ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ጋር በጽ/ቤታቸው በተወያዩበት ወቅት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ማዘጋጀት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።
በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሊካሄድ ስለታሰበው ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤን ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗን ነው አቶ ደመቀ መኮንን የገለፁት።
አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ስለ ጽ/ቤታቸው ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የአፍሪካና ሩሲያ ኩባንያዎች በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል የኢኮኖሚ ትብብር ማህበር መቋቋሙን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አያይዘውም የጉባኤው ዝግጅት አካል የሆነ ውይይት በመጪው ክረምት ከአፍሪካ ህብረትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትፈልግ አቶ ደመቀ ለአምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ገልጸውላቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩስያ በቴክኖሎጂ፣ በጸጥታ እና ደህንነት፣ በግብርና፣ በኑክሌር ቴክኖሎጂ እና ህክምና ዘርፎች ላይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ መወያየታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ዋና ጸሀፊ የሆኑት ሚስተር ኦሌግ ኦዝሮቭ አቶ ደመቀ መኮንን ሞስኮን እንዲጎበኙ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ግብዣ እንደቀረበላቸው መናገራቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባኤ ባለፈው ዓመት በሩሲያ ሱቺ የተካሄደ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባኤው ላይ መገኘታቸው የሚታወስ ነው። (ኢቢሲ)
Leave a Reply