በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ጥይት ተኩሶ በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ ወንጀሉን መፈፀሙን አመነ። አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ ጥይት ተኩሶ በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው አቶ ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል አረጋገጠ።
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደሉን ተከትሎ በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩት ጥላሁን ያሚ እና አብዲ አለማየሁ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው የተጨማሪ ስምንት ቀን ጊዜ የሰራውን የምርመራ ሥራ የገለጸ ቢሆንም በዋናነት ከተጠርጣሪዎች ጋር በግድያ ዙሪያ የተጠረጠሩት ላይም ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።
የስልክ ግንኙነትን በተመለከተም ቃል የመቀበል ስራ መሥራቱንም አስታውቋል።
የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ማስረጃ ማሰባሰብ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የተላከ የስልክ መልዕክት ሰፊ መሆኑን ተከትሎ የትንተና ሥራ እየሠራ መሆኑንም አመልክቷል።
ከተጠርጣሪዎች እጅ የተገኙ ስልኮችን ለብሄራዊ መረጃ ደህንነት በመላክ ሌሎች የምርመራ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ተናግሯል መርማሪ ፖሊስ።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ከዚህ በፊት ከሰራችሁት ስራ ውጭ ምን የተለየ ውጤት ተገኘ ሲል ላቀረበው ጥያቄ መርማሪ ፖሊስ ከተጠርጣሪዎች በስተጀርባ ሌሎች ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚያመላክት መረጃ መገኘቱን ጠቅሷል። እንዲሁም ከወንጀሉ በስተጀርባ የተቀነባበረ ወንጀልን ለመለየት ስራ ላይ መሆኑን የተናገረው መርማሪ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪው “ይህንን ተልእኮ የሰጡኝ ሰዎች ድርጊቱን መፈፀምህን በሚስጥር የማትይዝ ከሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ጉዳት እናደርሳለን” በማለት እንዳስጠነቀቁት ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የአራዳ ምድብ፣ አንደኛ ወንጀል ችሎት ተናግሯል።
በዚህም “ለቤተሰቦቼ በቂ ጥበቃ እንዲደረግላቸው እና የኔም ጉዳይ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
“የፀሀይ ብርሀን አግኝቼ አላውቅም፣ ካቴና ከእጄ አላወለቀም፣ ክስ እስከሚመሰረትብኝ እንኳን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር እንድቀላቀል ይደረግልኝ” በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል።
ተጠርጣሪው ባለፈው የጊዜ ቀጠሮ በዚሁ ችሎት ቀርቦ “እራሴን እንዳጠፋ ይፈቀድልኝ” ማለቱን ችሎቱ አስታውሷል። በዚያው ቀጠሮው መርማሪ ፖሊስ ካቴናው ከእጁ የማይወልቀው ተጠርጣሪው እራሱን እንዳያጠፋ ለመከላከል መሆኑንም ችሎቱ ገልጿል።
መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮው ተጠርጣሪው የካቴናውን ጉዳይ ዳግም በማንሳቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚመለከተው የስራ ሀላፊ በቀጣይ ቀጠሮው ስለሁኔታው ያስረዳ ብሏል ችሎቱ።
ፖሊስ ባለፈው የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ያከናወነውን የምርመራ ስራ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በቀጣይ በተለይም በቁጥጥር ስር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጀርባ ድርጊቱን ያቀነባበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማደራጀት ከጠየቀው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 11 ቀን ፈቅዷል።
በግብረአበርነት የተጠረጠረው አብዲ አለማየሁ የተባለው ግለሰብም በዛሬው ችሎት ከጥላሁን ያሚ ጋር ፍርድ ቤት ቀርቦ ነበር።
ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። (ምንጭ፤ ኢብኮ እና ፋና (ፎቶ፤ ከኢንተርኔት የተገኘና ለማሳየነት የቀረበ))
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply