
በትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) ተላላኪነትና ባንዳነት የፈረሰው ገናናው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከ፴ ዓመት ውርደት በኋላ ዳግም እያንሠራራ ነው። አዳዲስ ባሕረኞችን በውጭ አገር እያሠለጠነ ሲሆን አዳዲሶችን ደግሞ በአገር ውስጥ እያስመረቀ ነው። ትላንት በመሠረታዊ ባሕረኞችን አስመርቋል። ከመከላከያ ማኅበራዊ ሚዲያ ያገኘነው ዜና ከዚህ በታች ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አካዳሚ አዛዥ ኮማንደር ከበደ ሚካኤል በባሕረኞች የምረቃ ፕሮግራም ላይ እንደገለፁት አካዳሚው ባሕረኞች ከባህረኝነት ሙያ ጋር በቀጥታ ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሳይንሳዊ መርሆችን እንዲረዱ ስልጠና ወስደዋል።
ባሕረኞች በባሕር ላይ የሚያጋጥማቸውን ዋና ዋና የሚባሉ መሠረታዊ የባሕር ላይ ደህንነት ትምህርቶች እና ሌሎች ጠቅላላ እውቀት ማግኘታቸውንም ገልፀዋል።
ኮማንደር ከበደ ሚካኤል አክለውም ባሕረኞች ከዋናው የሙያ ትምህርት ጎን ለጎን በወታደራዊ ቁመናቸው የታነፁ፣ ጠንካራ የተስተካከለ አካላዊ ቁመና እንዲኖራቸው የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠና መከታተላቸውን ተናግረዋል።
ከተመራቂ ባሕረኞች መካከል ሲማን ሪኩሬት መንግስቱ አበበ እና ሲማን ሪኩሬት ማህሌት ንጉሴ በሠጡት አስተያየት የሀገር ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በመቀላቀላችን ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ባህረኞቹ በቀጣይ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ እና ተቋማዊ ግዳጅ በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በመሠረታዊ ባሕረኛ ያሰለጠናቸውን አባላት ሲያስመርቅ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የዕዝ አዛዦች ፣የዋና መምሪያ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕለቱም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት ጠላቶቻችን እና ባንዳዎች የህዝብ መከታ እና የሀገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻዎችን እየፈፀሙ ይገኛሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰራዊቱን ስም በማብጠልጠል ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ ሠራዊቱ ፈርሷል፣ ተበትኗል፣ እርስ በርሱ ተጋጭቷል፣ ተደምስሷል በሚል ዘመቻ ላይ ቢጠመዱም ሠራዊታችን ህዝባዊነቱን ጠብቆ ግዳጁን በጀግንነት የሚፈፅም ነው ብለዋል።
ሠራዊታችን እንደጠላት ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ሀገራችን እና የህዝባችን ደህንነት አደጋ ላይ ይወደቅ ነበር ያሉት ኢታማዦር ሹሙ ሠራዊታችን አላፊ አግዳሚ ሽፍታ የሚደመስሰው ሳይሆን በፕሮፌሽን የተገነባ የሀገራችን አለኝታ ሠራዊት ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሰራዊታችንን በከፍተኛ ደረጃ ለመገንባት እየተሠራ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተለይም ባሕር ኃይል ሪፎርሙን መሠረት አድርገን ወደ ቀድሞ ክብሩ በመመለስ የባህር ግዳጆችን እንዲፈፅም ይዘጋጃል ሲሉም ገልፀዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ለመጀመሪያ ዙር የባሕር ኃይል ተመራቂ ሙያተኞች እና ለሠራዊቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት በላቀ ቁርጠኝነት ግዳጅን መፈፀም አሥፈላጊ እና ቀጣይም የሚጠበቅ ነው።
በምረቃ መርሃግብሩ ላይ የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባህር ሃይል ካላቸው ቀደምት አገራት አንዷ ነች። ከዛሬ 30 አመት በፊት ኢትዮጵያ የባህር ሃይል እንዳይኖራት የተደረገው በራሳችን ድክመት ነው።
የፈረሰውን የባህር ሃይል እንዲድራጅ የተወሰነው ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ቀደምት የባህር ሃይል ያላት አገር በመሆኗም ጭምር ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤ በኢትዮጵያ ትልቅ የባህር ሃይል እየተገነባ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ስፍራዎች በተለይም ባህርዳር፣ አባይ ግድብ፣ ደብረብርሃንና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የባህር ሃይል ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፊልድ ማርሻሉ አያይዘውም፤ በተለያዩ የውጭ አገራት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የባህር ሃይል ባህረኞች እየሰለጠኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሰራዊት ገንብተን ለሚቀጥለው ትውልድ እናስረክባለን፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ደህንነት አይደራደርም፤ ሰራዊቱ የተወሰኑ ብሄሮች ስብስብ፣ የገዥውና የማንም ፓርቲ ተለጣፊ አይደለም ሲሉም ነው የተነጋሩት።
የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ የሆነ የኢትዮጵያ ከለላና መከታ የሆነ ሰራዊት አለን ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ የኢትዮጵያ ሰራዊት በጥብቅ ዲስፕሊን የሚመራ የኢትዮጵያና ህዝቦች አለኝታ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ተመራቂ የባህር ሃይል ሰልጣኞች በዲስፕሊን በመመራት የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ደህንነት ለማስጠበቅ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሟርተኝነት የበዛበት ወቅት በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊት ስም የሚያጠፉ በዝተዋል። በወሬ መከላከያ ሰራዊት አይበተንም፣ አይደመሰስም። በውጭ ያቃታቸው ሃይሎች በውስጥ የለጠፉልን ሃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እናስከብራለን ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ በምረቃ ስነስርአቱ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ነባር የባህር ሃይል ቢኖራትም ላለፉት አስርት አመታት የባህር ሃይል ሳይኖራት ቆይቷል። መንግስት ባደረገው የእንደገና ማደራጀት፣ በ2011 ዓም ባህር ሀይሉ እዲደራጅ ተደርጐ ላለፉት አራት አመታት የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የባህር በር ባይኖራትም 95 በመቶ የሚሆነው የወጭ ንግድ የሚከናወነው በባህር በር በመሆኑ የባህር ሃይል ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የቀይ ባህር ቀጠና አሜሪካን ጨምሮ የበርካታ ሃያላን አገራት ትኩረት የሚስብ ነው። በተለይም የባህር ላይ ውንብድናን ለመከላከል ብቁ የባህር ሃይል ማደራጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና በባህር ላይ ለሚሰነዘርባት ጥቃት፣ የባህር ላይ ውንብድና፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ስጋቶች ይስተዋላሉ ብለዋል፤ ሬር አድሚራል ክንዱ።
የኢትዮጵያን መርከቦች ደህንነት ለማስጠበቅ በቂ የባህር ሃይል መገንባት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ነው ያሉት ሬር አድሚራል ክንዱ፤ ይህን ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።



ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ እየተወሳሰበ ከመጣው የውሀ ላይ ውንብድና እና ተግዳሮቶች አኳያ ሀገራችን ኢትዮጵያ የባህር ኃይል ያስፈልጋታል ያሉት ሬር አድሚራል ክንዱ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳ ኃይል ከውሃማ አካል ወደ ውሀማ ወይም ከውሃማ አካል ወደ የብስ ሊቃጡ የሚችሉ ስጋቶችን የባህር ኃይላችን ይከላከላል ብለዋል።
ባህር ኃይል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን እጩ መኮንኖች ከዩኒቨርሲቲ መልምሎ በተለያዩ የውጭ ሀገራት እያሥተማረ ሲሆን ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 80 በመቶ የሚሆኑ የ4ኛ አመት 20 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የ3ኛ አመት የባህር ኃይል ካዴት ትምህርት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ገልፀዋል።
ተመራቂ መሠረታዊ ባህረኛ በአንድ ተዋጊ መርከብ ላይ በሚኖሩ ሙያዎች ተለይተው በየሙያ ዘርፉ ሰልጥነው የአለም አቀፉን የማሪታይም ስታንዳርድ አሟልተው ለምረቃ የበቁ ናቸው ብለዋል።
ከባሕር ኃይሉ እድገት ጋር አብሮ እንዲያድግ ታሳቢ በማድረግ ቀሪ ስልጠና የሚቀራቸው የማሪን ኮማንዶ ሻምበሎችን በመመስረት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የባሕር ኃይል መሠረታዊ ባሕረኞች ስልጠና ማዕከል ግንባታ በከፍተኛ ትጋት እና ፍጥነት እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል። ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ባሕረኞችን ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ሐገር ተማሪዎችን በመቀበል በወታደራዊ መስክ የራሱን ሚና ይወጣል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የስልጠና ስራዎችን በማጠናቀቅ በየትኛውም የውሃ አካል ላይ ግዳጅ ተቀብሎ ለመስራት በሚያስችለው ቁመና ላይ ይገኛልም ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአየር ኃይል አቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ወደ አገልግሎት የመለሳቸውን ፈጣን ተዋጊ ጀልባዎችን ጎበኙ።
ተዋጊ ጀልባዎቹ በቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አገልግሎት የሠጡ ሲሆን ዳግም የባሕር ኃይሉን ዝግጁነት እንደሚያጠናክሩ ተገልጿል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል አቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከል ከ30 አመት በላይ ተገለው እና አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ጀልባዎችን ዘመኑ የሚጠይቀውን የፈጣን ተዋጊ ጀልባ ቴክኖሎጂ እና መሳሪያዎች በመግጠም ለግዳጅ ዝግጁ ማድረግ ችሏል።
(ፎቶግራፍ ምስጋናው ከበደ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
የባህር ወደብ ከሌላቸው ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያ የባህር ሃይል ሲኖራት ቀዳሚ ልትሆን ትችላለች። ወያኔ ለምኖ ያስረከበው የአሰብና የምጽዋ ወደብ ዛሬ ከየት ሊገኝ። ይህን መጣጥፍ ሳነብ አንድ ጉዳይ ትዝ አለኝ። ሁሉ ነገር ሞልቶልኛል የሚል በቅርብ የማውቀው ሰው በጣም ውድ የሆነ መኪና ገዛና በሳምንቱ ተበሳጭቶ እባክህ ብቅ በልና infotainment system እንዴት እንደሚሰራ ታሳየኛለህ። እኔ ብዬ ብዬ ምንም ሊገባኝ አልቻለም። በዚያውም ትነዳዋለህ በማለት እንደ ቀልድ ብጤ ጣል አርጎ ጠየቀኝ። ነገርየውን ሂጄ ሳየው መኪና ሳይሆን የገዛው ኮምፒውተር ነው። ውስብስብ ነገር። ግራም ነፈሰ ቀኝ የምችለውን አመላክቼና መኪናውን ከነዳሁ በህዋላ አድንቄ “የገዛኸው መኪና ሳይሆን ኮምፒውተር ነው” ስለው ከት ብሎ ሳቀ። አይ አራቱን ጎማ ብታላቅቅ የቀረህ እሱ ነው አልኩት። መሳቅ ይወዳል ይኽን ያህል ንብረት አፍስሸበት ኮምፒውተር ነው ትላለህ በማለት እየሣቀ ቀናችን አበቃ።
ይህ የባህር ሃይል ነገርም ለዓይን ይማርካል። ፎቶው፤ ስፍራው በጣም ደስ ይላል። ግን ዓላማው ምን ይሆን በማለት ብዙ አሰላሰልኩ። መልስ የመጣልኝ ሁለት ነው። አንደኛው ምን አልባት ያው የዓለም ወታደራዊ አሰላለፍ አሁን ላይ እየዋለለ በመሆኑ ሌላ ሃያላን መንግስት ሊገለገልባቸው እያዘጋጀ እንደሆነ አልኩና በሌላ ጎኑ ደግሞ ያው መከረኛው የኤርትራ ወደብ ላይ ለመፋለም ይሆናል በማለት በመላ ምት ሃሳቤን ቋጠርኩት።
የእኔም ግምት ሆነ የሌላው ሰው እንዳለ ሆኖ በጥቅሉ የባህር ሃይሉ ተጠናክሮ አሁን ባለበት ሁኔታ ላይ መሆኑ በጣም ደስ የሚል ነው። በእርግጥ ከ 30 ዓመት በህዋላ ኢትዮጵያዊ ልብ ያለው የባህር ሃይል መገንባት ቀላል አይሆንም። ስንቱ ነው የቀይ ባህር የበላው? ስንቱ ነው በየመን፤ በጅቡቲ፤ በሳውዲና በሌሎች ሃገሮች የተሰደደው? የሞተው ሞቶ፤ የታገተው በሻቢያ ታግቶ፤ ነፍሴ አውጭኝ ያለው ደግሞ ዛሬ ላይ በህይወት ያሉት በባህር ሃይሉ መመስረት እጥፍ ደስታ እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። የባህር ሃይሉ የወደፊት ተግባር ጊዜ የሚገልጠው በመሆኑ ለአሁኑ መቋቋሙ ብቻ አጥጋቢ ነገር ነው። በርቱ!