የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጳጉሜ ወር ለሀገር ሰላም እና አንድነት በመላው ዓለም በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፀሎት እና ምህላ ወስኗል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ፣ ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፥ ቋሚ ሲኖዶሱ 5ቱን የጳጉሜ ቀናት በፀሎትና ምህላ እንዲታሰብ መወሰኑን ገልፀዋል።
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፥ 2013 ዓ.ም ብዙ ችግሮችን ያሳየ መሆኑን ያነሱ ሲሆን “በፈተናው ውስጥም ቢሆን ግን ብዙ በረከቶችን ያሳየን ነገሮች አሉ” ብለዋል። እንደሀገር፤ እንደዓለምም የተከሰቱ ችግሮች ወደቀጣይ ዓመት አብረው እንዳይተላለፉ እግዚአብሔርን በፀሎት መጠየቅ ስላለብን ይህ ውሳኔ ተላልፏል ሲሉ አስረድተዋል።
አክለውም፥ “ቤተክርስቲያን በሀገራችን ውስጥ ያለው ጦርነቱ፣ ረሃቡ፣ ስደቱ፣ መፈናቀሉ፣ ከቦታ ቦታ ያለው ህዝባችን በስጋት እንዳይኖር ይሄን ሁሉ ጉዳዬ ነው ብላ ወደእግዚአብሔር ማቅረብ አለብን በሚል ቀናቱን በፀሎት እና በምህላ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንዲታሰብ ወስናለች” ብለዋል።
“ወደሰዎች ሳይሆን ወደእግዚአብሔር በመፀለይ ለውጥ ይመጣል ፤ ያጣነው ሰላማችን ይመለሳል ፤ ወደእግዚአብሔር መፀለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው ብሩህ ተስፋ፤ ጨለማ ውስጥ ነን ብሎ ለሚያስብ ህዝብ ብርሃን የሆነ ህይወት እንዲኖረው የሀገራችንም ከፍታ እንዲኖር ያደርጋል” ብለዋል።
“በዚህች ሰዓት ይሄ ፀሎት ወሳኝ በመሆኑ ትንሹም ትልቁም በሀገር ውስጥም በውጭም ያለው ቢፆም ቢፀልይ መፍትሄ ይመጣል ፤ አምስቱን ቀን በፀሎት እና በምህላ ማሳለፍ ይገባል” ሲሉ አክለዋል።
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ፅ/ቤት የውጭ ጉዳይ መምሪያ የበላይ ኃላፊና የድሬዳዋና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ፥ ቋሚ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ከጳጉሜ 1 እስከ 5 ድረስ ባሉት ቀናት በአንድነት እና በፍቅር መፀለይ እንደሚገባ ገልፀዋል።
“ምዕመናኑ በአምስቱ ዕለታት ስለ ሀገር ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት፣ በፀሎት እና በምዕላ በትጋት ጊዜውን እንዲያሳልፍ ጥብቅ መመሪያ የተላለፈ መሆኑን በቋሚ ሲኖዶስ በኩል ለየአብያተክርስቲያናቱ እና ገዳማቱ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ላሉ ሁሉ እነዚህን ዕለታት በፀሎት እና በምዕላ እንዲያሳልፍ ተወስኗል” ሲሉ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ለEOTC ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። (tikvahethiopia)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply