መከላከያ ሰራዊታችን በውጊያ ወቅት ሀገርና ህዝብ የሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነትና በድል ለመወጣት ሀሩር እና ብርዱ ሳይበግረው በየተራራው በየጥሻው ድንጋይ ተንተርሶ ሙቀቱን በላቡ ዝናቡን በሰውነቱ ሙቀት እየተቋቋመ ግዳጁን በድል ይወጣል።
አንፃራዊ ሰላም ባለበት ደግሞ በደረሰበት ቦታ ሁሉ ህዝባዊ ሰራዊትነቱን በተግባር ያሳያል። ካለው የዕለት ጉርሱ ቀንሶ ለተቸገሩ ወገኖች ያካፍላል። በጉልበቱም በገንዘቡም ይረዳል።
በምዕራብ ዕዝ በሚገኝ ክ/ጦር ሁለተኛ አባይ ሬጅመንት የሆነው እንዲህ ነው።
ህፃን አማኑኤል ሽፈራው ይባላል። የ11አመት ታዳጊ ሲሆን ተወልዶ ያደገው በሰሜን ጎንደር አድዓርቃይ ወረዳ አምበራ አካባቢ ልዩ ስሙ አዲስ አለም በሚባል ሰፈር ነው ።
ህፃን አማኑኤል እንደሚለው እናቴ ትግራይ ለስራ እንደሄደች አልተመለሰችም። አባቴን አላውቀውም። ከአጎቴ ጋር ነበር የምኖረው። በጦርነቱ ምክንያት ከምንኖርበት መንደር ተፈናቅለን ወጣን። በመሃል ስመለስ አጎቴን ላገኘው አልቻልኩም።
የያኔውን ማረፊያ ማጣቱን ሲናገር ፊቱ ላይ የሚታየው ፍርሃት አሁን ላይ የተከሰተ አንዳች አስደንጋጭ ነገር ያለ እስኪመስል ድረስ በጉልህ ይነበባል።
አማራጮች ሁሉ የጠፋበት ህፃን አማኑኤል ከጎረቤት ተጠግቶ በርካታ ቀናትን አሳለፈ። አንድ ቀን ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር እየተጫወትኩ አንድ የወታደር ልብስ የለበሰ ሰው በመሐላችን ተቀላቀለ ይላል ትንሹ ልጅ።
ወታደሩ የሁላችንንም ስም ጠየቀን … የማነህ ልጅ? ….ማነው ስምህ ? እያለ ይጠይቅ ነበር። ጥያቄው እኔ ላይ ሲደርስ ጓደኞቼ እሱኮ ቤተሰብ የለውም አሉት።
ወታደሩ ጓደኞቼ በነገሩት ነገር እንዳዘነና ግን ደግሞ አንተ ጎበዝ ልጅ ነህ። አይዞህ እያለ ፀጉሬን እያሻሸ አፅናናኝ። አብረውኝ የሚሰሩትን ወታደሮች ላማክርና እኛጋ እንድትሆን ጥረት አደርጋለሁ አለኝ።
ወታደሩ ሻ/ባሻ መታደል አለም እንደሚባል እና የሁለተኛ አባይ ሬጅመንት አባል እንደሆነ ነገረኝ።
ሻ/ባሻ መታደል ሬጅመንቷ በተሰበሰበችበት ስለልጁ ሁኔታ ለአባላቱ አስረዳቸው አባላቱም በጣም አዝነው በአንድ ድምፅ እኛ የበላነውን እየበላ ከኛ ጋር እያደረ እንደ ልጃችን እናሳድገዋለን በማለት ተስማሙ።
አማኑኤልንም ወደ ካምፓቸው አስገብተው ልብስ አልብሰው መኝታውን አዘጋጅተው አብሯቸው እንዲኖር አደረጉ ።
አሁን ላይ አማኑኤል ከሰራዊቱ ጋር ይጫወታል፣ ይዝናናል ልክ እንደቤተሰቦቹ ሆኗል።
ሻ/ል ባሻ መታደል እንዳለው ለልጁ የራሱን ገንዘብ እንዲያጠራቅም የሊስትሮ መስሪያ ማቴርያል እንዲገዛለት አድርገናል። በየጊዜው ሰራዊቱ የሚያወጣለትን ገንዘብ እንዲያጠራቅምም አካውንት በስሙ ከፍተንለታል።
እኔም እሱን አግኝቼ ሰራዊቱ ተስማምቶ ወደ ካምፕ ገብቶ ከኛጋ ስለኖረና ደስተኛ ስለሆነ በጣም ደስ ብሎኛል ይለናል።
የሬጅመንቷ አዛዥም መቶ አለቃ ሳፋየ ካራፎ ይህን ታዳጊ ለማሳደግ ሬጅመንቷ ሙሉ ፈቃደኛ ስለሆነች እና የአባላቱ ህዝባዊነትን በተደጋጋሚ ስለማይ ደስታዬ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
ታዳጊው ህፃን አማኑኤል ሽፈራውም እጅግ በጣም ደስተኛ እንደሆነና “እኔም አድጌ እንደእናተ ወታደር ሆኜ ሀገሬን በውትድርና ሙያ ለማገልገል ህልም አለኝ” ሲል ተናግሯል። (ዘገባና ፎቶ: ፍርዱ ሀብቴ – የመከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply