
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለሚከሰቱ ግጭቶችና የሰላም እጦት ችግሮች ሙስና ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ አስታወቀ። ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በሙስና ከዓለም 87ኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች ተጠቁሟል።
የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሳሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ሙስና በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ግጭቶችና የሰላም እጦቶች ዋነኛ መንስኤ ነው።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የጸረ ሙስና ስምምነቶችን ብታደርግም፤ የጸረ ሙስና ትግሉን የሚያጠናክሩ ተቋማት አለመኖራቸው ውጤታማ ስራ እንዳይሰራ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ።
በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና የሰላም እጦቶች በአንድም ሆነ በሌላ ከሙስና ጋር የተያያዙ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ሳሙኤል፤ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ ዋነኛ ምክንያት ማህበረሰቡ ሙስና የሀገር ገዳይ ነቀርሳ መሆኑን አለመረዳቱና እንደብልጠት መቁጠሩ ነው ብለዋል። ከዚህም ባለፈ የኑሮ ውድነት፣ ድህነትና ሀገራዊ እሴት እየተሸረሸረ መምጣት ለሙስና መስፋፋት መንስኤ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በፍትህና በፀጥታ ዘርፎች፣ በሽያጭና ግዢ በተለይም ከመሬት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በብድር አሰጣጥና እጥረት ባለባቸው የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ዙሪያ ሰፋ ያለ ያለአግባብ የመበልጸግ እና የሌብነት ተግባራት የሚታዩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሙስና ተግባራቱ ኅብረተሰቡን ያማረሩ ችግሮች መሆናቸውንና በአገር እድገትና የብልፅግና ጉዞ ትልቅ እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀው፤ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍና ሙሰኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የጀመረውን እንቅስቃሴ በጥንካሬ አንስተዋል። የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለፃ፤ ሙስናን ለመከላከል የመንግሥት አስተዳደርና በህብረተሰቡ ውስጥ የፀረ-ሙስና ባህልን ማሳደግ አስፈላጊ ነው። በባለሥልጣናት እና በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ላይ የውጭና የውስጥ ቁጥጥር ዘዴዎችን ማጠናከርም ያስፈልጋል። ይህም የሙስና ወንጀሎችን በብቃት ከመለየት ባለፈ ሙስናን በዘላቂነት ለመከላከል ያስችላል።
ሙስናን በትክክል መዋጋት የሚቻለው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከሚሳተፉ ተቋማት ጋር መስራት ሲቻል ነው ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ ስለዚህ በዚህ ዓመት በመንግሥትና በህብረተሰቡ ጥረት ለሚሰሩ ተግባራት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል። ሙስናን መታገል በተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ህብረተሰቡ ሙስናን በተግባር የሚታገልበት፣ በሥነ ምግባር እራሱን የሚያንጽበት ሁኔታን መንግሥት ማመቻቸት ይኖርበታል። ከዚህም ባለፈ ለሙስና አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የመንግሥት ቁጥጥርና የመከላከያ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በየዓመቱ የሙስና ቅኝት ጥናት በማካሄድ የሀገራትን የሙስና ሁኔታ የሚያሳይ ደረጃና ውጤት ይፋ የሚያደርግ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የሙስና ቅኝት የ2021 ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት ውስጥ 39 ከመቶ ነጥብ በማግኘት 87ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስፍሯል። (አዲስ ዘመን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply