
በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ ሰብሳቢነት በተመራውና በአሸባሪነት የተፈረጀውን ሕወሃት ለመደገፍ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች በአሜሪካ ክገር ምርመራ ተካሂዶ ክስ እንዲመሰረትባቸው ተጠይቋል።
ህወሃትን ለመደገፍና በህዝብ የተመረጠን መንግስት ከስልጣን ለማውረድ በተጠራው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ምርመራ እንዲካድባቸውና ክስ እንዲመሰረትባቸው የጠየቁት በአሜሪካ አገር ያሉ አራት የትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ናቸው።
ብርሃኔ ገብረክርስቶስ፣ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ፣ ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፣ በቀለ ገለታ፣ ዶ/ር ታደሰ ውሂብ ፣ ኩላሂ ጃለታ፣ ዶናልድ ይማማቶን ጨምሮ 14 ግለሰቦች ናቸው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ምርመራ ተደርጎባቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተጠየቀባቸው።
ግሰለቦቹ እንዲከሰሱ የሚጠይቀውን ማመልከቻ ድርጅቶቹ ለአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በግለሰቦቹ ላይ ምርመራ እንዲካሄድባቸውና ክስ እንዲመሰረትባቸው ያበቃቸው ምክንያት በደብዳቤያቸው ላይ የጠቀሱ ሲሆን፣ በአሜሪካ መንግስት በውጪ ጉዳይ ፖሊስ እና ብሔራዊ ጥቅም ላይ የተፈፀመው ጉዳቶችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ረጅም ዓመት የዘለቀ ወዳጅ አገር መሆናቸወን የጠቀሰው ማመልከቻው አሜሪካ ወዳጅ በሆነችባቸው አገሮች ውስጥ በህጋዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት በሀይል ለማውረድ ማሴር ህገ-ወጥ መሆኑን አንቀፅ ጠቅሰው አመልክቷል።
በማመልከቻው ስማቸው የተጠቀሰው ግለሰቦችም ይህን የአሜሪካ ህግ በሚጥስ መልኩ ተሳትፈው መገኘታቸውንም አስረድተዋል ሲል ሸገር ኤፍ ኤም ዘግቧል።
ይህም በመሆኑ በአሜሪካ መንግስትና በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ እንዲሁም በኢትዮጵያ በሚገኘው ኤምባሲዋ ላይ ጉዳት ደርሷል ሲሉ ድርጅቶቹ አመልክተዋል።
ድርጅቶቹ በማመልዕክታቸው ሕወሃት በኢትዮጵያ ያደረገውንና እያደረሰ ያለውንም ጉዳት በዝርዝር ማስቀመጣቸውም ተገልጿል። (አዲስ ማለዳ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply