
የኢትዮጵያ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በተለያዩ ኤጀንሲዎች ውስጥ የሚሰሩ 7 የውጭ አገር ዜጎች በ72 ሰዓት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ማስተላለፉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢቲቪ በላከው መረጃ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት የመንግሥታቱ ድርጅት ባልደረቦች በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ መሆናቸውም ነው የተገለፀው።
የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት የውጭ አገር ዜጎች የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ የዩኒሴፍ ሃላፊ አዴል ኮርድ፣ የተራድኦ ምክትል አስተባባሪ ግራንት ሊያቲ፣ የተራድኦ ምክትል አስተባባሪ ተወካይ ጋዳ ኤልታሂር ሙዳዊ፣ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ምክትል አስተባባሪ ሰኢድ መሀመድ ሀርሲ፣ ሶኒ ኦኔግቡላ የስብዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ የቡድን መሪ፣ ክዌሲ ሳንስኩሎት የኦቻ የሰላምና ልማት አማካሪ እና ማርሲ ቪጎዳ የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የቢሮ ኃላፊ ናቸው። (ETV)
እነዚህ ግለሰቦች ከተሰጣቸው ሃላፊነት ውጪ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ለትህነግ የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ሲፈጽሙ የቆዩ መሆናቸው በቢሮአቸው ስም ሲወጡ የነበሩ ክሶች ያመለክታሉ።
ግለሰቦቹ በተቻላቸው መጠን ኢትዮጵያን የሚጎዳ መረጃን በማጋነን በማውጣት ወይም ት ህነግን የሚያስወቅስ መረጃ ትኩረት እንዳይሰጠው በማድረግ ወይም በማዳፈን በዓለምአቀፍ ሚዲያ ላይ ከተጠመዱት ጋር በጥምረት ሢሠሩ ነበር።
እርምጃው የዘገየ ቢሆንም መደረጉ ግን በጣም አስፈላጊና ለኢትዮጵያም እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሉ አስተያየቶች በብዛት ተሰምተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ቀናት በፊት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን “አንዳንድ የአሜሪካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች የተለያዩ ደባዎችን እየሰሩ ነው” ማለቱ ይታወሳል።
የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አንዳንድ የአሜሪካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች ለተፈናቃይ ወገኖች እርዳታ ለማቅረብ ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶች እያቀረቡ ነው ብሏል።
በኮሚሽኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ-ኢብኮ በሰጡት ቃል፥ የተራድኦ ድርጅቶቹ “ጦርነት ባለበት እንዴት እንገባለን”፣ “የተረጋጋ ሠላም አምጡልን” እንዲሁም “ሃብት የለንም” የሚሉ ተቀባይነት የሌላቸውን ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ መርሁ በሚያዘው መሰረት የተራድኦ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ተንቀሳቀሱ ድረስ የኢትዮጵያን ህግ ጠብቀው የሰብዓዊ እርዳታ የማቅረብ ግዴታ አለባቸው ያሉት አቶ አበበ የተራድኦ ድርጅቶቹ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ገብተው እርዳታ የማቅረብ የውል ግዴታ ቢቀበሉም ተግባራዊ አለመሆኑን ገልፀዋል።
መንግስት የተራድኦ ድርጅቶቹ ገበተው እርዳታ እንዲያቀርቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የሚፈልጉ አንዳንድ የአሜርካና የአውሮፓ የተራድኦ ድርጅቶች የተለያዩ ደባዎችን እየሰሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ደበበ፥ “ይህን ደባ ለማለፍ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ በወሮታና ኮምቦልቻ በቂ የእለት ደራሽ እርዳታ ክምችት አለ” ሲሉ አስረድተዋል። ችግሮችን በቅርበት ተረድቶ አፈጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችልም የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከለት በባህር ዳር፤ ኮምቦልቻና አፋር ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ማዕከላቱ የጤና፣ ውኃ፣ ምግብና የስነ ልቦና እና የጸጥታ ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት እንደሚያስችሉ ነው ለብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል የጠቆሙት።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
እነዚህ የተራዶ ሰራተኞች አይደሉም። ለስም ብቻ እንዲሁ ከተሰጣቸው የሥራ እርከን መረዳት ይቻላል። ተቀምጠው የሚቀለቡ እንጂ! እነዚህ በተለያየ የግልና የመንግስት የስለላ መረብ ውስጥ የተጠላለፉ ታዛዥና ለወያኔ አቀብሉ የተባሉትን የሚያቀብሉ ተላላኪዎች ናቸው። የሚለቀሰው፤ ኡኡታ የምንሰማው ራሱን በራሱ አቁስሎ ሌላውን ወገን ስለሚበጠብጠው ወያኔ መራብ እንጂ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለእነዚህ ጉዶች ጉዳያቸው አይደለም። የአሜሪካ መንግስት አሁን እነዚህ ሰዎች ሊባረሩ ነው ብሎ ዛቻና ማስፈራሪያ ጭምር መደፋቱ የቱን ያህል እነዚህ በስመ ተመድና በሌሎችም የእርዳታ ድርጅት ስም ገብተው የሚሰልሉለት ሥራ መስተጓጎሉ አበሳጭቷቸዋል እንጂ ለህዝብ መራብና መራቆት ለዚያውም ለጥቁር ህዝቦች ደንታ የላቸውም።
እውነተኛ ሰው ሊረዳው የሚገባው ነገር እነዚህ ሰዎች ቀደም ባለው በወያኔ ግዛት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከወያኔ ጋር ሰርቀው የሚካፈሉ ወያኔያዊ ፍቅር ያላቸው መሆኑን ነው። የዓለም የጤና ጥበቃ ሃላፊው ሁሌ የሚያላዝነው ስለ ትግራይ ህዝብ መራብና መቸገር መሆኑ ምን ያህል ከወያኔ ስልትና ብልሃት ጋር ጭንቅላቱ እንደገጠመ ያሳያል። በሰውነቱ የሚያምን ሰው የሌላውንም መከራና ችግር ይረዳ ነበር። ትህነጎች ግን የሰው አውሬ ስብስቦች ናቸው። በቅርቡ አምስቱ ወታደራዊ ጄኔራሎች የሰጡትን መግለጫ ልብ ብሎ ላዳመጠ እብደታቸው ሰማይ ላይ መድረሱን ያሳያል። የሚያሳዝነው ግን ደጋፊዎቻቸው የሚያናፍሱት የፈጠራ ወሬና ድጋፍ ነው። እንዴት ሰው ለአበደ ሰው እሳት ያቀብላል? ለመሆኑ እልፍ የትግራይ ልጆች ረግፈው እነዚህ ሰዎች በድል አድራጊነት ወጣን ቢሉስ ጥቅሙ የቱ ላይ ነው? ግን ፓለቲካ በጭቃ የተለወሰ ውሸት ይዞ ነው ሰው የሚያወናብደው። በጊዜው ያስጨፍራል፤ እየተዘፈነ ያገዳድላል፤ ከዚያ የተሞተለት ዓላማና ግብ ወደ ኋላ ተገፍቶ በአዲስ “እኔ ብቻ” ፓለቲካ ይተካና ሰውም አብሮ እንደ ቀደመው ይተማል። ፍሬፈርስኪ ፍልስፍና! አሜሪካና ደጋፊዎቿ የሚፈልጉት አሜን አለሁ እዘዙኝ ልታዘዝ የሚል መንግስት ነው። ያ ተላላኪ መንግስት ደግሞ ቀን ሲጨልምበት ሰካራም እንደረገጠው እቃ አጨራምተውት ያልፏሉ። በዓለም ዙሪያ ያየነውና የምናየው ሴራ በዚሁ ወልጋዳ የውጭ ፓሊሲያቸው የሚመራ ነው።
የሃበሻው መንግስት እነዚህ ሰዎች በ 72 ሰአት ውጡ ከማለቱ በፊት በሰውና በኤሌክትሮኒክ ወይም በሌላ መንገድ በተቀናበረ መንገድ መረጃ በማቀናበር መረጃውን ከተመድና ከሚመለከታቸው ሃገራት ጋር አጋርቶ ቢሆን አሁን ለምን ለሚሉ አውቆ አበዶች አፍ መዝጊያ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ይውጡ ከተባሉ በህዋላ መረጃ ማቅረቡ ያን ያህል ጠቃሚነት ላይኖረው ይችላል። ትግራይን እንገነጥላለን፤ ትግራይ የራሷ መንግስት ትሆናለች ብሎ የሚሰራው ወያኔ ቶሎ ቢገነጠል ጥሩ ነበር። ያው የጫካውን ቅዥት እውን ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ግልጽ ነው። ልክ ከሱማሊያ ተገንጥላ ሃገር ነኝ እንደምትለው የሃርጌሳዋ ሱማሌ አብሮ መኖርን የጠላ ምንጥቅ ማለት ነው። ግን የምንካፈለው ሃብት አለ የሚለው ጡርንባ ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን እንደሚለው ወልጋዳና የተገላቢጦች ሃሳብ ጋር ይመሳሰላል። ለዘመናት የተመዘበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ/ከትግራይ የሚጠይቀው ሃብት ይኖራል። የአማራ ገበሬና የአፋር ወገኖቻችን ባይሆን እንኳን የሊጥ መያዣ እቃቸው እንዲመለስላቸው ይሻሉ። የማይጠራ ሁሌ የመገዳደል ፓለቲካ። በዘርና በቋንቋው፤ በክልሉ ጭንቅላቱ የላሸቀ የሙታን ስብስብ ሙት ሆኖ ሌላውን ይዞ የሚሞት ህልፈተ ቢስ የሁልጊዜ ያዘው ጥለፈው የማይሰለቸው የሃበሻ ፓለቲካ ቋቅ ከማለት አልፎ ያስታውካል። በቃኝ!