ላለፉት ሰባት ዓመታት የጋምቤላ ሕዝብ አንድነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ጋሕአዴን) ሊቀመንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ጋትሉዋክ ቱት ከፓርቲው ሊቀመንበርነታቸው “በፈቃዳቸው” ለቅቀዋል። ከእርሳቸው ጋር አብረው ምክትላቸው ሰናይ አክዎርም ከፓርቲው ምክትል ኃላፊነታቸው እንደዚሁ በፈቃዳቸው ለቅቀዋል። በምትካቸው የክልሉ የሥነምግባርና ጸረ-ሙስና ኃላፊ ዑመድ ዑጁሉ ሊቀመንበር፤ የጋትሉዋክ ሚስት ወንድም የሆኑትና የክልሉ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ታንኩዌይ ጆክ ሮምን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። የክልሉ ነዋሪዎች ምርጫውን “የቀድሞ ደጃዝማቾች ካባቸውን አውልቀው ለሚፈልጉት በመስጠት እንደሚሾሙት ጋትሉዋክም ለዘመዱ የስልጣኑን ካባ ያጎናጸፈበት ቀልድ ነው” ሲሉ አውግዘውታል፤ ይልቁኑም ጋትሉዋክ ቱት በበርካታ ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ስለሆነ ሌሎቹንም አመራሮች ጨምሮ ሁሉም “ለፍርድ መቅረብ አለባቸው” ብለዋል።
ለ424 የአኙዋክ ተወላጆች በግፍ መገደል ተጠያቂ የሆነው ኦሞት ኦባንግ ኦሉም በ2004ዓም ከክልሉ መሪነት ከለቀቀ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ክልሉንና ፓርቲውን በጣምራነት ሲመሩ የነበሩት ጋትሉዋክ ቱት በበርካታ ወንጀሎች እጃቸው አለበት በማለት ይጠረጠራሉ። ከግድያ ጀምሮ በሥልጣን መባለግ፣ መረን የለቀቀ ሙስና፣ አድልዖ፣ ብልሹ አሠራር፣ ወዘተ የጋትሉዋክን ስም የማያነሳ የክልሉ ነዋሪ የለም ማለት ይቻላል።
ግፍና ሙስና የሞላበት የጋትሉዋክ ዓመታት
በተለይ በጥር ወር 2008ዓም በሁለት ግለሰቦች (አንድ አኙዋክና አንድ ኑዌር – የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዲን) መካከል በተከሰተ አለመግባባት ምክንያት ጉዳዩ የጎሣ ግጭት መልክ እየያዘ ሲመጣና በውጤቱም ሰዎች ሲሞቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ነበሩ።ጋትሉዋክ ለወገኖቻቸው በማድላት ቅጥር ነፍሰገዳዮችን ወደ እስር ቤት በማስላክ ታስረው የነበሩትን ምክትል ዲን ባስፈቱበት ጊዜ ሰባት አኙዋኮችና ሁለት የመሐል አገር ሰዎች መገደላቸው በእርሳቸው ትዕዛዝ የተከናወነ ድርጊት ነው በማለት በርካታዎች ይከሷቸዋል። ይህ በራሱ ከሥልጣን አስነስቶ ለፍርድ የሚያስቀርብ ነው በማለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ይናገራሉ።
ከዓመት በላይ የክልሉን መስተዳድር ሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ግምገማ እንዲካሄድ ሲጠየቅ የፓርቲውና የርዕሰ መስተዳድሩን ሥልጣን ደርበው በመያዛቸው ጋትሉዋክ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሲያስተላልፉ እንደቆዩ ከክልሉ የተገኘና ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የደረሰ ሰነድ ያብራራል። ይህ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መስከረም 15፤ 2011 የተላከ ሪፖርታዊ ይዘት ያለው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ጋትሉዋክንና አጠቃላይ አመራሩን በአምስት ነጥቦች ማለትም በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሠራር፤ ከፓርቲና መንግሥት አሠራር ውጪ በመሥራት፤ የወጣቶችን ጥያቄ ባለመቀበልና አዲስ መጣውን ለውጥ ባለመቀበል ይሞግታል፤ ጥፋተኝነታቸውንም በማስረጃ ያቀርባል።
በሰነዱ ላይ እንደቀረበው አላስፈላጊ የአገር ውስጥና የውጪ ጉብኝቶችን በማድረግ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በርካታ ገንዘብ ማባከናቸውን ያመለክታል። ዶ/ር ዐቢይ ወደ ኬኒያ በሄዱበት ወቅት ርዕሰመስተዳድሩ “አብሬ እንድሄድ ተጋብዣለሁ በማለት ለአንድ ሌሊት አዳር ብር 200 ሺህ ለትራንስፖርት፣ ለመኝታና ለውሎ አበል” ወስደው አለማወራረዳቸውን ይጠቁማል። ያለ ሕክምና ቦርድ ፈቃድ ወደ አሜሪካ በተደረገ ጉዞ አንድ ሚሊዮን ብር ከክልሉ በጀት መውጣቱንም ያስረዳል። የክልሉ የቢሮ ኃላፊዎችም ለአንድ ቀን የአዲስ አበባ ጉዞ ከ10 – 20 ቀን የውሎ ዐበል እየተከፈላቸው ከደመወዝ ሌላ እንዲተዳደሩ እንደሚደረግ፤ ርዕሰመስተዳድሩ የጎሣቸው አባላት (ኑዌሮች) በጭፍን እንዲደግፏቸው የሚቻላቸውን ቢያደርጉም አፈንግጠው በወጡና “ፕሬዚዳንቱ መምራት አልቻሉም፤ ከሥልጣን ይውረዱ” ብለው በተናገሩ ስድስት ኑዌሮች ላይ አፈናና እስር የመፈጸም ተግባራትን በሥውር ሲያከናውኑ እንደነበር በዘገባው ተገልጾዋል። ይህ ሁሉ ብክነት ሲፈጸም በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ግን ለሦስት ወራት ያህል ያለ ደመወዝ እንዲሠሩ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ሰነዱ ዋቢ ያደርጋል።
ከሙስና ጋር በተያያዘ የአዳራሽ ግንባታ፣ የመንገድ ሥራ፣ የ150 ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ፣ የሦስት ዘመናዊ ሞተር ጀልባ ግዢ፣ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች ግንባታ፣ የትራፊክ መብራት ዝርጋታ፣ ወዘተ ለሚቴክ፣ ከህወሃት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ግለሰቦች፣ ከአመራሩ ጋር በጥቅም ለተሳሰሩ ባለሃብቶች፣ ወዘተ ያለ አንዳች ጨረታ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ቢደረግም አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የግንባታ ፈቃድ የላቸውም፣ እስካሁንም ተሠርተው አልተጠናቀቁም፣ አንዳንዶቹም ያለዲዛይን እንዲሠሩ የተደረጉ መሆናቸው ከጋምቤላ የተገኘው የሰነድ መረጃ ያመለክታል። የተጠናቀቁ የሚባሉትም በጣም በርካሽና በጊዜያዊ ሁኔታ የተሠሩ ከመሆናቸው የተነሳ ከጋምቤላ አየር ማረፊያ ወደ ከተማው የሚወስደው መንገድ እንዲሁም በከተማዋ በተለይም በምክርቤቱ አካባቢ ያለው አስፋልት ትልልቅ ጉድጓዶችን ከመሥራቱ ባሻገር ውሃ የሚያቁር ኩሬ ሰርቶ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የተዘጋ ነው። ሚሊዮኖች የፈሰሱበትን ከኤርፖርት ወደ ከተማ የሚወስደውንም መንገድ የአገሬው ሕዝብ ሲቀልድ “ሽሮ ፈሰስ” እያለ የሚጠራውና ከአገልግሎት ውጪ የሆነ መንገድ ሆኗል።
በ2008ዓም ኢህአዴግ “የብሔር ብሔረሰቦች ቀን” በማለት በጋምቤላ ከበሮ በደለቀበት ወቅት የጋትሉዋክ አመራር መጠነሰፊ ምዝበራ ማካሄዱን ይኸው ለዶ/ር ዐቢይ የተላከው ሰነድ ያብራራል። ኃይለማርም ደሳለኝ በተገኘበት የተከናወነው ሥነሥርዓት ላይ በክልሉ ካቢኔ “ለእንግዶች የምግብ አገልግሎት” በሚል የተመደበው 12 ሚሊዮን ብር ሆኖ ሳለ ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙ ለተባሉት የሆቴል ባለቤትና ከህወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ሴት ለተመሳሳይ ወጪ 16,659,200 (አስራ ስድስት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሁለት መቶ) ብር የተከፈላቸው ሲሆን ከዚህም አብዛኛው ከዚህ በፊት እንደሚደረገው በካሽ በግል እንዲሰጣቸውና ግለሰቧ ከትርፍ እና ከመሳሰለው ግብር ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል ይላል ሰነዱ።
ከዚሁ ሙስና ጋር በተያያዘ ለዋግ ኽምራ ልማት ማኅበር ዕርዳታ በሚል በጋትሉዋክ ፊርማ “በ2006 እና በ2009ዓም በድምሩ 10ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ” የታዘዘ ሲሆን ገንዘቡ ግን ለማኅበሩ “በባንክ ሒሳብ በቀጥታ ከማስገባት (ይልቅ) በግለሰብ ስም ወጪ” መደረጉ ገንዘቡ ለታሰበለት ማኅበር ለመዋሉ ትልቅ ጥርጣሬ እንደሚጭር ሰነዱ ይጠቁማል።
በእነዚህና በሌሎች የሙስና ተግባራት የተበከለው ክልል፤ በ2010 ዓም በክልሉ መንግሥታዊ ቢሮዎችና መ/ቤቶች ላይ ብቻ “በተደረገው ኦዲት ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ ጉድለት መታየቱን ዋና ኦዲተር” ማሳወቁን ሰነዱ ያጋልጣል።
ከፓርቲና ከመንግስት አሠራር ውጪ በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚፈልጓቸውን ሰዎችና የጥቅም ተካፋዮቻቸውን ከቀበሌና ወረዳ አንስተው እስከ ክልል ቢሮዎች ውስጥ በማስመደብ ወንጀላቸውን ለመሸፈን ከመፈለግ አልፈው በርካታዎችንም የወንጀላቸው ተባባሪዎች እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ሰነዱ በተጨባጭ ማስረጃዎች ያስረዳል። ለአብነትም ያህል “በሐምሌ ወር 2010ዓም በኑዌር ዞን በተካሄደው ሹምሽር ለዋና አስተዳዳሪነት የፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያፀደቀውን ግለሰብ፤ ርዕሰ መስተዳድሩ በራሳቸው ሥልጣን በሌላ ሰው” የቀየሩት ሲሆን “በዞኑ ከ25 ሰዎች በላይ በርዕሰ መስተዳድሩ ትዕዛዝ ተሽረው በምትካቸው እርሳቸው የሚፈልጓቸው ሰዎች እንዲሾሙ” ተደርጓል ይላል። ከዚህ በከፋ መልኩ ደግሞ ጋትሉዋክ በሥልጣን ለመቆየት ሲሉ በተቻለ መጠን በአኙዋክና በኑዌር መካከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋና ቢቻል የጎሳ ግጭት እንዲከሰት የተለያዩ ሤራዎችን ሲያቀነባብሩ እንደነበር ከሰነዱ ሌላ የክልሉ ነዋሪዎችም ይመሰክራሉ።
ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የሚገዳደሯቸውን ወጣቶች (ዳልዲሞች) በማስፈራራት፣ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በመግፈፍ፣ ሰልፍ ሲወጡ እንዲገደሉ በማድረግ፣ ወዘተ በርካታ ግፎችን ጋትሉዋክ ቱት ለመፈጸማቸው የዳልዲም አመራሮችና ሌሎች የክልሉ ነዋሪዎች ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። ይህንን ለማሳየትም ከሦስት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ከተማ ከሁሉም ጎሣዎች ተውጣጥተው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉትን ወጣቶች ያለ አንዳች ምክንያት ለእስር ዳርገዋቸዋል። እነዚህም፤ ዶ/ር ማኝ ኦቻላ፣ ኦባንግ ኦጉታ አዲው፣ ኦክዎም ኦጅዋቶ፣ ቻም ቶን፣ ኡጁሉ ኦማን፣ ሩዋክ ቱት፣ ቱዎክ ሞአንግ፣ ባንግ ኩዎን እና ጃስዋ ጀምስ ናቸው።
“አልተደመርንም፤ አንደመርም”
ከላይ በተጠቀሰው ሰነድ በግልጽ እንደሰፈረው በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ አንቀበልም በማለት ከህወሓት ጋር ቁርኝት ያለው የጋትሉዋክ አመራር ይደግፉኛል ያላቸውን ሰዎች ሲያስተባብር እንደቆየ ያስረዳል። በተለይም የዶ/ር ዐቢይ ለውጥ የብሔርብሔረሰቦችን መብቶች የሚደፈጥጥ ነው በማለት የኑዌር ተወላጆችን በማስተባበር “አልተደመርንም፤ አንደመርም” በማለት በዳልዲምና የለውጡ አራማጆች በሆኑ ላይ ተጽዕኖ ሲሳድሩ ቆይተዋል።
እንደማስረጃም ሰኔ 16 በጠ/ሚ/ር ዐቢይ ላይ ከተቃጣው የመግደል ሙከራ በኋላ በተለያዩ የአገራችን ከተማዎች ጥቃቱን የመቃወምና ጠ/ሚ/ሩን የመደገፍ ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ በጋምቤላ ግን ይህንን መሰሉ ሰልፍ ለማድረግ ያቀዱ ወጣቶችና ነዋሪዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ እንደተካሄደባቸው ይናገራሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሌሎች ክልሎች አመራሮች በቦምቡ ጥቃት የተጎዱትን በሥፍራው እየተገኙ ሲጎበኙ የክልሉ አመራሮች ግን ጉዳዩን “በዝምታ ማለፋቸውን” ሰነዱ ያስረዳል።
በለውጡ ምክንያት በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካና ሌሎች ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ወደ አገራቸው እንዲገቡ በተፈቀደው መሠረት የጋምቤላ ክልል ንቅናቄ (Gambella Regional Movement – GRM) እና ለአዲሲቷ ኢትዮጵ የጋራ ንቅናቄ ወደ ክልሉ ሄደው ህዝቡን ለማነጋገር ባሰቡበት ጊዜ ከጋትሉዋክ አስተዳደር ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያደረግባቸው ቆይቶ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቶቹ ወደ ክልሉ እንዲመጡ አቀባበል ለማድረግ በሚጥሩ ወጣቶችና አስተባባሪዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና እንግልት ደርሶባቸው እንደነበር ይኸው ለጠ/ሚ/ር ዐቢይ የተላከው ሰነድ ያስረዳል።
ከፌዴራል መንግሥት ቀጥተኛ ተጽዕኖ ባይደረግ ኖሮ ሁለቱም ድርጅቶች በክልሉ እንዳይገቡ አሻጥር ሲሰራባቸው እንደነበር ጎልጉል ከጉዳዩ ጋር አግባብ ካላቸው ያገኘው መረጃ ያስረዳል።
ግምገማውና አዳዲሶቹ ሹሞች፤ የጋትሉዋክ የማምለጫ ስልት
በሙስና፣ በወንጀልና በበርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተበላሸውን የጋትሉዋክን አገዛዝ ለግምገማ ለማቅረብ በክልሉ የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ያቀረቡት ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ ሲደረግባቸው ቆይቷል። በትውልድ ደቡብ ሱዳናዊ የሆኑት ጋትሉዋክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ብቻ ሳይሆኑ የጋህአዴንም ሊቀመንበር በመሆናቸው ግምገማ እንዳይካሄድ ሲከላከሉ ዓመት አልፏል። በመጨረሻም ከውስጥና ከውጭ በተለይም ከፌዴራሉ መንግሥት በተደረገ ጫና ከጥቅምት 10 – 19፤ 2008ዓም በአዲስ አበባ ግምገማ ሊካሄድ ችሏል። ጎልጉል ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ግምገማው በጋምቤላ ከተማ እንዲካሄድ ጋትሉዋክ ያደረጉት የመጨረሻ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
ግምገማው በተጀመረበት ጊዜ በጋትሉዋክ ላይ 142 ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን የእርሳቸውን ግማሽ ያህሉ ጥያቄ ከባለቤታቸው ጋር የተያያዘ እንደነበር ይነገራል። በግምገማው ወቅት ጋትሉዋክ የሚመልሱት እየጠፋባቸው ብዙ ሲቸገሩ እንደነበሩ እንዲያውም በአማርኛ መናገር ጀምረው ሌሎች ሊሰሙ በማይችሉበት ሁኔታ ሳያስቡት በኑዌር ቋንቋ ፍርሃት በተቀላቀለበት ሁኔታ በመናገር ለማስረዳት ሲጥሩ እንደነበር በስብሰባው የተገኙ ለጎልጉል ተናግረዋል። በመቀጠልም የግምገማው ሁኔታ እያየለ በሄደበት ወቅት ጋትሉዋክ አሞኛል በሚል ከስብሰባው አዳራሽ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው የስብሰባው ተሳታፊዎች ለጎልጉል አስረድተዋል።
የግምገማው ጊዜ ከመጠናቀቁ ጥቂት ቀናት በፊት የፓርቲውንም የክልሉንም ሥልጣን ደርበው የነበሩት ጋትሉዋክ እና ምክትላቸው “በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸው” ተሰማ። በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ እና ከስብሰባው በኋላ ጋትሉዋክ ለፋና በሰጡት መግለጫ “… ችግሩ እኔን የሚመለከት በመሆኑ … ውስጤን በማየት ዕረፍት መውሰድ ስላለብኝ … ያለምንም ተፅዕኖ ሥልጣን ለቅቄአለሁ” ብለዋል። ምክትላቸው ሰናይም በተመሳሳይ ከስልጣን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱም አመራሮች ከፓርቲው ሥልጣናቸው ቢለቁም በማዕከላዊ ምክርቤት ውስጥ አባል ሆነው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለቱም ኃላፊዎች ከክልሉ መስተዳድር ከፍተኛ ኃላፊነታቸው ስለመልቀቃቸው በግልጽ አልተናገሩም፤ በወጡ መግለጫዎችም ላይ ይኸው በግልጽ አልተነገረም።
ግምገማውን እንዲመሩ ከፌዴራል መንግሥት የተወከሉት ፈቃዱ ተሰማ እና ተፈራ ድሪቦ ግምገማው ከመጠናቀቁ በፊት በጋትሉዋክና በሰናይ ምትክ ዑመድ ኡጁሉ የጋህአዴን ሊቀመንበር፤ ታንኩዌይ ጆክ ምክትል አድርገው አስመርጠዋል። ሆኖም ሁለቱ ከፌዴራል የተወከሉትን የግምገማ መሪዎች በርካታ የተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚቀርብባቸው ብቻ ሳይሆኑ ምናልባትም የጋትሉዋክን ዓላማ በማሳካት ሰፊ ሚና የተጫወቱ ናቸው ተብለው በአንዳንዶች ዘንድ ይወቀሳሉ።
በጋትሉዋክና በሰናይ ምትክ የተመረጡት ሹሞች ከጋትሉዋክ ጋር ለዓመታት የሠሩ ሲሆኑ ዋና ሊቀመንበር የሆኑት ዑመድ ኡጁሉ የክልሉ የሥነምግባርና የፀረሙስና ዋና ኃላፊ ነበሩ። ምክትላቸው ታንኩዌይ ጆክ ደግሞ የክልሉ የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ የጋትሉዋክ ሚስት ወንድም ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ታንኩዌይ ጆክ ፈጽሟቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩት ወንጀሎች በተለይ ከሙስና ጋር በተያያዘ የክልሉ ሰዎች “የጋምቤላ አልቅት (ደም መጣጭ)” በሚል ቅጽል ስም ይጠሯዋል። ሹመቱንም ጋትሉዋክ እንደ ንጉሣዊ ቤተሰብ ወይም እንደ ቀድሞ ባላባት ሥልጣኑን ለሚፈልጉት የቤተሰባቸው አባል እንዳወረሱት ተደርጎ ተወስዷል።
ጎልጉል በክልሉ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው ተወላጆች ግምገማውን አስመልክተው እንደሚሉት ከሆነ ግምገማ ከተካሄደና ጋትሉዋክ ራሳቸው እንዳሉት ችግሩ እርሳቸውን የሚመለከት ከሆነ ከሥልጣን መልቀቂያ ሳይሆን ማቅረብ የነበረባቸው ከፓርቲውና ከክልሉ አመራር መባረርና ጥፋተኛ ሆነው ለተገኙበት በሙሉ ተጠያቂ በመሆን በቁጥጥር ሥር መዋል ነው። ሥልጣን የሚለቁ ከሆነ ደግሞ ለግምገማ መቀመጥ አልነበረባቸውም፤ ከግምገማው በፊት ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን መናገር ነበረባቸው ይላሉ። ጋትሉዋክና ተባባሪዎቻቸው በዚህ መልኩ ለፍርድ ቀርበው በሕግ ካልተጠየቁ ወደፊት ወደ ሥልጣን የሚመጡ ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ስለመጠየቃቸው ምን ዋስትና አለ በማለትም ይጠይቃሉ። “ለሞቱትስ፤ በግፍ ለተደገሉት፤ ለዓመታት ለባከነው ብር፤ ውድመት፤ … ተጠያቂው ማነው? የሕዝብን ሃብት እንደፈለግህ አባክነህ ስታበቃ ከዚያ ለማምለጥ ደግሞ ሌላ ገንዘብ ከፍለህ የምትድን ከሆነ ግምገማ ለምን ያስፈልጋል?” በማለት ከዳልዲም ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው የኑዌር ተወላጅ ይጠይቃሉ።
“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የለውጥ ዓላማ አንግበው በአገራችን ብዙ ተስፋ ይዘው የመጡ መሪ ናቸው፤ በሶማሊ ክልል ወንጀለኛ የተባሉትን አብዲ ኢሌ ከሥልጣናቸው ማንሳት ብቻ ሳይሆን ለፍርድ እንዲቀርቡ አድርገዋል፤ በአፋርም ተመሳሳይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፤ በጋምቤላ ግን የተካሄደው ከዚህ ያነሰ መሆኑ በጣም አሳዝኖኛል፤ የጋምቤላ አለመረጋጋት ከኢትዮጵያ አልፎ ደቡብ ሱዳንና ቀጣናው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው፤ ክልላችን ብዙ ብቃት ያላቸው ሰዎች አሉት፤ በጋትሉዋክና አሁን በተሾሙት ዓይነት የህወሓት ተላላኪዎች በመመራት እንዲቀጥል መደረጉ እኔንና ሌሎች በርካታ የክልሉ ነዋሪዎችን አሳዝኗል፤ ለጋምቤላ እንዲህ ከሁሉ ያነሰ፤ “ይህ ይበቃቸኋል” የሚመስል ውሳኔ መሰጠቱ በምንም በማንደራደርባት አገራችን ኢትዮጵያ አሁንም ገና መብታችንን ለማስከበር ብዙ እንደሚቀረን ነው፤ ጥያቄያችን ግን አሁንም ግልጽ ነው – በወንጀልና በሙስና ብዙ መረጃ የተያዘባቸው ጋትሉዋክና ተባባሪዎቻቸው በሙሉ ለፍርድ ይቅረቡ ነው” በማለት አቡድአኳይ የተባሉ የክልሉ ነዋሪ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
gi Haile says
There is no excuse those who are responsible authorities committed fraud, genocide, corruptions, Human rights abusers should face Justice. Power not given to destroy humanity to empowered and to care for their wellbeing. All Dictators shuld resign, but if replaced by other election they must be arrested and let the justice system feal with it. The people knows the bad guys.
Ojulu Odola says
PM Dr Abiy has a leadership problem if he let’s Gatluak Tut and his TPLF”s associates walk out free committing these crimes and fraud.