የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያን አስመልክቶ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፦
ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት መንግሥት አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዛሬው ዕለት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻሉን ያስታውቃል። ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውስው ይህ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ወደሆነና በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደሚያሸጋግራትና በኢኮኖሚ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትና መዛባት እንደሚያሻሽል ይታመናል። የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የሚተገበር ይሆናል።
ይህ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ላይ የተመሠረተና በቀጣይ ሥራ ላይ ከሚውሉ ሰፊ ማክሮ ኢኮኖሚአዊ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ዋና ግቡ ቀጣይነት ያለው፣ መሠረተ ሰፊና ሁሉን አሳታፊ የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን ለማረጋገጥ ነው።
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያው ቁልፍ ይዘት
ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚከተሉትን ዐበይት አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦችን ያካትታል፡-
1. የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና፣ ገበያውን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ይሆናል።
2. የውጭ ምንዛሪን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀሪ ሆኗል። በመሆኑም፣ ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት ይችላሉ፤ ይህም ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ ያሻሽላል።
3. ቀደም ሲል በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነሥቷል። ወደ ውጭ የሚደረግ የካፒታል ሂሳብ ፍሰት እንደ በፊቱ የተገደበ ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያው ለገቢ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ነጻ ሆኗል።
4. ምርቶችን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለራሳቸው ያስቀሩት የነበረው 40 በመቶ ወደ 50 በመቶ ብሏል።
5. ቀደም ሲል ባንኮች ለተለያዩ ገቢ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ አሠራርና አደላደል ደንቦች ቀሪ ሆነዋል።
6. አሁን በሥራ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (Forex Bureaus) በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ይቋቋማሉ። ለእነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲገዙና እንዲሸጡ የሥራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።
7. ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ረገድ የተጣሉ ክልከላዎች ለማንሳት በቅርብ ጊዜ የማሻሻያ ደንብ ይወጣል።
8. በውጭ ተቋማት፣ በውጭ ኢንቨስተሮች እና በትውልደ ኢትዮጵያውያን (በዳያስፖራዎች) የተከፈቱ የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦችን አስተዳደር የሚመለከቱ በርካታ ሕጎች እንዲላሉ ተደርጓል።
9. በኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከውጭ የሚላክላቸውን ሐዋላ፣ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል ደሞዝን/የኪራይ ገቢን እና ሌሎች ገቢዎችን የሚያስቀምጡባቸውን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች እንዲከፍቱ፣ እንዲሁም እነዚህን የውጭ ምንዛሪ ሂሳቦች ተጠቅመው የውጭ አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ተፈቅዷል።
10. ቀደም ሲል የግል ኩባንያዎች ወይም ባንኮች በሚወስዷቸው የውጭ ብድሮች ላይ ይከፍሉት የነበረው የወለድ ተመን ጣሪያ ተነሥቷል።
11. መመዘኛውን የሚያሟሉ የውጭ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ስነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange) እንዲሳተፉ ተፈቅዷል።
12. በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚሠሩ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ሙሉ በሙሉ ለራሳቸው መያዝን ጨምሮ ልዩ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም መብት ተሰጥቷቸዋል።
13. ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የሚጓዙ ወይም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ሊይዙ በሚገባ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ መጠን ላይ ተጥለው የነበሩ የተለያዩ ጥብቅ ደንቦች እንዲላሉ ተደርጓል።
ከላይ በአጭሩ የቀረቡት የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያዎች ቀጣዩን የኢትዮጵያን የዕድገት ደረጃና ከቀረው የዓለም ሀገራት ጋር ያላትን እያደገ የመጣውን ትስስር ለማጠናከር የሚረዱ ናቸው። እንዲሁም ማሻሻያዎቹ የአስር ዓመቱን መሪ ዕቅድና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራምን በመሳሰሉ ቁልፍ ሰነዶች ውስጥ ከሰፈሩት የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር የተናበቡና ወጥነት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሰነዶች ኢኮኖሚው እየተወሳሰበና እያደገ ሲሄድ ሀገሪቱ ቀስ በቀስ በገበያ ላይ ወደተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት እንደምትሸጋገር የሚያወሱ ናቸው። ይህ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ በውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የዘገየ ቢሆንም፣ አዲስ የበጀት ዓመት መጀመሩና ከዋና ዋና የውጭ የልማት አጋሮች ጋር የተሳካ ውይይትና ድርድር መደረጉ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ መልካም አጋጣሚ ፈጥረዋል።
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርማሻሻያ ለምን?
ከዛሬ ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ ምንም ያህል ቀላል ባይሆንም አስፈላጊ ነው። አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመንና ዝቅተኛ የዋጋ ንረት መኖሩን ለማረጋገጥ የታለመ ቢሆንም፣ በሂደት ግን ለጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ በከበሩ ማዕድናት ሎሚደረግ ሰፊ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ከባንክ ሥርዓት ውጭ እንዲሆንና ከሀገር እንዲሸሽ አንዱና ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ይህ ሁሉ ከአምራች ዘርፎች ይልቅ ጥቂት ሕገወጦችና ደላሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከስት አድርጓል። ከዚሀም የተነሣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ተጎጂ ሆነዋል፤ የወጪ ንግድንና የፋብሪካ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ የተቀመጡ ፖሊሲዎችንና ጥረቶችን ውጤታማነት ሸርሽሮታል።
በአንጻሩ፣ በገበያ ወደሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት መሸጋገር በርካታ ኢኮኖሚአዊ ጥቅሞችን ያስገኛል፡-
አንደኛ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች የተሠማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል። ወደ ውጭ የሚላኩ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት የመሳሰሉ ሸቀጦችን የሚያመርቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ገበሬዎች፣ የቁም እንስሳትና ሥጋ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አርብቶ አደሮችና ነጋዴዎች፣ በወጪ ንግድ ዘርፍ የተሠማሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ በርካታ ዜጎችና አምራቾች፣ በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፎች የተሠማሩ በሺህ የሚቆጠሩ ነጋዴዎች፣ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው/ጓደኞቻቸው የውጭ ምንዛሪ የሚላክላቸው በሚሊዮን የሚገመቱ የሐዋላ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ከውጭ ገንዘብ ፈስስ የሚደረግላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ተቋማት፣ ከእነዚህም ጋር በሽርክና የሚሠሩና ምርት የሚያቀርቡ ሌሎች አካላት የዚህ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ።
ሁለተኛ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱንና ለነዋሪዎችና ለአምራች ዘርፎች ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ ይረዳል። አሁን ያሉ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎች ወደ ጎረቤት አገሮች የሚደረግ የኮንትሮባንድ ንግድን የሚያበረታቱ፣ ላኪዎችና አስመጪዎች የሸቀጦችን ዋጋ ያለአግባብ ከፍ ወይም ዝቅ እንዲያደርጉ የሚገፋፉ፣ የካፒታል ሽሽትን የሚያጠናክሩ፣ በጥቅሉ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትንና በእጅጉ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያሳጡ ናቸው።
ሶስተኛ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ያበረታታል፤ የማምረት ሥራቸውን እንዲያስፋፉና የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። በኢንዱስትሪና በፍጆታ ዕቃዎች ምርት ዘርፎች የተሠማሩ ተኪ ኢንዱስትሪዎች፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት “ኢትዮጵያ ታምርት” በተሰኘው ዕቅድ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ በርካታ ኢንዱስትሪዎች፣ ከማሻሻያው ተጠቃሚ ይሆናሉ።
አራተኛ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የግሉን ዘርፍ ለማሳደግና የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዘመን እንዲሁም ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ የተወሰዱ ሌሎች በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን የሚደግፍና የሚያጠናክር ይሆናል። ከእነዚህም የማሻሻያ እርምጃዎች መካከል፣ ቀደም ሲል ለግል ዘርፍ/ ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ የነበሩ ዘርፎችን (ለምሳሌ፣ ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስ፣ ባንክ፣ ካፒታል ገበያ፣ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ) ክፍት ማድረግ፣ የንግድ ማሳለጫ ሥርዓት ማሻሻል፣ የግል ዘርፍና በመንግሥት ፕሮጀክቶች በአጋርነት ማሳተፍ፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማቋቋም ወዘተ ይገኙባቸዋል። በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱ ዘርፎች የተደረጉ ለውጦች ለግሉ ዘርፍና ለኢኮኖሚ ዕድገት አያሌ መልካም ዕድሎችን ቢከፍቱም፣ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲዎች ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ማነቆ ሆነው በመገኘታቸው ማስተካከያ ማድረግ የግድ ሆኗል።
አምስተኛ፡- የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የንግድ ሥርዓታችንንም ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ከታላላቅ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎችና በማደግ ላይ ከሚገኙ በርካታ ሀገራት መካከል የውጭ ምንዛሪ ቁጥጥር ሥርዓትና የውጭ ምንዛሪ አጥረት ያለባት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ከሕዝብ ብዛት፣ ከሠለጠነ የሰው ኃይል፣ ከተመጣጣኝና ከተወዳዳሪ ግብአቶች (የሰው ጉልበት፣ መሬት)፣ ከተጠናከረ የአየር ትራንስፖርትና ከተሻሻለ ሎጂስቲክስ፣ ከኃይል አቅርቦት፣ ከተፈጥሮ ሀብትና ከማዕድናት አኳያ በብዙ መልኩ ለኢንቨስትመንት ምቹና ሳቢ ሀገር ብትሆንም፣ እነዚህ ሁሉ ዕድሎች በአስቸጋሪና ጥብቅ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ምክንያት ውጤታማነታቸው የተጠበቀውን ያህል አልሆነም። ስለዚህ፣ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ለውጭ ኢንቨስተሮች ማነቆ ሆኖ የቆየውን አሠራር ለማስወገድና ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ይጠቅማል።
ስድስተኛ፡- የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ በኢኮኖሚው ውስጥ ኢ-መደበኛነትንና ሕገ ወጥነትን ሲያበረታቱ የቆዩ በርካታ የንግድ አሠራሮችን ለማስቀረት ይረዳል። አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማዕቀፍ የውጭ ምንዛሪ በባንኮች በኩል እንዲመጣ የማያበረታታ፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያፈሩ ኩባንያዎች ወይም ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ እንዲያሸሹ የሚያደርግ ነው። በውጭ ምንዛሪ የሚካሄድ ኢ- መደበኛ ገበያ እየተስፋፋ በመምጣቱ አብዛኛው የንግድ ማህበረሰብና የሐዋላ ተገልጋዮች በአብዛኛው በጥቁር ገበያ ሲገዙና ሲሸጡ ይሰተዋላል። ስለዚህ፣ዛሬ የተካሄደው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ይህንን የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና እንዲህ ዐይነቱን ኢ-መደበኛ አሠራር በማስቀረት ተወዳዳሪ፣ ግልጽና አመቺ ወደሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መግባትን የሚያበረታታ ይሆናል።
በጥቅሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ሌሎች የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ የወጡ በርካታ የለውጥ እርምጃዎችን ለማጠናከር ይረዳል።
ለፖሊሲው ስኬታማነት የሚወሰዱ እርምጃዎች ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ሰፊ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጓል፡-
አንደኛ፣ በሕዝቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማቃለል መንግሥት ከውጭ የሚገቡ የአንዳንድ መሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በጊዜያዊነት ለመደጎም ወስኗል። በዚህ ረገድ፣ መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚጠቀሙባቸውን ነዳጅን፣ ማዳበሪያን፣ መድኃኒትና የምግብ ዘይትን የመሳሳሉ ከውጭ የሚገቡ የአራት መሠረታዊ ሸቀጦች የዋጋ ጫና በአንድ ጊዜ ወደ ሸማቹ እንዳይተላለፍ ወስኗል።
ሁለተኛ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ የዋጋ ንረት ምክንያት የእውነተኛ ገቢያቸው ዋጋ ለተሸረሸረባቸው ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። በዋጋ ንረት ምክንያት የደረሰውንና ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለማርገብ ሲባል ያለውን የገንዘብ ምንጭ በመጠቀምና የመንግሥትን የበጀት ጉድለት በማያባብስ መልኩ ለመንግሥት ሠራተኞች የኑሮ ዉደነት መደጎሚያ ደሞዝ ለመጨመር ታስቧል። እንዲሁም፣ በከተማም ሆነ በገጠር ለሚገኙ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የሚደረገው የሴፍቲኔት እርዳታ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ተደርጓል። የእነዚህ እርምጃዎች ዝርዝር አፈጻጸም በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የሚገለጽ ይሆናል።
ሶስተኛ፣ የመንግሥትን የማህበራዊ ወጪ ለመደገፍና ሰውጭ ዕዳ ክፍያ የሚውለው ከፍተኛ የብር ወጪ ሌሎች ወጪዎችን በማይሻማ መልኩ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዳ የውጭ ዕዳ ማቅለያ እርዳታ ተገኝቷል። ይህን መሰል እርዳታ ቀደም ብሎ መገኘቱ መንግሥት ለማህበራዊና ድህነት ተኮር ወጪዎች የሚያውለው የሀብት አመዳደብ እንዳይስተጓጎልና በቀጣይ ዓመታትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይረዳዋል።
ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት የመፍትሔ እርምጃዎች ባሻገር፣ ወደ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ለማሳለጥና በገንዘብና በፊስካል ፖሊሲዎች መካከል ቅንጅት መኖሩን ለማረጋገጥ የብሔራዊ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል። ለምሳሌ፡-
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን የሚያረግብባቸው አዳዲስ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ሥራ ላይ ውለዋል። ባንኩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በባንክ ብድር ዕድገት ላይ ካስቀመጠው ገደብ ሌላ፣ የገንዘብ ዕድገት የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ሥርዓቱን እንዳይሸረሽር ለመከላከልና የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚረዳ በመለድ ተመን ላይ የተመሠረተ አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ በቅርቡ ተግባራዊ አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ጠንካራ የገቢ መሠረት ለመጣልና የዋጋ ንረትን የሚያባብሱ (ለምሳሌ ከብሔራዊ ባንክ የሚወሰድ ቀጥታ ብድርን የመሳሰሉ) የመበደሪያ ስልቶችን ሳይጠቀም የመንግሥት ወጪን ለማሳደግ የሚያስችሉ እርምጃዎች ሥራ ላይ ማዋል በመጨረሻም፣ የሽግግር ወቅት ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ የሚረዳ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች ተገኝቷል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ይጨምራል።
ነገር ግን፣ በሁለትዮሽ የማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ (central bank deposits) እና በከረንሲ ልውውጥ (currency swap) መልክ የሚመጣውን 2.8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር አንዲሁም ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እና ከሌሎች ባለብዙ ወገኖች (multilaterals) ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውንና በሂደት ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ይፋ የሚደረገውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አያካትትም። ይህ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የሚለግሱት ልዩ የገንዘብ እርዳታ የመንግሥትን የሪፎርም ሥራዎችን ጥንካሬ ያገናዘበና በአፍሪካ አህጉር ትልቁ ከሚባሉት የገንዘብ እርዳታዎች አንዱ ነው።
በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎች የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ሥራ ላይ መዋል፣ ከሌሎች አጋዥ ማክሮ እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ፣ ኢትዮጵያ ዕድገቷንና የወደፊት ብልጽግናዋን እንድታፋጥን ዐይነተኛ ዕድል ይሰጣታል። ቁልፍ የሆኑ መሰናክሎችንና አደናቃፊ እክሎችን በማስወገድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪዎቹ ዓመታት ትልቅ እመርታ እንደሚያሳይ ይጠበቃል። በዓለም የገንዘብ ድርጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ መሠረት፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ዕድገትን ለማፋጠን፣ የዋጋ ንረትን ለማርገብ፣ የፊስካል አቅምን ለማሳደግ፣ የወጪ ንግድንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
እንዲሁም በዚሁ ትንበያ መሠረት፣ በማሻሻያ እርምጃዎቹ ምክንያት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢከኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል ያድጋል፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ የተጠጋ ይሆናል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ ይደርሳል፣ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ይላል፤ የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል፤ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊዮን ዶላር ( የ3.3 ወራት የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ለመሸፈን የሚበቃ) በላይ ይሆናል። እነዚህ ትንበያዎች በቀጣይ ዓመታት ከላይ በተጠቀሱት ማሻሻያዎች ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ሽግግር ደረጃ የሚያመለክቱ ናቸው።
በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታን የማረጋገጥ ቁልፍ ኃላፊነቱን ከመወጣት ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያውን ስኬታማና ውጤታማ በማድረግ ላይ የሚያተኩር ይሆናል። እነዚህንም ተግባራት ለማከናወን ባንኩ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ስለ ማሻሻያው ተፈላጊውን መረጃ ለሕዝቡና ለገበያ ተዋናዮች በመግለጫ መልክ ይሰጣል።
በዚሁ መሠረት የሚሰጡ ገለጻዎች የሚከተሉት ይሆናሉ፡-
በገበያ ላይ ተመሠርቶ የሚዘጋጀውን የውጭ ምንዛሪ ተመን አመልካች ዕለታዊ መረጃ መስጠት፤ እንደ አስፈላጊነቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስሎሚያካሂደው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ (አጠቃላይ የአቅርቦት መጠኑንና የምንዛሪ ተመኑን ያካተተ) መረጃ መስጠት፤ ስለ ገበያው ውሎ፣ ስለሐስተኛ መረጃዎችና ሌሎች አሉባልታዎች እንዲሁም ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ዐበይት ጉዳዮች መረጃና ማብራሪያ መስጠት፣ ስለ አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መመሪያ ከባንኮች፣ ከደንበኞችና ከሰፊው ሕዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠት።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚቀጥሉት ወራት ለቁጥጥርና ለክትትል ሥራዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣል። አብዛኞቹ የውጭ ምንዛሪ ሥራዎች በውክልና ወደ ባንኮች በመተላለፋቸው፣ ባንኮቹ አዲሱን የውጭ ምንዛሪ መመፊያ በጥብቅ ስለመተግበራቸው፣ በተለይም የውጭ ምንዛሪ ለሕጋዊ ግብይቶች ብቻ መዋሉን ስለማረጋገጣቸው ብሔራዊ ባንኩ ጥብቅ ክትትል ያደርጋል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ ባንኮች ከወጪ ንግድ ገቢ ስለሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ክፍፍል (export retention) የወጡ ደንቦችን፣ ስለባንኮች ዕለታዊ የውጭ ምንዛሪ ሀብትና ዕዳ የተቀመጡ ገደቦችን (dally net open position) እንዲሁም ስለ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር (Anti-Money Laundering) ቁጥጥር የተዘረጉ አሠራሮችን በጥብቅ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።
በውጭ ምንዛሪ ተመን ወይም በአገልግሎት ክፍያ ረገድ የማጭበርበር ድርጊት በጥብቅ የተከለከለ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተለያዩ ዘዴዎችን፣ በተለይም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ በመጠቀምና እንደ አስፈላጊነቱ ከፋይናንስ ደህንነትና ሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር እነዚህን የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች ያከናውናል። ህግን በሚተላለፉት ላይም አስተማሪ እርምጃ ይወሰዳል።
በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ክፍትና ተወዳዳሪ ከሆኑ የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዷ ለመሆን በጀመረችው የለውጥ ጉዞ የሀገራችን ቁልፍ የውጭ ምንዛሪ ተዋናዮችና የባንኩ ማህበረሰብ እንዲሁም ሰፊው ህብረተሰብ ለኢትዮጵያና ለመላ ሕዝቦቿ ጥቅም ሲሉ ለዚህ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን።
Leave a Reply