤ ይሄ ካለፈው አመት አንጻር 28 በመቶ እድገት አለው፤
* የሰባት ወራት ወጪያችን 376 ቢሊዮን ብር ነው፤ ከገቢያችን የበለጠ ነው፤
* በሰባት ወራት የወጪ ንግዳችን በተለይም በማዕድን ዘርፍ በኮንትሮባንድ ምክንያት ቀንሷል፤
* በአገልግሎት ዘርፍ በሰባት ወራት በ25 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፤
* የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባለፉት ስምንት ወራት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ውስጥ ገብቷል፤
* ከገቢ ምርት አንጻር 9 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር አውጥተናል፤ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛው ገንዘብ የወጣው ለነዳጅ ነው፤
የመንገድ ሥራ እና ካሣ አከፋፈል
* የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ አንድ ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል
* በመንገድ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 320 ፕሮጀክቶች አሉ፤
* እነዚህን ፕሮጀክቶች ለመጨረስ አንድ ትሪሊዮን ብር ያስፈልጋል።
* እነዚህ መንገዶች ሲያልቁ በአስፓልት እስካሁን ኢትዮጵያ ከሰራችው መንገድ ይልቅ በአምስት አመት ውስጥ የተጀመሩት ይበልጣሉ፤
* ስራውም በጣም ስፊ ስለሆነ ተጨማሪ ጥያቄ እያመጣ ነው
* በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አንድም መንገድ የማይቆፈር ዞን የለም
* መንግስት መንገድ ላይ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሆነ የሚያመለክት ነው
* ይህ ስራም እንደየከባቢው ሁኔታ የሚፈጥንና የሚዘገይበት ሁኔታ አለ
* በባህር ዳር የተጀመረው ድልድይ በዋጋም ይሁን በዲዛይን ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከተሰሩ ድልድዮች የተለየ ነው ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ነው
* በርካታ መንገዶች አጀማማራቸውና ሂደታቸው ጥሩ ሊባል ሚችል እንደ እንሆነ ውስጡ ግን ውስንነቶች አለ
* ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ትልቅ ፈተና እየሆነ ያለው የካሳ ጉዳይ ነው
* ዘንድሮ ብቻ ለካሳ 20 ቢሊዮን ብር መንግሥት ከፍሏል
* ከዚህ በኋላ ክልሎች ለፌዴራል ፕሮጀክቶች ከካሳ ውጪ ቦታ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፤
የፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸም
* ባለፉት ስድስት ወራት የፋይናንሱ ዘርፍ ጥሩ አፈጻጸም አስመዝግቧል
* የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያጋጥመው በመሰረታዊነት በሶስት ጉዳዮች ምክንያት ናቸው
* የመጀመሪያው ከፍተኛ ባለእዳ መሆን፣ እንደ አገር ለመክፈል የሚያዳግት እዳ ሲኖር፣
* ሁለተኛው የአሴት ዋጋ መውረድና ሶስተኛው የገቢ መቀነስ ናቸው
* በተጨማሪነት የዋጋ ግሽበት ሲታከልበት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን የሚችል መናጋትን ሊፈጥር ይችላል
* በኢትዮጵያ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ምርት ባለመኖሩና ወደውጭ በመላኩ ምክንያት አይደለም
የምርት እጥረት የለም
* በየአርሶ አደሩ ቤት ከፍተኛ የምርት ክምችት አለ
* ነገ ከነገ ወዲያ ዋጋ ይጨምራል በሚል የተከዘነና የተያዘ ነው
* በየመንገዱ የተፈጠሩት ኬላዎችም አርቲፊሻል ችግሮች ሆነዋል፡
* አሁን ስንዴን የያዙ ሰዎች በዘንድሮው በጋ ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት የሚሰበሰብ መሆኑን ካለመረዳት ያደረጉት ስግብግብነት ነው
* በዚህ ሁለትና ሶስት ወራት በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ገታ ያለ እንጂ እንደሚባለው አይደለም፡፡
* የጤፍ ዋጋ ጨምሯል፤የስንዴ ዋጋ ጨምሯል፤ የአንዳንድ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል፡፡
* ቢሆንም በዚህ ዙሪያ እየተወሰዱ ያሉት የማስተካከያ ርምጃዎች ተጠናክረው እየቀጠሉ በመሆናቸው የሚረጋጋና ወደነበረበት የሚመለስ ይሆናል
* ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው የዋጋ ንረት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነ ገልጸው * ይህ የሆነበት ምክንያት ባለፉት ሃያ አመታት በተከታታይ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እያደገ በመሆኑ
* በአምራችና በሸማች መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ባለመቻሉ ከሌሎች የአለም አገራት ጋር ባለ ግንኙነት ግሽበትም የምንሸምት መሆኑ ከጦርነት ጋር ተደማምሮ የፈጠረው ጫና ነው
የመንግስት ወጭና ገቢን በተመለከተ
* የተጣራ ታክስ 210 ቢሊዮን ብር ገቢ እስከአሁን ተገኝቷል
* ይሄ በአሃዝ ደረጃ በ28 በመቶ አድጓል
* ነገር ግን በታክስ ጂዲፒ ሬሾ ስሌት ካየነው በጣም ዝቅተኛ ነው
* የምንሰበስበው በቂ ባለመሆኑ ብዙ ስራ ይጠይቃል
* ወጭው በሰባት ወራት 376 ቢሊዮን ብር ነው
* ከገቢያችን ብዙ ይበልጣል
* ወጪ ብቻውን 31 በመቶ አድጓል ይሄን ያመጣው ሰው ሰራሹ እና የተፈጥሮ አደጋው ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጣ በመሆኑ በብድር የሚሞላ ካልሆነ በስተቀር እንደመንግስት ያስቸግራል
* በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ ዘርፈብዙ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን ፋይናንስ ዘርፍ በማጠናከር የአገሪቱን ኢኮኖሚና ለውጥ ወደላቀደረጃ ያሻግራሉ ተብሎ ይታመናል (ከተለያዩ የሚዲያ አካላት የተጠናቀረ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
እውቁ ኢትዮጵያዊ አቶ አበራ ጀምበሬ “የእስር ቤቱ አበሳ” በተሰኘው መጽሃፋቸው መግቢያ ላይ በግጥም ይህን አስቀምጠዋል።
በእኛስ በሃገራችን ልማድ ሆነ ደገል ( ደገል ማለት – ቂም፣ ቂም በቀል፣ መበቀል)
መንግስት ተገልብጦ ስልጣን ሲደለደል
ሥርዓተ ህግ ሆነ ሰው ማሰር ሰው መግደል።
የሃገራችን ችግር ብዙ ነው። አሁን ዘምኛለሁ የሚለው የመገናኛ አውታርም በሶሻል ሚዲያና በሌሎችም ድህረ ገጾች ሽርፍራፊ ሳንቲም ለማግኘት የሆነውን አጋኖ፤ ያልሆነውን ፈጥሮ ማቅረብ ሙያ ሆኖ ተገኝቷል። በዚህ አንጻር ካሜራ ፊት ሆነው የሚናገሩትና በግል የሚያወሩት ጭራሽ የማይገናኝ ሰዎች ዛሬም ልክ እንደ ሴተኛ አዳሪ ለመኖር ብቻ ወሬ በማናፈስ ሃገር ያተራምሳሉ። ጊዜው ሸፍቷል። ሰው ግን በአርቲፊሻል ዓለም እንደሚኖር ዘንግቷልም። አይኑ በቁሳዊ ፍቅር ታውሯል። 1 ሚሊዪን የቲክቶክ ተከታይ አለኝ ይላል/ትላለች። የሰው ልጅ ያልገባው ግን ሞኝና ወረቀት የያዘውን እንደማይለቅ ነው። ሞኙ ሰው ወረቀቱ ኮምፒውተር ነው። ዛሬ በዚህም በዚያም ሰውነታችንም ሆነ ሌላውን ነገር ለጣጥፈን ሽራፊ ሳንቲም መልቀሙ መልሶ የሚጎዳ እንጂ ጠቀሜታ የለውም። ይህ ግን በጊዜአዊ ዝናና በንዋይ ፍቅር አይኑ ለታወረ ዛሬን እንጂ ነገን ለማየት አይቻለውም። ጮቤ ረገጣው ይቀጥላል።
በመሰረቱ የጠ/ሚሩ ምላሽ ሸፍጥ ያለበት ነው። ያው በሰላ አንደበት ይህንም ያንም በማለት የሰውን ሃሳብ መሳብ ችለው ይሆናል እንጂ መሰረታዊ ጥያቄዎቹን በቀጥታ አልመለሱም። ሲጀመር የጠ/ሚሩ ከስልጣን መውረድ የሚያመጣው አንድም ፋይዳ አይኖርም። እንዲህ አይነቱ ጥያቄ ለሚዲያ ፍጆታ ተብሎ የሚቀርብ እንጂ እውነትነት የለውም። ልክም ነው “አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግስት ይውረድ ማለት” ጅል የሚያደርገው። ግን መንግስት ራሱን በራሱ እየበደለ እንደሆነ በመሬት ላይ ያለው እውነት ያሳያል። ያለፈው በደም የተለወሰ ታሪካችን እንደሚያመላክተው የዛሬውም ከትላንቱ ሳይማርና ሃገራዊና ዓለም አቀፋዊ የፓለቲካ እይታዎችንና አሰላለፎችን በሰከነ መንገድ ሳይመለከት በክልልና በቋንቋ ፓለቲካ ተሳክሮ እርስ በእርሱ ይላተማል። ስንዝር ሲሰጡት ክንድ ከሚጠይቅ የፓለቲካ ቡድን ጋር ሰላም ማምጣት በጣም አስቸጋሪ ነው። የተጣረሰው የዘር ፓለቲካ ያው እንዳለፈው ታሪካችን በየሰበቡ ሰውን ማሰር፤ መደብደብ፤ ማፈን፤ ማስፈራራት አልፎ ተርፎም መግደሉ ምን ያህል የጊዜው አለቆቻችን ካለፈው ውድቀት እንዳልተማሩ ያመላክታል። አውቃለሁ፡፤ የኢትዮጵያን ህዝብን ማስተዳደር እጅግ ውስብስብና ከባድ ነው። የሰው ቁጥር የትየሌሌ ከመድረሱ ጋር ብዙው የከተማ ኗሪ ለመሆን ትላልቅ ከተማዎችን ማጥለቅለቁ በቻይናና በሌሎችም ሃገሮች የታየ ነገር ነው። መሬት ላራሹ በማለት ህይወታቸውን የሰውት እነዚያ ቀደምት ታጋዪች ዛሬ መሬት ገበሬውን በማፈናቀል ለባለ ሃብት ሲቸበቸብ በህይወት ያሉ ይህን ሲያዪ ምን ይሉ ይሆን?
ሌላው እውቅ ኢትዮጵያዊ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊስ – Red Tears እና ክህደት በደም መሬት በሚለው መጻፍቶቹ ያስነበበን ካለፈው የማንማርና ጨካኞች እንደሆን ነው። ጥያቄው ሃገሪቱ ከአንድ ጨካኝ አመራር ወደ ሌላው ሁሌ የምትሸጋገረው ለምንድን ነው? የአሁኑስ ካለፈው የተሻለው ምኑ ላይ ነው? ሰውስ በሰውነቱ መለካቱ ቀርቶ በቋንቋውና በዘሩ አልፎ ተርፎም በክልሉ መሆኑ እንስሳዊ ባህሪ አይደለምን? ያበደ ሰው ራቁቱን መሆኑ ለራሱ አይታየውም። የእኛ ሃገር ፓለቲካ ያኔም ዛሬም ወልጋዳ ነው። የወያኔውንና የብልጽግናውን ጊዜ ከሌሎቹ የተለየ የሚያደርገው ሰው በዘርና በቋንቋው እየተመረጠ የሚገደልበት ጊዜ መሆኑ ነው። ችግር በንጉሱም ጊዜ ነበር፤ ደርግም አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር እያለ እንዳላፋከረ ሃገሪቱን ለወያኔና ለሻቢያ አስረክቦ እግሬ አውጭኝ ነው ያለው። እልፎች ግን በአመኑበት በጠላት እጅ አንወድቅም በማለት በየምሽጋቸው ራሳቸውን አጥፍተዋል። ሌሎችም በዚህ በዚያም ተበትነዋል፤ በወያኔ እስርቤት አሳር ቆጥረዋል፤ ሞተዋል። ያለፈውን የኢትዪጵያ ሰራዊት መፈራረስ ሳስብ አንድ ያነበብኩት መጽሃፍ ወደ ሃሳቤ ይመጣል። Secondhand Time: The Last of the Soviets by Svetlana Alexievich. ከዘመን ዘመን አንድ የሰራውን ሌላው በንቀት እየደረመሰ ሃገር ይሰራል ማለት አይቻልም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመኖች ሲሸነፉ አሜሪካና ራሺያ ያደረጉት እውቀት ያላቸውን ሳንቲስቶች እየለቀሙ ወደ ሃገራቸው ወስደው በምህረት ማሰራት ነው። እኛ ያወቀ ሰው ካገኘን አንገት መቁረጥ ሙያ አርገን ይዘነዋል። ግን ይህ መቼ ነው የሚያበቃው? ባጭሩ የፓርላማው ውሎ የቃላት ድርደራ የበዛበት፤ በመሬት ላይ ላሉ ጭብጥ ችግሮች ቀጥተኛ ምላሽ ያልተገኘበት፤ በለበጣ ሳቅና ማሾፍ የተከናወነ ቆይቶ አሿፊና ሳቂውንም የሚያስለቅስ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት አያዳግትም። ይህ እኔ ብቻ ልክ ነኝ ከሚለው ግትር የሃበሻ ባህሪ እስካልተላቀቅን ድረስ ስንገልና ስንሞት ስንገዳደል እንኖራለን። በቃኝ!